Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

እንቆቅልሽ የሆነው የወተት ምርት

 ኢትዮጵያ በቀንድ ከብቶች ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚውን ሥፍራ፣ በዓለም ከ10 አገሮች መካከል አንዷ ብትሆንም ከወተት ሀብቷ ማግኘት የሚገባትን ያህል ጥቅም እያገኘች ስላለመሆኗ ይወሳል፡፡ በሌላ በኩልም ሌላው ዓለም ባለው የእንስሳት ቁጥር ልክ ወተትን በየገበታው በተለያየ መልኩ ሲጠቀም እንደሚታይ በኢትዮጵያ ግን ባሉት እንስሳት ልክ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ አለመሆኑ ይነገራል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ዓመታዊ የወተት ምርት ከአራት ሚሊዮን ሊትር የዘለለ አይደለም፡፡ ባንድ ወቅት የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው፣ በኢትዮጵያ ለአንድ ሰው በዓመት በአማካይ የሚደርሰው የወተት መጠን 19 ሊትር ብቻ ሲሆን በጎረቤት ኬንያ ከ100 ሊትር በላይ ነው፡፡ ከምክንያቱም አንዱ ያሉትን የወተት ላሞች እንደብዛታቸው ወተት የሚሰጡ ባለመሆናቸው ነው፡፡ የወተት ኢንዱስትሪው በሚጠበቀው ደረጃ ዕድገት ባለማሳየቱና ግብይቱም ጤናማ ባለመሆኑ ወተት አቅራቢዎችና አቀናባሪዎች የሚተዳደሩበት ‹‹የጥሬ ወተት ግብይት ረቂቅ የመግባቢያ ሰነድ›› በቅርቡ በኢንስቲትዩቱ መዘጋጀቱ ይታወቃል፡፡ በአገሪቱ ባለው የወተት ምርትና አቅርቦት እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ፣ በዘርፉ ከተሰማሩት የግል ተቋማት አንዱ የሆነው የኤሌምቱ ኢንትግሬትድ ወተት ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ በላቸው ሁሪሳ ዳዲን ታምራት ጌታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የወተት ምርት ምን ይመስላል?

አቶ በላቸው፡- በመጀመርያ ደረጃ ወተት ማለት ሙሉ ምግቦችን ያካተተ ነው፡፡ አንድ ሕፃን ተወልዶ ከአየር ቀጥሎ የሕይወቱ ቀጣይነት የሚረጋገጠው ከእናቱ ወይም በሌላ መንገድ በሚያገኘው ወተት ነው፡፡ ይህ ለሰው ልጅ ወሳኝ የሆነን ምርት አገራችን በጣም በዝቅተኛ መጠን ታመርታለች፡፡ በአገሪቱ በአሁኑ ሰዓት ቀንድ ያላቸው የዳልጋ ከብቶች 57 ሚሊዮን፣ በግና ፍየል ከ60 ሚሊዮን በላይ፣ ግመሎች ትክክለኛው ቁጥር ባይታወቅም ከ2.5 ሚሊዮን በላይ እንዳሉን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እንግዲህ ሰዎች የሚጠቀሙት በብዛት የላምን ሲሆን በተወሰኑ ቆላማ አካባቢዎች የግመልን፣ በጥቂት አካባቢዎች ደግሞ የበግና የፍየልን የወተት ምርትን ይጠቀማሉ፡፡ የላም ወተት ምርትን የሚሰጡት ካሉን የዳልጋ ከብቶች ውስጥ 10.4 ሚሊዮን ናቸው፡፡ ከውጭ በማዳቀል ወተት የሚሰጡ ላሞች ደግሞ 1.6 ሚሊዮን ናቸው፡፡ የአገራችን ላሞች በተፈጥሮ ወተት የማምረት አቅማቸው በጣም ደካማ በመሆኑ በአንድ አለባ ወቅት የሚገኘው ከ1 እስከ 5 ሊትር ብቻ ነው፡፡ ከውጪዎቹ ደግሞ ከ40 እስከ 60 ሊትር ይገኛል፡፡ ስለዚህ በዓመት ከአራት ቢሊዮን ሊትር በላይ አይመረትም፡፡ ይህ ደግሞ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይኖርበታል ተብሎ በሚገመት አገር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ እንደውም ወተት አይመረትም ማለቱ ይቀላል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀንድ ከብት ብዛት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም አሥረኛ እየተባለች እንደምትጠራ  ይታወቃል፡፡ የከብት ሥጋ አቅርቦት ችግር አለ፡፡ የወተት ምርት ደግሞ የለም እያሉን ነው ይህ አይጋጭም?

አቶ በላቸው፡- በአገራችን እንስሳት የሚረቡት፣ ለእርሻ፣ ለትራንስፖርት በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ እንደ ገንዘብና ሀብት መለኪያ በመሆን ነው፡፡ አንድ ገበሬ ላም የሚያረባው ለወተት ብሎ አይደለም፡፡ ለእርሻው በሬ እንድትወልድለት ነው፡፡ ፈረስ የሚረባው ለንግድ አይደለም ለትራንስፖርት ነው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ግመልና የቀንድ ከብቶች እንዲሁም በግና ፍየል በብዛት ለዝና፣ ትንሽ ትንሽ ደግሞ የሚሰጡትን ወተት ለመጠቀም ሲባል በሰዎች እጅ ላይ ይቀራሉ፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እንስሳት ሁለገብ አገልግሎት ስለሚሰጡ ለገበያ ባለመዋላቸው ቁጥሩ እንዳለ ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወተት እስከዛሬ እንደ ልብ እንዳይመረት ያደረገው ችግሩ ምንድነው?

አቶ በላቸው፡- ችግሩ በርካታ ነው፡፡ ዋነኛውና መሠረታዊ ችግሩ ግን ወተት ተመጋቢዎች አለመሆናችን ነው፡፡ እንደውም አሁን አሁን የቅንጦት ምግብ እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህ ባለመሆኑ ምርቱ ላይ ትኩረት አይሰጥም፡፡ የሚመረተውም ቢሆን የእኛ ላሞች በተፈጥሯቸው ወተት የመስጠት አቅማቸው ደካማ ስለሆነ የውጭ ላም የምትሰጠውን ያህል ከኛ ለማግኘት 40 ላም ያስፈልገናል፡፡ ሌላው እነዚህን ያሉንን ላሞች በትክክል አንይዛቸውም፣ ሜዳ ለቀን በራሳቸው ያገኟትን ለቃቅመው ነው የሚመገቡት፣ ሕክምና የላቸውም፣ መኖ፣ መጠለያ በአግባቡ ባለማግኘታቸው በችግር ነው ምርቱን የሚሰጡት፡፡ እንስሳቱም የሚረቡት እንደተገለጸው ለወተት የሚሆኑ ላሞች ተብለው ከውጭ በማዳቀል የሚረቡ አይደሉም፡፡ ትልቁን ሚና የሚጫወተው ደግሞ መንግሥት ነው በቅርቡ እንስሳትን የተመለከተ ከአረባብና ከሚሰጡት ምርት አጠቃቀምን ጨምሮ በርካታ ነገሮችን የያዘ አዋጅ አፅድቋል፡፡ ምን አልባት ይህ ተግባራዊ ከሆነ ሊስተካከል ይችል እንደሆነ እንጂ እስከዛሬ በወተት አመራረት ዙሪያ ምንም የተሠራ ነገር ባለመኖሩ ዕድገት ሊያመጣ አልቻለም፡፡

ሪፖርተር፡- የወተት ምርት ጥራቱና የገበያውስ ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ በላቸው፡- ይህ ችግር በተለይ በከተማው በስፋት ይታያል፡፡ ምክንያቱም አርቢ ስላልሆነ 80 በመቶ የሚሆነው የሚያመርተው የገጠሩ ሕዝብ ነው፡፡ እንግዲህ ገበያውን በሁለት መንገድ ባህላዊና ዘመናዊ ብለን ልናየው እንችላለን፡፡ በዚህም ግብይት ቢሆን 70 ከመቶው የሚሆነው ምርት ከሚመረትበት አካባቢ ወይም የአገራችን አቀማመጥ አስቸጋሪነት የመሠረተ ልማት ችግር የምርቱ አናሳ መሆን ተደማምሮ በንጹሕ ወተትነት ወደ ገበያ አይገባም፡፡ ገበሬው ይህን ምርት ለራሱ ይጠቀመዋል፣ ወይ ረዥም ጊዜ እንዲቆይለት ወደ ቅቤ፣ አይብ በመቀየር ያስቀምጠዋል፡፡ ቀሪው 30 በመቶው ደግሞ ወደ ገበያ ይመጣል፡፡ ይህ ደግሞ 95 በመቶው ንግዱ የሚከናወነው በባህላዊ መንገድ ነው፡፡ ይህ ማለት በከተማ ውስጥ የሚኖሩ ወተት አርቢዎች ለራሳቸው በመጠቀም፣ የተረፈውን ለጎረቤት ወይም ለካፌና ለሆቴሎች በባህላዊ ዘዴ የሚሠራጭ ነው፡፡ ባለበት ቁጥጥሩ ባለበት የሚካሄድ አይደለም፡፡ ሌላው ዘመናዊ ንግድ የምንለው ከአምስት በመቶ የማይበልጠው በፋብሪካዎች የሚደረገው ንግድ ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከሁለት በመቶ አይበልጥም፡፡ ይህን ስንመለከት በአገራችን የወተት ምርት ገበያ የዳበረ ወይም የሠለጠነ አለመሆኑን እናያለን፡፡ ያለውን 30 በመቶ የሆነውን ምርት ብቻ እንኳን ወደ ዘመናዊ ገበያ ብናመጣው በወተት ገበያው ላይ ትልቅ ለውጥ ይመጣል፡፡ ሁሉንም ተጠቃሚ ማድረግ ያስችላል፡፡ ይህም ባለመደረጉ በዓመት እስከ አራት ሚሊዮን ዶላር በማውጣት የውጭ ወተት ይገባል፡፡ ሌላው ዓለም ባላቸው የእንስሳት ቁጥር ልክ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ሁልጊዜም ከገበታቸው በተለያየ ሁኔታ ይቅረብ እንጂ ወተትን ይጠቀማሉ፡፡ በዚህም ንግዱ በስፋት ይካሄዳል፣ ወደ አገራችን ስንመጣ ግን ተቃራኒ ነው እንስሳት እያሉን ተጠቃሚዎች አይደለንም፡፡ በዚህ ምክንያት ዛሬ ዩኒቨርሲቲ ጨርሶ የሚወጣ ወጣት ቅጭጭ ብሎ ነው የምናየው፤ ገበያ ላይ እንደልብ ባለመኖሩ የቅንጦት እየሆነበት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የቀነጨረ ማኅበረሰብ ነው የሚፈጠረው፡፡ ለምሳሌ በአገራችን ወተትን አምርተው የሚጠቀሙ ማኅበረሰቦችን ብናይ ቦረና አካባቢ ወደ ምሥራቁ ክፍል ሶማሌ ክልል የሚወለዱ ልጆች፣ ረዥምና አጥንተ ሰፋፊ ናቸው፡፡ እነዚህ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ዋና ምግባቸው ወተት ነው፡፡ ሌላው ተደራቢ በመሆኑ ጠንካራና ጤነኛ ማኅበረሰብን ነው የሚፈጥሩት፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ያለው የወተት ምርት በጣም እንቆቅልሽ ነው፡፡ ምርቱ የለም፣ ያለውም ገበያ አይወጣም፡፡ ገበሬው ደግሞ ገበያ የለም ይላል፡፡ ምክንያቱም ወተትን እንዲመገብ የሚያስተባብር የሚያስተምር ባለመኖሩ ወተት ማዕዳችን ውስጥ የለም፡፡ እኛ የምንጠቀመው ለቅቤ ወጥ ለመቀላቀል፣ አይብ በሽሮ መብላት እንድንችል፣ ለበዓል ብቻ ጠብቀን በዶሮ እንመገበዋለን፡፡ ወተት በብዛት የምንጠቀመው በቡና ነው፡፡ ይህ ደግሞ ወተት መጠጣት አይደለም፡፡ በኪራይ መልክ እንኳን ብናገኝ ለልጆች እስከተወሰነ ዕድሜያቸው ብቻ ነው የምንጠቀመው፡፡ ሌላው በብዛት በአገራችን በደጋው አካባቢ በዓመት ውስጥ ከ200 በላይ የጾም ቀኖች አሉ፡፡ በእነዚህና በሌሎች ምክንያት ገበያው ሊስፋፋ አልቻለም፡፡

ሪፖርተር፡- እንስሳቱ በየጊዜው በሚከሰተው ድርቅና በሽታ እያለቁ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውሰጥ ደግሞ ወተትን የሚሰጡ ይገኙበታል፡፡ በእነዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

አቶ በላቸው፡- ይህ እውነት ነው፤ እንስሳትን ብቻ ሳይሆን ዘራቸውንም እያጣን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የመንግሥት ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ የተረፉትን በማቆያ በማገገም ዘራቸው እንዲቀጥል ማስቻል አለበት፡፡ በዚህ ላይ እስካሁን የተሠራ ነገር አላየሁም፡፡ ብዙም ያጣን ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ዘርፍ ያለውን ችግር ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ በላቸው፡- ችግሩ ሲንከባለል ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ግን መንግሥት ያወጣው አዋጅ ከተተገበረ መፍትሔ ያመጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡ አንድ እንስሳ እንዴት መርባት አለበት? ጤናውን እንዴት መጠበቅ አለበት፣ መኖርያው እንዴት ነው? ንግዱስ እንዴት መካሄድ አለበት ለሚለው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በጠቅላላው የእንስሳት አረባብና አደቃቀል ሕግ ስለወጣ ይህ ከተተገበረ ለውጥ ይመጣል፡፡ ሌላው በሚዲያዎች የወተትን ጥቅም በማስተማር ዘርፉን ማሻሻል ይቻላል፡፡ እኛ የውጭን ምርት ባስተዋወቅን ቁጥር የእኛን ገበሬ እየገደልነው መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡ በተለይ በወተት ምርት ማስተዋወቂያ ሥራ ላይ የተሰማሩ ወደ አገራቸውም መለስ ብለው ቢያዩ ሌላው ለውጥ አምጪ መንገድ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ለጉራጌ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደሚታገል የሚናገረው አዲሱ...

‹‹ኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ ውጫዊ ጫናዎችን ለመቀልበስ የፖሊሲ ሪፎርሞች ያስፈልጋሉ›› ዓለም ባንክ

በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ፣ በኢትዮጵያ ውጫዊ...