Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የአገር ጉዳይ ትርፍና ኪሳራ አይወራረድበት!

ሰላም! ሰላም! ምን ሰላም አለ አጥፍቶ ጠፊ በአስብቶ አራጅ ተተክቶ አትሉኝም። ‹‹እንዲያው ይህቺ ዓለም፣ ገሎ ከሚፎክር ይልቅ የሚቀበር ጠላት የሚመሰገንበት ዘመን ላይ ትድረስ? አሸባሪ ቆሞ ከሄደ ተሸባሪ ምኑን እንቅልፍ ባይኑ ዞረ?›› ስላቸው ባሻዬን፣ ‹‹ይመስለናል እንጂ እውነት በእሱ አምሳያ ተፈጥሮ፣ የእናት ጡት ጠብቶ ያደገ ሥጋ ለባሽ ይኼን ያህል ጭካኔ በራሱ ይካናል? ሰፋ አድርገህ ማየት ነው። በቀል የእኔ ነው ሲል ደግሞ ፈጣሪ አሸባሪን አይጨምርም አላለም፤›› አሉኝ። እንዲህ ሲሉኝ በገዛ እጄ ቆስቁሼ በፈጣሪ ቃል ቀለበት ውስጥ መግባቴ መልሶ አናደደኝ። ‹‹እና አንዳች ዕርምጃ ከሰማይ ቤት እስኪታዘዝ እንለቅ?›› ልላቸው ብዬ በተራቸው እሳቸውን የፍትሕ ቀለበት ውስጥ ከትቼ ከፈጣሪ እንዳላቀያይማቸው ስል ተውኩት። ከምድራውያን የምንቀያየመው አንሶ ደግሞ ከሰማዩ? በየትኛው ጫንቃ!

 በበኩሌ ብዙ አላቂ የተፈጥሮ ሀብቶች አጥንቻለሁ። ተማሪ ቤት ሳለሁ ማለቴ ነው። ሆኖም ጀግንነት ከአላቂ የተፈጥሮ ሀብቶች ጋር እንደሚመደብ ያወቅኩት ሰሞኑን ነው። ምንም እንኳ በወገኔ እስኪደርስ መጠበቅ እንዳልነበረብኝ ዘግይቶ ቢገባኝ። ለካንስ ሜዳሊያ የሚታደልበት የጀግነት ኩርማን አልቆ፣ በደም ጥማት ሥጋ ለባሽ እንደ አውሬ እየታደነ ይፎከራል? አይገርምም ግን? ያደጉበትንና የሮጡበት መስክ በጠላት ሲያዝ ጠላት ገሎ ፉከራ ያባት ነው። ቅጥር በሌለው ሜዳ ለአጥፊነት ብቻ ተማምለው እየተሯሯጡ ቡሃቃ ለመሙላት፣ ሌማት ለማትረፍረፍ የሚሯሯጥ ምስኪንን አድኖ ማረድ የእውነት ምን ይባላል? ‘ኧረ እንጃልኝ ፈራሁ!’ አለ ጀግንነት ሳያንሰው ጊዜ የቀደመው የአገሬ ሰው። እኔማ ሰሞኑን ግራ ግብት ብሎኝ ቅልጥፍና የሚጠይቀው የድለላ ሥራዬ ላይ ተኝቼ ሰነበትኩ። መሰንበት አይበለውና!

 ‹‹አምባሰል ተንዶ ግሸን ገድቦታል፣ የቆመውን ጀግና የተኛው ገሎታል። የቆመውን ጀግና የተኛው መግደሉ፣ ሥፍራ በመያዙ በመደላደሉ፤›› ያለችው አዝማሪ ትዝ ስትለኝ እንዲያው እንደ ዘራፍ ደርሶ እንደ መወራጨት ያደርገኝና ቀልቤን እንደበተንኩ ተነስቼ እብከነከናለሁ። ውዬ ቤት ስገባ ደግሞ ማንጠግቦሽን በከባዱ አስጠንቅቄያለሁ። ቴሌቪዥን ወላ ሬዲዮ የሚባል ነገር እንዳትከፍትብኝ ነዋ። አበጣሪውን ከአጫጁ ምን ይለየዋል? በሉ እስኪ ንገሩኝ? ታዲያ እራት ቀማምሰን ትንሽ እንደቆየን፣ ‹‹ኧረ ቤቱ ሊበላኝ ደረሰ፤›› ትለኛለች። ‹‹ስንት ነፍሰ በላ እያየሽ አገርሽ ያውም ቤትሽ ምን ብሎ ይበላሻል?›› ብዬ እደነፋለሁ። ‹‹ባይሆን ድምፁን ቀነስ አድርጌ ልክፈት?›› ብላ ትለማመጠኛለች። ቤታችን እኩልነት ስለሌለ አይደለም የምትለማመጠኝ። (ደግሞ ነገር እንዳይመጣ ላብራራ እንጂ! አልብራራ፣ አላብራራ እያሉ ነገር በራሳቸው ከሚጠመጥሙት ካልተማርን ከማን እንማር?) የምትለማመጠኝ ክፉኛ ስላዘንኩና ስሜቴ ስለተጎዳ ብቻ ነው። ሌላ ፆታዊም ሆነ ፖለቲካዊ የበላይነት እኛ ቤት እንደሌለ ልታውቁልኝ እወዳለሁ። በስንት ጭቅጭቅ አጩሃም ሆነ ቀንሳ ስትከፍተው ደግሞ ትኩስ አስከሬን  ደግሞ ሌላ ቄራ ፊታችን ድቅን። መጥኔ!

ታዲያላችሁ ዘንድሮ ለተወለደም ለወለደም ክፉኛ እያዘንኩ ነው። ያሳዘነኝ ምኑ መሰላችሁ? ‹‹ክፋት በሰው ልጅ ታሪክ የአንበሳውን ድርሻ እንዳልተጫወተ፣ ጥንትም የሰው ልጅ አገሩን ርስቱን ከማልማት በደም ሲታጠብ ኖሮ ኖሮ ዛሬ ምንድነው እንደ አዲስ የደም ሥር ሕመም የሆነብን?›› ብዬ የባሻዬን ልጅ ስጠይቀው ‹‹ድሮ ‘ፖስት’ ፣ ‘ሼር’፣ ‘ላይክ’፣ ‘ታግ’ የለ። ዛሬ ድርጊቱ ከተፈጸመ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ጀንበር እዚያ ያየችውን አይታ እዚህ ወደ አንተ ሳትዞር ዜናው ኪስህ ውስጥ ይንጣጣል። በዚህ አያያዛችን እኮ ወደፊት ‘የታሪክ ትምህርት’ የሚባል ሳይታጠፍ ይቀራል?›› አለች። እሱ ሲያወራ ብዙ ነገር አሰብኩ። የተበላሸው የመርዶ ወግ ትዝ አለኝ። ‘እንዴት አድርገን ነው አሁን ቤተሰብ የምናረዳው?’ እያላችሁ ተጨንቃችሁ ተጠባችሁ ሰብሰብ ብላችሁ ስትሄዱ ድንኳን ተተክሎ ‘አይ የዘንድሮ ልጅ! ካስማ አብሮ የማይተክል’ ስትባሉ ትደርሳላችሁ። ወላጅ እንዲህ እንደ ቀልድ የልጁን አስከሬን ያያል፡፡ እንደዋዛ፣ ለየዕለት ጉርሱን ሲባዝን የነበረን ሟች ያም ያም በየፌስቡኩ ገጽ ሲለጥፈው አይቶ ባለመደንገጡ ብቻ ሲደነግጥ አውጠነጠንኩ። ከሁሉ በላይ ገና አፍ ሳይፈቱ ከእናት አባት ጠረን ይልቅ የቴክኖሎጂ ቱርፋቶችን አንስተው በመጣል ጡንቻቸውን የሚያፈረጥሙ ሕፃናት ትዝ አሉኝ። ከፍ ሲሉ ባላ ከማስፈንጠር ጀምሮ ‘ኤኬ–47’ እያንጣጡ የአሻንጉሊት አንገት የሚበጥሱባቸው ጌሞች ታወሱኝ። የዘመኑ ታዳጊዎች ክፉኛ አሳሰቡኝ። ሁሉንም አይቼ ባሰብኝ። ያየሁትን እስክነግራችሁ ከፈለጋችሁ እናንተ እየዞራችሁ የማጣራት ሕገ መንግሥታዊ መብታችሁ የተከበረ ነው። መቼስ በትንሽ ትልቁ አትተማመኑ ተብለን ተፈጥረን የለ!

መቼ ‘ለት 150 ካሬ ላይ ያረፈ መጠነኛ ቪላ ላከራይ እቻኮላለሁ። ቤቱን የሚከራዩት ባልና ሚስት ልጃቸውን ይዘው ቤቱን ያጠናሉ። ሰዎቹ ለልጃቸው ከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት ስላላቸው ቤቱን እነሱ ብቻ አይተው ብቻቸውን እንዲወስኑ አልፈለጉም። ደጋግመው ልጁን ‹‹ወደድከው? የትኛውን ክፍል መረጥክ?›› እያሉ ይጠይቃሉ። ልጁ ደብተር የምታህል ነገር ይዞ (በኋላ የባሻዬን ልጅ ስጠይቅ ‘ታብሌት’ ይባላል ብሎኛል። እኛ ታብሌት የምናውቀው የሚዋጥ ክኒን እንጂ እንዲህ በራስ ዓለም የሚያቀዣብር ‘አደንዛዥ ዕፅ’ አልነበረም። ስንትን ያሳየናል ይኼ መድኃኒት አጣሽ ጊዜ) ልጁ ይመልሳል። ‹‹‘ያ! ‘ዋት ‘ኤቬር›› ነው መልሱ። እናትና አባት በልጃቸው መልስ ተከፍተው የውሸት ፈገግታ ሲለግሱኝ ‘ለእኔ ተውት’ አልኩና ወደ ልጁ ጠጋ አልኩ። ‘እንኳን ይህቺን ብላቴና ስንቱን አደራድረናል’ ብዬ ነዋ በእኔ ቤት።

ኋላ ወደ ያዛት ‘ታብሌት’ ጠጋ ብዬ ሳይ የአንድ ወጠምሻ ጥቁር ሰውዬ  ጀርባ ይታየኛል። ያልታጠቀው መሣሪያ የለም። በፈራረሰ ከተማ ውስጥ ይሮጣል። የ‘አርፒጂ’ ናዳ ይወርድበታል። ‘ጌም’ ስልሆነ አይሞትም። (ምነው አንዳንዴስ ‘ጌም’ ቢሆን የእኛ ኑሮ ያሰኛል ብታዩት) ‹‹ፊልም ነው?›› አልኩት። ያልገባኝ ብዙ ነገር አለ። ‹‹ኖ! ይኼ የምታየው ሰውዬ እኔ ነኝ፤›› አለኝ። ቀና ብሎም ሳያየኝ። ‹‹ለምንድነው የምትሮጠው?›› ስለው፣ ‹‹እይ ዝም ብለህ፤›› ቀጭን ተዕዛዝ ደረሰኝ። ተሹሎክሉኮ የሆነ ሥርቻ ውስጥ ተደበቀ። ‘ላውንቸሩን’ አወጣ። ጠላቶቹ ወደመሸጉበት ሕንፃ ተኮሰው። ሕንፃው ፈራረሰ። ‹‹የተረፉትን ደግሞ በአንድ አንድ ጥይት ለመጨረስ፤›› ብሎ እንደነገረኝ ‘ሻት ጋን’ መዘዘ። አናት አናታቸውን ሲመታቸው ደም እንደ ፏፏቴ ይገነፍላል። በአዋቂነት ዘመናችን ከወዳጆቼ ጋር የውኃ ፏፏቴ ለማየት ሸራተን ስንገባ ትዝ አለኝ። ይኼ ልጅ ግን ቢከፍሉት አይደለም ሸራተን ኒያግራ ቢወስዱት ብርቅ እንደማይሆንበት አሰብኩ። ‘ለእኔ ተውት’ ያልኩትን ልጅ ለማግባባት ‘ጌሙ’ ውስጥ ተወክዬ ካልገባሁ እንደማላባብለው ገባኝ። ተራዬን በኃፍረት ፈገግ አልኩ። የሀብታም የድሃ ልጅ ሳይል በየአቅጣጫው፣ በየመልኩ ስናይ እሴቶችን የሚያኮስስ የቴክኖሎጂ ተዋፅኦ ትውልዱን እንደከበበው (በአግባቡና በዕውቀት ለሚጠቀምበት አገልግሎቱ ሳይረሳ አደራ) ስረዳ ደግሞ ይባስ አዋቂዎቹንም ማግባባት አቃተኝ። ኧረ የሚያቅተን በዛ እናንተ!

ሆነም ቀረ ለእኔ ብሎት ቤቱ ተከራየልኝ። አንዳንድ የደንበኞቼ ቁጥሮች ላይ ‘ድብ ድብ’ ተጫውቼ በርከት ያሉ የማሽነሪ ዕቃዎች ገዥ እንደሚፈልጉ መረጃ ደረሰኝ። ስከንፍ አግኛቸው ወደተባልኩት ወይዘሮ ሄድኩ። የዘመናቸውን መግፋት ሳይ ማሽኖቹም በርካታ ዓመታት ያሳለፉ ይሆናሉ ብዬ ሰጋሁ። ዋጋቸው ሲወርድ ‘ኮሚሽኔ’ ስለሚቀንስ እስኪያሳዩኝ ቸኮልኩ። ጥቂት አውርተን በእርጋታ የሚጓዙትን ወይዘሮ ተከትዬ የተንጣለለ የቤታቸው ጓሮ ሜዳ ላይ የቆሙ ጥሬ የኮንስትራክሽን ማሽኖች ሳይ ግን ዓይኔን ማመን አቃተኝ። ‹‹እማማ የሚከራዩ ነው ያሉኝ የሚሸጡ?›› አልኩ ተጠራጥሬ። ነገሩ ገብቷቸው፣ ‹‹ስማ እንጂ›› አሉኝ። ‹‹ይኼ ሁሉ የምታየው ሀብት የእኔ ሳይሆን የልጄ ነው። ‘ነይ አገርሽ ላይ ኢንቨስት አድርጊ ብዬ’ ጨቅጭቄ ጨቅጭቄ መጣች። አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም ‘እዚያ ሂጂ’ ስትባል ‘እዚህ ነይ’ ሲሏት አራት ወራት ከረመች። ‘ይኼን ሁሉ የምትሠሪኝ አንቺ ነሽ ተመልሼ እሄዳለሁ’ ብላ ጓዟን ጠቀለለች። ‘የለም እኔ አብሬሽ እንከራተታለሁ’ ብዬ ስወጣ ስወርድ ዕድሜዬም ነው መሰል አቃተኝ። እየሰማኸኝ ነው? ኬንያ 20 ዓመት ኖሬያለሁ። ሥራ ልትጀምር ፈልገህ ንግድ ፈቃድ ስታወጣ ምን እንደሚጠይቁህ ታውቃለህ? ‘ምን ያህል የሥራ ዕድል ትፈጥራለህ? በዓመቱ ምን ያህል ትጨምራል?’ ነው። ሌላ የቢሮክራሲ ጣጣ አላውቅም። ይኼው ወንድሟንና እኔን ‘ሽጡና ገንዘቤን ባንክ አስገቡ’ ብላ ከሄደች ወር አለፋት፤›› አሉኝ። ‘አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል’ እያልኩ በውስጤ ‹‹በሉ ምርጫ እስኪያልፍ አሁን ለእኔ የነገሩኝን ለማንም አይናገሩ፤›› አልኳቸው። ግመል እንደ መዋጥ ትንኝ እንደ ማጥራት እያደረገኝ። ድንቄም ማስጠንቀቂያ!

በሉ እስኪ እንሰነባባበት። ምንም እንኳ የሚሰማውና የሚታየው የመኖር ትጥቃችንን ሊያስፈታ ቢታገለንም ይህቺን ታህል መተንፈሳችን አልጎዳችንም። እሱም ተራው ደርሶ አትቁም እስኪባል ቋሚ ምን ይሆናል አትሉኝም? አዎ! ተስፋ ሳለ ምን ይሆናል። ባሻዬ ምን ሲሉኝ ነበር መሰላችሁ? ‹‹እሱ ኑር እስካለ ድረስ ብታጣ ብትራቆት ብትታረዝ ምን ማድረግ ትችላለለህ? ‘እሱ የከፈተውን ጉሮሮ ሳይዘጋው አያድርም’ ትላለህ። ዳሩ እሱ የከፈተውን ጉሮሮ አረመኔ ሲቆርጠው ዝም እያለ አስቸገረ። ግን መታገስ ነው። ሃይማኖትህ ምንም ሆነ ምን መሠረቱ ትግሥትና ፍቅር መሆን አለበት። ይኼውልህ ምሳሌ፡፡ አንድ የቆሎ ተማሪ ‘በንተ ስለማርያም’ ይላል ጭራሮ አጥር ጥግ ቆሞ። ውስጥ ያሉ እናት ሰምተው ‘ተሜ አትቁም’ ይሉታል። ‘እመ እኔ መቼ ቆሜ? በእኔ ተመስሎ እኮ ፈጣሪ ነው የቆመ’ ቢላቸው ‘ከምኔው አንተ ዘንድ ደረሰ? አሁን ሌማቴ ባዶ መሆኑን ከፍቼ አሳይቼ ሳልከድነው?’ አሉት። ተሜ ተራውን ‘ነው? እንግዲያስ ልቀመጥ’ ብሎ ተማሪነቱን ተወው ይባላል። የሚለመን ሳይኖር ለምን ልለምን ብሎ እኮ ነው። አይ ተሜ! ‘ከሰነፍ ተማሪ፣ ከገንዘብ ቀርቃሪ፣ ከሸምጣጣ ሱሪ ይሰውርህ’ የሚባለው ይኼኔ ነው። ስንፍና የጥበብና የተግሳፅ ጠላት ናት። አየህ ዓለም በማጣት በማግኘት፣ በመውጣት በመውረድ፣ በሞት በሕይወት ጋጣ ስትከፋፈል ታግሶ ለሰነበተ፣ ቆሞ ለታዘበ፣ ታክቶ ላልተቀመጠ የማስተዋልንና የዕውቀትን ብርሃን ታበራለት ዘንድ ነው። ጅብ ቸኩሎ ምን ነከሰ? ቀንድ አትለኝም? ምንድነው እኔን ብቻ የምታስለፈልፈኝ? አዎ! ሁሉን ታግሰን እኛው በእኛው እዚሁ ተረባርበን ይህቺን ምድር ብናርሳት ታጠግበናለች። ‘ወንድሜ ፊት ነሳኝ’ ብሎ ሰው የአባቱን ርስት ጥሎ ከሄደ ያው ባርነት ያው የባዳ በደል ነው የሚጠብቀው። አፉን የከፈተ ባህር ነው የሚውጠው። አይደለም? መቻል ያሳልፋል። መቻቻል ያሰነብታል። ‘ኢትዮጵያዊም ኢትዮጵያዊነቱን፣ ነብር ዥንጉርጉርነቱን አይቀይርም’ ብሎ ወገብን ጠበቅ ይበጃል። እህ ሌላማ ያልሞከርነው ምን አለ?›› ሲሉኝ ‹‹ምንም!›› ከማለት ውጪ ሌላ መልስ አልመለስኩም። ባሻዬ መልዕክታቸው ግልጽ ነው፡፡ እኛ እርስ በርሳችን ካልተደጋገፍን ማንም አይደርስልንም ነው የሚሉት፡፡ አገራችን ለሁላችንም ትበቃለች፡፡ ነገር ግን በክፉ አንፈላለግ ነው የሚሉት፡፡ በአገር ጉዳይ ትርፍና ኪሳራ አናወራርድ ነው መልዕክቱ! መልካም ሰንበት!             

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት