Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሐዘኑን ዋጥ እናድርግ!

እነሆ መንገድ። ከካዛንቺስ ወደ ቦሌ ድልድይ ልንጓዝ ነው። ጨለማ ከመባረሩ መንፈስ የሚያጨልም፣ ልብ የሚጎት መርዶ እንሰማለን። ‘የዛሬው ይባስ’ እያሰኘ ይሉትን የሚያሳጣ ሐዘን ‘እኮ ለምን ሰላም አድራችሁ’ ይለናል። የሕይወት ጎዳና ብዙ ቢያሳየንም ቅስም አሰባበሩን ልንለምደው አልቻልንም። አፋችን ሳይሟሽ ትናንት የሰማነውን ሳንረሳ፣ ጠባሳችንን ለማሻር በየፊናችን ጉዞ ስንጀምር የሚያስተክዘን በደል አናጣም። የግል እንጉርጉሯችንን ሳንጨርስ በማኅበር ለቅሶ ያስቀምጠናል። ያለፉ ቂም በቀሎች ሳይረሱን ጎዳናው ማቅ ያስለብሰናል። ዕልልታችን ትንሳዔን ከመሸኘቱ እንደ በግ ስንታረድ ዋይታ እንዳያጥረን ይስበናል። የክት ልብሳችን ሳያድፍ ‘ሸንበቆ ላይ ሰቅላችሁ አዙሩኝ’ ይለናል። አወይ ብለን ሳናባራ ለእግዚኦታ ያቻኩለናል። የምህላችን  ሰንሰለት የመንገዳችን መታጠቂያ ይመስላል። በልተን ሳንጠግብ የእፎይታ ጥግ ሳናገኝ በውስጥ በውጭ ስቃያችን እንደ ጭድ እሳት ይቀጣጠላል። በጣር መሽቶ በጣር ከመንጋቱ መርዶ በላይ በላዩ ይግተለተላል። ማርገጃ እስኪጠበን እንባ ያለ ስሜት እስኪፈሰን ጥፋት ሊላመደን ይጎሽመናል።

‹‹አንገቴን ማስገቢያ ጎጆ አቀና ብዬ፣ ሥለት አስላለሁ በሰው አገር ቀዬ፤›› ትላለች ከሹፌሩ ጀርባ የተቀመጠች ተሳፋሪ። ‹‹መንገድ መንገድ ይላል ይህ እግሬ ከርታታው፣ ራስ አልችል ብሎ አንገቴ ለግላጋው›› ብላ ከጎኗ የተቀመጠች ወይዘሮ ታግዛለች። ‹‹ለዓውደ ዓመት ለበዓል በግ አርዳለሁ ብዬ፣ እጄን ሸረከትኩት አንገት ያዥ አጥቼ፤›› እያለ ደግሞ ሦስተኛ ረድፍ ላይ ከጎኔ የተቀመጠ ጎልማሳ ይገባል። ወያላው፣ ‹‹ይኼን ነው መፍራት። ብላችሁ ብላችሁ ድንኳን ታክሲዬ ውስጥ ተከላችሁ?›› እያለ የጨፈገገውን ድባብ ወደተለመደው የስላቅና የምፀት ይዞታው ሊመልስ ይጣጣራል። ጥንትም ግጥም ወትሮም ሙሾ መተንፈሻው የሆነ ኅብረተሰብ ተው ቢባል ይሰማል? እንዲያው ግን የሰው ልጅ በስንቱ ይገኛል?

ጉዟችን ተጀምሯል። የተሳፋሪው ወሬ ተጀምሮ እስኪያልቅ ማለት ይቻላል የጽንፈኛው አረመኔ አይኤስ ቡድን አባላት ኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሱት ጭካኔ የተሞላ የሽብር ድርጊት ሆኗል። ‹‹ወጣ ወጣና እንደ ሸንበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ’ የሚባለው አሁን ነው፤›› ትላለች አንዱ ከመጨረሻ ወንበር። ብራንድ መነጽሯን አሥር ጊዜ እያወለቀችና እየወለወለች። ከጎኗ ያለችው በበኩሏ ያልታዘበቻት መስላ ‘ጉቺ’ መነጽሯን ሰረቅ አድርጋ እያየች፣ ‹‹ማንን ነው?›› ስትል ተለሳልሳ ትጠይቃታለች። ‹‹አጠቃላይ የሰው ልጅ ሥልጣኔ ነዋ! የእጆቹን ሥራ በጭንቅ አምጦ ያገኛቸውን የዕውቀቱን ቱርፋቶች ሁሉ ገደል የሚከት ኢሰብዓዊ ድርጊት ሲታይ ሌላ ምን ትያለሽ ታዲያ?›› በተራዋ ትጠይቃለች።

‹‹ተው አንተ ፈጣሪ ተው!  ወይ ዝናብ ጣልልን ወይ ዝናብ ሆነህ ና!›› መሀል መቀመጫ ነጠላ የተከናነቡ አዛውንት ያጉተመትማሉ። ‹‹ቢያካፋም እሱ፣ ቢዘንብም እሱ፣ ምን ዓይነት ልመና ነው እማማ?›› ሲላቸው ከጎናቸው ‹‹እህ ተቃጠልና ተቃጠልን!›› ብለው እጃቸውን ወደ ሰማይ ይዘረጋሉ። ‹‹ያልወለደ ምኑን ያውቀዋል? ‘አልቅሱ እንላቀስ የባሰው ከባሰው፣ ያልተነካውማ ሳቁም አያደርሰው’ አለች ያቺ ጓዴ፤›› ለጥቂት ጊዜ ጓዴ ወዳሏት ትዝታቸው በሐሳብ ተጓዙ። ቆዝመው ቆዩና፣ ‹‹ስማ ልንገርህ ‘ወለደች አላሉኝ የት ነው ወጋወጉ፣ የተሠራው አልጋ የታረደው በጉ፤ ይቀብሩታል እንጂ ልጅን ተጠንቅቆ፣ አሁን ምን ያደርጋል ልብስ በሸንበቆ’ ማለት ለወላጅ ሁለተኛ ሞት ነው። አዎ! የዛሬ ልጆቼ ሳቅ አታውቁ። ለቅሶ አታውቁ። ሁሉን ልትጨብጡ ሁሉን ልትሆኑ ስትወጡ ስትወርዱ ይኼው በዱር አውሬ የተተካ የሰው አውሬ ይበላችሁ ጀመር። እኛ ምን ሆንን? አርፋችሁ አገራችሁ ቁጭ በሉ በቃ። ምን መርፌ ይሆን ይኼ እላቂ ዘመን መቀመጫችሁ ላይ የተከለው? እንጃ ዘንድሮ›› እያሉ ተንገሸገሹ። ‘ያልወለደ አያውቀውም’ ብለው ስለጀመሩ ይሆን ስለሚያዛክረን መርፌ መተረክ ከተጀመረ መሽቶ ስለሚነጋ ብቻ የሚሞግታቸው ጠፋ። ስንቱን ተሟግተው ይችሉታል ጎበዝ!

‹‹እኔን የሚገርመኝ . . .›› ከአፍታ ዝም ዝም በኋላ መጨረሻ ወንበር ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ተሳፋሪ ከወዳጁ ጋር ይጫወታል። ‹‹የዘንድሮ ልጅ ሲበዛ ፈጣን ነው። ተመልከት እስኪ አሁን ሦስት ዓመት ትመስላለች፤›› የልጁን ፎቶ እያሳየው የጓደኛውን አስተያየት በጉጉት ይጠባበቃል። ‹‹አንተ ቁርጥ እናቷን አይደል እንዴ የምትመስለው? በል ቶሎ ወንድ ልጅ ወልደህ ወገን አደራጅ። ዘንድሮ በተደራጀ ነው፤›› አለው  ወዳጁ። ‹‹ዝም በል አይቀርም፤›› ይፎክራል። ‹‹ሆሆ! አሸባሪዎችንን እንዴት እንበትን እያልን መከራ እያየን፣ ጭራሽ አንድ ቤተሰብ በተመሳሰል ሊወግን ያሴራል? ኧረ ይኼ ዘረኝነት እንዲያው ምን ይሻለዋል?›› ይለኛል ጎልማሳው ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብሎ። ከአዛውንቷ አጠገብ የተቀመጠው ወጣት ሰምቶት ኖሮ፣ ‹‹ሰው ያለ ቡድን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም’ ተብሎ ሳይፈጠር ቀረ ብለህ ነው? እያደር ነገሩን ያከረረው እኮ እንዲህ መሰሉ ነው።

በዓይን፣ በአፍንጫ፣ በጆሮ፣ በቅንድብ የእኔ ነው የእኔ እያሉ አሳድገው ነገ በሃይማኖት፣ በዘርና በአመለካከት እየተቧደነ ትውልድ ሲተራመስ ዕዳው መልሶ አምጦ ለወለደ ይሆናል፡፡ እሳቸው ቅድም ያሉት ማለት ነው፤›› ይላል። ከኋላ ቀጥለዋል። ‹‹ደግሞ እኮ ቴሌቪዥን ስታይ ልክ እንደ ትልቅ ሰው ነው። ቁጭ ካለች በቃ መነቃነቅ የለም፤›› ይላል ዓይኑን በዓይኑ አይቶ ያልጠገበው አባት በስስት። ይኼኔ አዛውንቷ ሰምተው፣ ‹‹ኤድያ! ወልዶ ማሳደግ በእኛ ጊዜ ቀረ። አሁን እስኪ ልጅ አተኩሮ ማጥናትና ማየት ያለበት አካባቢውን እንጂ ቴሌቪዥን ነው? ደግሞስ በዚህ ጣቢያው ሁሉ ደም በደም በሆነበት ጊዜ? አያድርስ እኮ ነው እናንተ!›› ብለው አፋቸውን በነጠላቸው ይሸፍናሉ። እውነት በዘንድሮ አያያዝ ‘ቴሌቪዥን ልጆች የማይደርስበት ቦታ ርቆ ይቀመጥ’ ሳይባል ይቀራል! ማን ያውቃል?

ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላው እያረፈ ሒሳብ ይቀበላል። ለወሬ ያለው ጉጉት ሥራ የሚያሠራው አልሆነም። ‹‹እሺ ሒሳብ” አለ። ከሹፌሩ ጀርባ ሙሾ ሲቀባበሉ የነበሩ ሴቶች ያለ ዛሬ ሳይተዋወቁ፣ ‘እኔ ልክፈል እኔ’ ታክሲዋን በአንድ ጎማዋ አቆሟት። ‹‹ደስ አይልም ይኼ ፍቅርና መተሳሰብ? ምናለበት ግን በስሜትና በሰሞን ባይሆን? ስንሞት ባንተዛዘን? ሳንሰደድ ብንረዳዳ? ምናለ?›› ከአዛውንቷ አጠገብ የተቀመጠው ወጣት ተናገ። ወዲያው ታክሲያችን ቆመች። ‹‹አስገባቸው›› ወያላው ዘሎ ወረደ። ‹‹ቦታ አለህ?›› ተሳቀው ዓይን ዓይናችን የሚያዩን ተሳፋሪዎች በሩን አንቀው ቆመዋል። ‹‹ቦታ አለ?›› ወያላው መልሶ ጠየቃቸው። ‹‹ደግሞ ከዚህ በኋላ ቦታ ሊጠፋ ነው? እስካሁን ቦታ እየጠፋ የጠፋው ነፍስ ይበቃል። ነገ ከአገሬ የተሰደድኩት ታክሲ አጥቼ ነው ልትሉ ነው እንዴ? እስኪ ጠጋ ጠጋ በሉላቸው። መተሳሰብ ከዚህ ይጀምራል። ‘የወገን ፍቅር የሚጀምረው ታክሲ ውስጥ ነው’ ብሎ መንግሥት መግለጫ እስኪሰጥ አትጠብቁ፤›› ወያላው የራሱን መግለጫ አነበበ። የሰውን የልብ ስብራት ትርፍ ማግበስበሻ ሊያደርገው ዓይኑን በጨው አጥቧል።

ጥንድ መቀመጫዎች ላይ የተሰየምን ስንጠጋጋ ሦስቱም ገቡና ታክሲያችን ተንቀሳቀሰች። ወያላው ካቆመበት ሊቀጥል ዘወር ሲል ሴቶቹ እንዳልተስማሙ ያያል። ‹‹ምንድነው ይኼን ያህል? በቃ አንዳችሁ ክፈሉ። ሰው እንኳን የታክሲ ለወደደው የነፍስ ታሪፍ ይከፍላል፤›› አላቸው። ቀደም ቀደም ማለቱ አናዷቸዋል። የቀረበችው እጇን ዘረጋች። ተቀብሎ ወደ እኛ ሲዞር አዛውንቷ ለወጣቱ የሚሉትን ያደምጣል። ‹‹እኛ ለወዳጁ ብቻ የሚሞትም ሆነ የሚኖር አንፈልግም። ለማይወደው፣ ለጠላቱም ዋጋ የሚከፍል፣ ይቅር ባይ፣ ሁሉን በእኩል ዓይን የሚያይ፣ ለዘርና ለፆታ የማያደላ ነው የሚያስፈልገን። አይደል እንዴ? አዎ። ለወደደውማ ማንም ይሰዋል። ለእኩልነት፣ ለሰላምና ለፍትሕ ሲል ለሁሉም መስዋዕት የሚሆን ነው የናፈቀን?›› ብለው ሳይጨርሱ ትን አላቸው። ወዲያው ዘወር ብለው፣ ‹‹ፖለቲካ ተናገርኩ እንዴ?›› ሲሉ ተሳፋሪው ሳቀ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርባናል። ወያላው ሒሳብ ሰብስቦ መልስ ሊያረሳሳ ዳር ዳር ይላል። ‹‹አንተ መልስ አምጣ እንጂ። በዘገየ ማፅናኛና ግራ የሚያጋባ መግለጫ እርር ድብን የምንለው አይበቃም ደሞ አንተ የምትብሰን?›› መንገድ ላይ ከተሰፈሩት አንደኛው ይደነፋል። ድምፁ ውስጥ ስሜታዊነት ይወራጫል። ‹‹ምን ይታወቃል? መልሱ የእኛ ይሁን የሌላ እያጣራ ይሆናላ፤›› መጨረሻ ባለመነጽሯ ታብራራለች። ‹‹ወልደህ እየው ትል ነበር እናቴ። ዛሬ ወልጄ ምን ለማለት እንደፈለገች ገባኝ። መንግሥት ሆነህ እየው ብትለኝ ኖሮ ደግሞ አስቡት። እስኪ በስሜታዊነት ገና ንዴታችን ሳይበርድ ለፍርድ አንቸኩል፤›› አለ የወላጅነት ደስታ ሊገለው የሚቃጣው ተሳፋሪ። ‹‹ምን እናድርግ ወንድሜ? እንዲያው የመልካም አስተዳደር እንከኑን ትተህ፣ ሙሰኛ መሄጃ መድረሻ አሳጥቶን ሃይ ባይ ማጣታችንን ትተህ፣ የፍትሕ መጓደል መፈጠራችንን እንዳስጠላን ዘንግተህ፣ በሰው አገር እንደ ደመራ ስንነድ እንዲያው ዝም እንዲያው ጭጭ ሲሉን ብሶት ይዞን እኮ ነው፤›› ጎልማሳው ተናገረ።

‹‹ምናልባት ሰብሰብ ብለው ከሚጠፉት ነፍሶች ነጠል ብለው የሚጠፉቱ ለዓይን አይሞሉ ይሆናላ? ማነው ቅድም ዘመኑ የመደራጀት ነው ሲል የሰማሁት?›› ብላ ወይዘሮዋ ስታስነካው፣ ‹‹እንዲያ!›› እያለ ወያላው ያዳንቃል። ወዲያው ታክሲያችን ጥጓን ያዘች። ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን ከፈተው። ‹‹የሆነው ሆኖ ለእኛ ከሚታየን ይልቅ ከላይ ላሉት ብዙ የሚታያቸው ይበልጣል። ዛሬ በድንፋታና በእልህ የሚወሰን ውሳኔ ቀንድ ያስነክሳል እንጂ ፋይዳ አይኖረውም። ብልህ አይቸኩልም። ወንዝ ሞላ ተብሎ በባልዲ አይጠለቅም። ምንጩን ማድረቅ ነው። ሰላም ለምድራችን። ፍቅር ለሰው ልጆች!›› እያሉ አዛውንቷ ቀደሙን። ከኋላችን አልፈው መንገዳቸውን ሲያቀኑ ደግሞ፣ ‹‹እስኪ ሐዘናችንን ዋጥ እናድርገው፤›› ሲሉ አንገታችንን እያወዛወዝን ተከተልናቸው። ሐዘኑን ዋጥ እናድርግ! መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት