Wednesday, April 17, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የሕዝብ መረጃ የማግኘት መብት ማተሚያ ቤት ውስጥ አይታገት!

ከጊዜ ወደ ጊዜ ከድጡ ወደ ማጡ እየተንሸራተተ ያለው የማተሚያ ቤት አገልግሎት ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ ነው፡፡ በተለይ የግል ጋዜጦች ለዓመታት ተቆራኝቷቸው ያለው የኅትመት አገልግሎት ችግር፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሚቋቋሙት በላይ እየሆነባቸው ነው፡፡ ለአንባቢያን ወቅታቸውን ጠብቀው መቅረብ ያለባቸው ትኩስ መረጃዎች በኅትመት አገልግሎት ችግር ምክንያት ለዛቸውና ወዘናቸው ተሟጦ ይወጣሉ፡፡ መረጃ የማግኘት መብት ያላቸው ዜጎችም በተገቢው መንገድ እየተስተናገዱ አይደሉም፡፡ በአጠቃላይ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በተለያዩ ምክንያቶች የሚደርሱ የኅትመት መዘግየቶች፣ ከሚመለከተው የመንግሥት አካላት ትኩረት ተነፍጓቸዋል፡፡ ከማኔጅመንቱም ሆነ ከሥራ አመራር ቦርዱ ቁጥጥር በላይ የሆኑም ይመስላሉ፡፡

ጋዜጦችን በማተሚያ ድርጅቱ የሚያሳትሙ አሳታሚ ድርጅቶች ከሚደርስባቸው ኪሳራና እንግልት በላይ እያሳሰበን ያለው፣ ስለአገሩ ተጨባጭ ሁኔታ አማራጭ መረጃ የማግኘት መብት ያለው ሕዝብ ጉዳይ ነው፡፡ የድርጅቶቻቸውን ማስታወቂያዎች ገንዘብ ከፍለው የሚያወጡ ወገኖችም ጉዳይ እንዲሁ፡፡ በዚህ ምክንያት እየደረሰ ያለው ኪሳራ የአገር ሀብትን እየጎዳ ነው፡፡ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የኅትመት አገልግሎት የሚያገኙ አሳታሚዎች በተደጋጋሚ ጊዜያት ከድርጅቱ ማኔጅመንትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በችግሮቹ ዙሪያ ቢወያዩም አዎንታዊ ምላሽ ሊገኝ አልቻለም፡፡ ማተሚያ ድርጅቱ የማስፋፊያ ፕሮጀክት መጀመሩና እያገባደደ መሆኑ ቢነገርም፣ በሥራ ላይ ያሉት ማሽኖቹ በተደጋጋሚ ስለሚሰበሩና ስለሚበላሹ ጋዜጦች ለበርካታ ቀናት ይዘገያሉ፡፡ የያዙዋቸው ትኩስ መረጃዎች ያረጃሉ፡፡ ይበላሻሉ፡፡ ዋጋ ያጣሉ፡፡ ለትንሳዔ በዓል ሰሞን ታትመው ለሕዝቡ መቅረብ የነበረባቸው በርካታ ጋዜጦች ከሦስት ቀናት እስከ ሳምንት በላይ ቆይተው ወጥተዋል፡፡ በዚህ መሀል ግን ሕዝቡ የሚጠብቃቸው ወቅታዊ መረጃዎች ባክነው ቀርተዋል፡፡

በየሳምንቱ የማተሚያ ማሽን በመሰበሩና በተለያዩ ምክንያቶች ጋዜጦች ከሁለትና ከሦስት ቀናት በላይ ይዘገያሉ፡፡ ወቅታዊ መረጃዎችን የያዙ ጋዜጦች ጊዜያቸውን ጠብቀው ባለመውጣታቸው ሕዝቡ በመረጃ እጦት እየተንገላታ ነው፡፡ በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች በሳምንቱ መጨረሻ ሕዝብ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን የሚያነብባቸው አካባቢዎች ጭር እያሉ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጭርታ ሲፈጠርና የግል ጋዜጦች በጊዜያቸው አልደረሱም ሲባል ለምን ብሎ የሚጠይቅ አካል የለም፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት ወይም የፕሬስ ነፃነት በሕገ መንግሥቱ ዋስትና ባገኘበት አገር ውስጥ፣ ሕዝቡ አማራጭ መረጃዎችን በተለያዩ ምክንያቶች በተደጋጋሚ ሲነፈግ ለምን ተብሎ አይጠየቅም? ችግሩን ቀረብ ብሎ በማየት መፍትሔ ለምን አይፈለግም? ችግሩ የጋዜጣ አሳታሚ ድርጅቶች፣ የጋዜጠኞች ወይም በሚዲያው ዙሪያ ያሉ አካላት ብቻ ነው ተብሎ ከታሰበ በጣም ስህተት ነው፡፡ ይህ ችግር በሕዝብ መረጃ የማግኘት መብት ላይ የተጋረጠ አደጋ ነው፡፡ በምክንያት እናስረዳለን፡፡

አንድ አገር ከፀረ ዴሞክራሲያዊ  አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ስትሸጋገር አስፈላጊ ከሆኑ ቁልፍ ግብዓቶች ውስጥ አንዱ የፕሬስ ነፃነት ነው፡፡ ይህ የፕሬስ ነፃነት የሚያስፈልገው ደግሞ ሕግ አውጭው፣ ተርጓሚውና አስፈጻሚው ተግባራቸውን እየተናበቡ መፈጸማቸውን መከታተል ነው፡፡ ችግር ሲኖር ደግሞ  በመረጃ ላይ ተመሥርቶ ያጋልጣል፡፡ ሦስቱ የመንግሥት አካላትን የእርስ በርስ መስተጋብር የሚከታተለው ፕሬስ በሠለጠኑ አገሮች ‹‹አራተኛው መንግሥት›› ይባላል፡፡ ዝነኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቶማስ ጀፈርሰን፣ ‹‹ጋዜጣ ከሌለው መንግሥት ይልቅ፣ መንግሥት የሌለው ጋዜጣ እመርጣለሁ፤›› ያለው በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ሚዲያው የሚኖረውን ተተኪ የሌለው ሚና ለማሳየት ነው፡፡ ሕዝቡ ከፕሬሱ ጋር ቁርኝት የፈጠረው ደግሞ አገሩ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንድታድግና እንድትበለጽግ ስለሚፈልግ ነው፡፡

በአገራችን ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና የተሰጠው የፕሬስ ነፃነት ደልቶት ኖሮ አያውቅም፡፡ በበርካታ ችግሮች በመተብተቡ ምክንያት ሁሌም አበሳ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ይህ እውነት መሆኑን የሚያሳየን ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኅትመት ውጤቶች አደባባይ የሚወጡበት ወቅት አልፎ አሁን በጣት የሚቆጠሩ ቀርተዋል፡፡ እነሱም ምንም ያህል የሙያ ሥነ ምግባሩን ጠብቀው ቢሠሩም ፈተናው አብሯቸው አለ፡፡ አሁን በጣም እየከበደ የመጣው ፈተና በማተሚያ ቤት እየተፈጠረ ያለው መጓተት ነው፡፡ ጋዜጦች ወቅታዊ መረጃዎችን ይዘው መውጣት ሲገባቸው እንደዋለና እንዳደረ እህል እጅ እጅ እያሉ ነው፡፡ ለትንሣዔ በዓል መውጣት ሲገባቸው እስከ ዳግማዊ ትንሣዔ መዘግየታቸው ይህንን እውነታ ያስረዳል፡፡ የመንግሥት ዝምታ ምን ይባላል? በጣም አነጋጋሪ ነው፡፡

በዚህ ባለንበት ዘመን የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብም ሆነ የአገሪቱን ገጽታ ለማስተዋወቅ በሚደረግ ጥረት፣ በተለይ የግሉ ፕሬስ ጤንነት ትኩረት ካልተሰጠው ችግር አለ፡፡ ፕሬሱ በዓመት ለኅትመት ከሚያወጣው ወጪና ለመንግሥት ከሚከፍለው ታክስ በተጨማሪ፣ ለሕዝብ ትክክለኛና ሚዛኑን የጠበቀ መረጃ ማቅረቡና የሕዝቡ እርካታ ይለካል፡፡ አገሪቱ በዘመኑ አስተሳሰቦች እየተመራች ነው ወይ ለሚለውም ማሳያ ነው፡፡

ያለንበት ወቅት ምርጫ የሚካሄድበት ነው፡፡ ምርጫው አንድ ወር ያህል እየቀረው ነው፡፡ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጊዜ ሰሌዳው መሠረት የምርጫ ክርክርና ቅስቀሳ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ፕሬሱም ምርጫውን የሚመለከቱ ማናቸውንም ጉዳዮች በተመለከተ ለአንባቢያን ወቅታዊ መረጃ ማቅረብ አለበት፡፡ ምርጫው ‹‹ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ›› ይሆናል ሲባል ሁሉም ሚዲያዎች ያለ አድልኦ በእኩልነት ሲዘግቡ ጭምር ነው፡፡ ምርጫ መሀል ተሁኖ አንድ ጋዜጣ ከሳምንት በላይ ማተሚያ ቤት ታስሮ ሲቀመጥ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ብቻ ሳይሆን፣ ለዕለት ተዕለት የዜጎች ሕይወት ጭምር አይመችም፡፡ ትኩስና ወቅታዊ መረጃ የሚፈልጉ
ዜጎች ይገለላሉ፡፡ በምርጫው ሒደት ተበድለናል የሚሉ ወገኖች ይጎዳሉ፡፡ መረጃ በሚፈለገው ደረጃ ወቅታዊ ሆኖ ካልተላለፈ እንደሌለ ይቆጠራል፡፡ መንግሥት ይህ ካላሳሰበው ምን ያሳስበዋል?

አገሪቱ እያስመዘገበች ባለችው የኢኮኖሚ ዕድገትና የመሠረተ ልማት ግንባታዎች መስፋፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟ በአዎንታዊ እየተነሳ ነው፡፡ በአንድ ወቅት በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ችግሮች የሚያብጠለጥሏትም እየለዘቡ ይመስላል፡፡ ይህ በበጎ የሚወሳ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ችግሮቹ በሒደት እንደሚቀረፉ ተስፋ ማሳየት የመንግሥት ድርሻ መሆን አለበት፡፡ ይህ ተስፋ ከሚያካልላቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የፕሬስ ነፃነት ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እንቅፋት እንዳይገጥመው ደግሞ መንግሥት ተደራቢ ኃላፊነት አለበት፡፡ የአገሪቱ ገጽታ ‹‹ግማሽ ጎፈሬ ግማሽ ልጩ›› ሆኖ መታየቱ ተገቢ ባለመሆኑ፣ የአገሪቱን መልካም ገጽታ የሚያጎድፈው የፕሬስ ነፃነት ፈተና ችላ ባይባል ይመረጣል፡፡ መንግሥት ትኩረት ይስጠው፡፡

‹‹ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው›› ተብሎ በመንግሥት ዘወትር ይነገራል፡፡ ይህ ዓቢይ ጉዳይ በንድፈ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባር መታየት ካልቻለ ትርጉም የለውም፡፡ ለሕዝባችን ዴሞክራሲም ሆነ ሰብዓዊ መብት ከመሠረታዊ የሰው ልጆች ፍላጎቶች እኩል ይፈለጋሉ፡፡ እንደ አየር፣ ፀሐይና ውኃ አንገብጋቢ ናቸው፡፡ የሕዝቡ መረጃ የማግኘት መብት እንዲከበር እንቅፋቶች ይወገዱ፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ውስጥ እየገዘፈ የመጣው የኅትመት አገልግሎት ችግር መንግሥትን ያሳስበው፡፡ በምን ቸገረኝ ችላ ያሉ ባለሥልጣናትም ሕዝብን ያስቡ፡፡ ‹‹ጋዜጣ የሌለው መንግሥት እርባና ቢስ ነው›› የሚለውን አባባል ይቀበሉ፡፡ ስለዚህም የሕዝብ መረጃ የማግኘት መብት ማተሚያ ቤት ውስጥ አይታገት!    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...