ሲና ተስፋዬ የተባለች የ29 ዓመት ወጣት ሚያዝያ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ማምሻውን በሸራተን አዲስ ሆቴል መዝናኛ ሥፍራ፣ በመዋኘት ላይ እያለች ሕይወቷ ማለፉ ታወቀ፡፡
ወጣቷ ከሴት ጓደኛዋ ጋር ሆና ወደ መዝናኛ ሥፍራው ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት አካባቢ ከሄደች በኋላ፣ በመዋኘት ላይ እያሉ በመዋኛ ገንዳው ውስጥ ጠለቅ ወጣ እያለች ሙዚቃ ስትሰማ እንደነበር ጓደኛዋ ለሪፖርተር ተናግራለች፡፡ ጓደኛዋም ሙዚቃውን እንድትሰማ ደጋግማ እየጠየቀቻች እያለ ድምጿን አጥፍታ በደረቷ ተዘርግታ ስታያት፣ ተጠግታ ለማናገር ስትሞክር ምላሽ ማጣቷን ገልጻለች፡፡
እየገፋች ወደ ዳር ካደረሰቻት በኋላ ሁኔታዋን ስትመለከት ራሷን መሳቷን እንዳወቀች የገለጸችው ጓደኛዋ፣ ባሰማችው ከፍተኛ የድረሱልኝ ጩኸት ይዋኙ የነበሩ ሌሎች ሰዎችና የሆቴሉ ተጠቃሚዎች ደርሰው፣ ወደ ላንድማርክ ሆስፒታል በአምቡላንስ እንዳደረሷት ተናግራለች፡፡ ሲና ግን ሆስፒታል ስትደርስ ሕይወቷ ማለፉን የሆስፒታሉ ሠራተኞች እንዳረዷቸውም ጓደኛዋ ገልጻለች፡፡
ወደ ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል የተላከው የሟች ወጣት ሲና ተስፋዬ አስከሬን ሚያዝያ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ለቤተሰቦቿ ተሰጥቷል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ግን የአስከሬን ምርመራ ውጤት እየተጠበቀ ሲሆን፣ የወጣቷ ሕይወት ሊያልፍ የቻለበት ምክንያት በውል አልታወቀም፡፡ ለቤተሰቦቿ የመጀመርያ ልጅ የሆነችው ሲና፣ ፋርማሲስት ስትሆን በግል ድርጅት ውስጥ ትሠራ እንደነበር ታውቋል፡፡ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ዓርብ ሌሊት ድረስ የቀብር ሥርዓቷ ሚያዝያ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ይፈጸማል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡