Tuesday, February 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቀድሞው የበጎ አድራጎት ሕንፃ ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ማኅበር ሊመለስ ነው

የቀድሞው የበጎ አድራጎት ሕንፃ ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ማኅበር ሊመለስ ነው

ቀን:

‹‹የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ማኅበር›› ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በዘመነ መንግሥታቸው (1923-1967) ያቋቋሟቸውና በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት ስር ከዋሉት የቀድሞ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሕንፃዎች መካከል፣ አንዱ እንዲመለስለት ለመንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ ያቀረበው ጥያቄ ዘንድሮ አንድ ዕርምጃ ወደፊት ሂዷል፡፡ ትክክኛውን ቀን በውል ለመግለጽ ቢያስቸግርም ጥያቄው በቅርቡ አዎንታዊ ምላሽ ያገኛል ተብሎ ተስፋ ማሳደሩን የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ገልጸዋል፡፡

ሚያዝያ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደው የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ሰብሳቢው ሊቀ ካህናት አባይነህ አበበ እንደገለጹት፣ አንድ ዕርምጃ ወደፊት የደረሰውን ይህንን ጉዳይ ማኅበሩን ወክለው ከመንግሥት ጋር በመነጋገር እንዲያስፈጸሙ የማኅበሩ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ዳዊት ዘውዴ እና የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የልጅ ልጅ ልዑል በዕደማርያም መኰንን ተመድበዋል፡፡

የሕንፃው መመለስ ለማኅበሩ የዓላማ ማስፈጸሚያ በተለይም በተለያዩ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ለሚገኙና በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ለሚያስመዘግቡ ችግረኛ ተማሪዎች ማኅበሩ ለሚሰጠው ስኮላርሺፕ የገቢ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል ሰብሳቢው አመልክተው መንግሥትም ይህንን በመገንዘብ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዳሰበበት አስረድተዋል፡፡

በዋቢ ሸበሌ ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ በተከናወነው በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የማኅበሩን የሥራ ክንውንና የሒሳብ መግለጫዎችን የዳሰሱ ሪፖርቶች ቀርበው ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ ከቀረበውም የሥራ ሪፖርት ለመረዳት እንደተቻለው ማኅበሩ በአሁኑ ጊዜ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ 70 ችግረኛ ተማሪዎች ነፃ ስኮላርሺፕ ሰጥቷል፡፡ በተለያዩ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ከሚገኙ ከእነዚሁ ተማሪዎችም መካከል በሕክምና ዶክተር 32፣ በሲቪልና በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ 11 ይገኙበታል፡፡

እንዲሁም ከአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ ጋር በመተባበር ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የገቢ ማሰባሰቢያ በዓል ለማካሄድ ታቅዶ ለተግባራዊነቱ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ በመካሄድ ላይ መሆኑ በጉባኤው ተመልክቷል፡፡

ማኅበሩ ቀደም ሲል በሰጠው ስኮላርሺፕ የሕክምና ትምህርቱን ተከታትሎ በመመረቅ በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ የሚገኘው ዶ/ር መርስኤ ሞገስ፣ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ እስከተመረቀበት ዕለት ድረስ ማኅበሩ 5,400 ብር ድጋፍ እንዳደረገለት ገልጿል፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ግን እሱና የስኮላርሺፕ ተጠቃሚ የሆኑት መሰል ጓደኞቹ ለማኅበሩ ዓላማ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ ከማድረግ እንደማይቆጠቡ አስረድቷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የማኅበሩ አባል፣ ዕውቅ የታሪክ ጸሐፊና ጋዜጠኛ የነበሩትና በቅርብ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አምባሳደር ዘውዴ ረታ ‹‹የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት›› በሚል ርዕስ ካሳተሙት መጽሐፍ አንድ ሚሊዮን ብር የሚያወጣው ሁለት ሺሕ ኮፒ በመላ አገሪቱ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ለሚገኙ ቤተ መጻሕፍት በቅርቡ በነፃ እንደሚታደል የማኅበሩ አባል ኢንጂነር ተረፈ የራስ ወርቅ አስታውቀዋል፡፡

ኢንጂነሩ ለጉባኤው ታዳሚዎች እንደገለጹት መጻሕፍቱ ለቤተ መጻሕፍቱ እንዲሰጥ የተደረገው በቀብሩ ሥነ ሥርዓት ፍጻሜ ላይ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ብዛቱና የዋጋው መጠን ከፍ ብሎ የተጠቀሰው መጻሕፍት ለኅብረተሰቡ በነፃ እንዲሰጥ በፈቀዱት መሠረት ነው፡፡

ኢትዮጵያን ከድህነት አረንቋ ለማውጣት በሚደረገው ትግል በተለይም የትምህርት አገልግሎት ለማዳረስ በመሳተፍ፣ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በዚሁ ዘርፉ ያደረጉት አስተዋጽኦ ሕያው የማድረግ ዓላማ ያነገበው የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ማኅበር የተቋቋመው ሐምሌ 16 ቀን 1987 ዓ.ም. ሲሆን፣ መንግሥታዊ ያልሆነ የበጎ አድራጎት ማኅበር በመሆን የተመዘገበው ደግሞ ጥር 4 ቀን 1991 ዓ.ም. ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቤተክህነት ባቀረበችው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዕሮብ ተቀጠረ

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገወጥ ነው በተባለው አዲሱ ሲኖዶስና...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...