Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

የፋሲካ በዓል

ትኩስ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ መድፍ እና በግሪክ ሮኬት የታጀበው የፋሲካ በዓል

ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ መሠረት እንዲሁም በዓለም ዙርያ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስ ከ2,000 ዓመታት በፊት የተነሣበትን የፋሲካ በዓል ባለፈው እሑድ (ሚያዝያ 4 ቀን 2007 ዓ.ም.) አክብረዋል፡፡ የሮም ካቶሊክና ፕሮቴስታንቶች ከሳምንት በፊት (መጋቢት 27 ቀን) በግሪጎሪያን ካሌንደር መሠረት ሲያከብሩ፣ ምሥራቆቹ ኦርቶዶክሳውያን ደግሞ ከሳምንት በኋላ ያከበሩት በሚጠቀሙበት ጥንታዊው የጁሊያን ካሌንደር መሠረት ነው፡፡  በኢትዮጵያ፣ በኤርትራና በግብፅ ኮፕቲክ ክርስቲያኖች እኩለ ሌሊት ላይ በቅዳሴ፣ በጧፍ ብርሃንና በመጸለይ ሲያከብሩ፣ በሩሲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭና ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሞስኮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በመገኘት የቅዳሴው ተካፋይ ሆነዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ የትንሣኤው ብሥራት ዘጠኝ ጊዜ መድፍ ሲተኮስ በግሪኳ ምሥራቃዊ ኤጌያን ደሴት ኮበሌዎች በባህላዊ አከባበራቸው ትውፊት መሠረት ሰው ሠራሽ ሮኬት ሌሊቱን ተኩሰዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ምዕመናን ጨምሮ በርካቶች በኢየሩሳሌም በቅዱሱ መቃብር በመገኘት በግሪኩ ጳጳስ የተለኮሰውን የትንሣኤው ብርሃን በመቀባበልና በመዝሙር ማክበራቸው ተዘግቧል፡፡

 

*****

አንችዬ የኔ ነሽ

ከቶ ግድ የለኝም

አያሳስበኝም

የሆነው ቢሆን

…ሁሉም

ሌላው ሁሉም፣

              ባይጣፍጥ ባይጥም፤

ፍሬሽ ቢሆንብኝ

እጅግ አማሳኝ

መቼ ግድ አለኝ?

ላንቺ እንጂ መድከሜ

መድቀቅ መታመሜ

ምኔም መባዘኔ

ፍስሐዬ ለኔ፡፡

እንደዓይኔ…እንደጣቴ

እንደው እንደፍጥረቴ

ተቀብዬሻለሁ በሰራ አካላቴ፡፡

አንችዬ የኔ ነሽ

እኔም የምንግዜሽ

ዕድሌ የሰጠኝ

ዕጣሽ የለገሰሽ፡፡

1961

  • ደበበ ሰይፉ ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ›› (1992)

*****

‹‹ሁሉም መሬት ሆነዋል››

ልጄ ሆይ ከኃይለኛና ከነገረኛ ሰው ጋር አትጣላ፡፡ ከነገረኛና ከኃይለኛ ሰው ጋር መጣላት በሚነድ እሳት ላይ ገለባ እንደ መጨመር ነውና ተጠንቀቅ፡፡

ልጄ ሆይ፤ ለጌታህ ገንዘብ አታበድር፡፡ ክፈለኝ ባልኸው ጊዜ አንተ የምትጠፋበትን ምክንያት ይፈልጋልና፡፡

ለተሟጋችም አታበድር፡፡ ክፈለኝ ባልኸው ጊዜ ነገር ፈልጎ ወደ ዳኛ ይወስድሃልና፡፡ ልጄ ሆይ፤ ጠላት በዛብኝ፤ ምቀኛ አሴረብኝ ብለህ እጅግ አትጨነቅ፡ በዓለም የሚኖር ፍጥረት ሁሉ ጠላትና ምቀኛ አለበት እንደ ባንተ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚሁም በጥቂቱ እጽፍልሃለሁ፡፡ በፍየል ነብር፤ በበግ ተኩላ፤ ባህያ ጅብ፤ በላም አንበሳ፤ በዓይጥ ድመት፤ በዶሮ ጭልፊት አለባቸው፡፡ ይህንንም የመሰለ ብዙ አለ፡፡ ሰውም እርስ በርሱ እንዴሁ ነው፡፡

ስለዚህ የመጣብህን ነገር ሁሉ በትዕግስት ሆነህ ተቀበለው፡፡ በመጨረሻው ግን ሁሉ አላፊ ነውና ጠላቶችህ ሁሉ ያልፋሉ፡፡ ወይም አንተ አስቀድመህ ታልፍና ከዚህ ዓለም መከራና ጭንቀት ታርፋለህ፡፡

ልጄ ሆይ፤ እስቲ ያለፉትን ሰዎች ሁሉ አስባቸው፡፡ እነዚያ ሁሉ ጀግኖች ሁሉም መሬት ሆነዋል፡፡

እነዚያ ሁሉ ዓለመኞች፤ እነዚያ ሁሉ ቀልደኞችና ፌዘኞች እነዚያ ሁሉ ግፈኞች፤ እነዚያ ሁሉ በድሃ ላይ የሚስቁና የሚሳለቁ ሁሉም መሬት ሆነዋል፡፡

እነዚያ ሁሉ ድሆች ሲበደሉ፣ ሲያዝኑ፣ ሲያለቅሱ ካንዱ ሀገር ወደ ሌላው ሀገር ሲሰደዱ፣ ሲራቡ፣ ሲጠሙ፣ ሲታረዙ የነበሩ መሬት ሆነዋል፡፡

ስንት ሰዎች የነበሩ ይመስልሃል፡፡ የድሃ እንባ ሲፈስ የወንዝ ውኃ የሚፈስ የሚመስላቸው ስንት ሰዎች ነበሩ፡፡

ድሃ ታስሮ ወይም በሌላ ጭንቅ ነገር ተይዞ ሲሞት የወፍ ግልገል የሚሞት የሚመስላቸው ስንት ሰዎች ነበሩ፡፡

ጉልበት ካለን ብለው በደካሞች ላይ ያሰቡትን ሁሉ የሚሠሩ ስንት ሰዎች ነበሩ፡፡ ሰውን ለማጥፋት እጅግ የሚጥሩ ሰውን ካላጠፉ እንቅልፍ የማይወስዳቸው ስንት ሰዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀድሞ የነበሩትን ሁሉም መሬት ሆነዋል፡፡ ከመሬት የተገኘ ሁሉ መሬት ስለ ሆነ ወደ መሬትም የማይመለስ ስለሌለ እኛም ነገ እንደነዚያው እንሆናለን፡፡ ስለዚህ በማናቸውም ምክንያት ቢሆን፤ የሰው ደስታውና አዘኑ እጅግ አጭር መሆኑን በጣም እወቀው፡፡

  • ኅሩይ ወልደሥላሴ ‹‹ለልጀ ምክር ለአባት መታሰቢያ›› (2001)

*****

ይህች ምራቅ ሳትደርቅ

‹‹ና! የእኔ ፉንጋ! ዓረብ ቤት ትሄድና የአራት ፍራንክ ዘይት፣ የሁለት ፍራንክ ጨው፣ አራት ፍራንክ መልስ አለው፡፡ እንካ ስሙኒውን፡፡ ስትመለስ የማደርግልህን አታውቅም! ብርር በል ቱፍ! (ምራቃቸውን እየተፉ) ይህች ምራቅ ሳትደርቅ ከተፍ በል አሉ እማማ ረታሽ፡፡

‹‹እሺ፡፡››

‹‹ቆይ አትንከውከው፤ ምንድነው ግዛ ያልኩህ?››

‹‹የአራት ፍራንክ ዘይት፣ የአራት ፍራንክ ስኳር!››

‹‹ይኸው! አላልኩም፡፡ ይሄ ልበቢስ! ስኳር መቃምዋ ሱስ ሆናብሃለች ማለት ነው? ልብ በልና አድምጠኝ!…›› ብለው ያርሙኛል፡፡ ከአፋቸው ነጥቄ ‹‹የአራት ፍራንክ ጨው፡፡››

‹‹ኧረ እኔ አልወጣኝም!›› የአራት ፍራንክ ጨው ምን ላደርግበት ነው? ድግስ የለብኝ!›› ብለው እማማ ረታሽ አረሙኝ፡፡

እኔና አብሮ አደጎቼ በሰፈራችን ውስጥ ትላልቅ ሰዎችን ዓረብ ቤት በመላላክ አገልግሎት መስጠቱ አንድ የውዴታ ግዴታችን ነበር፡፡ ጎረቤቶቻችን ከእናታችን ማሕፀን ስንወጣ ሁሉ የዓይን ምስክር ናቸው፡፡ እንደ አሳዳጊዎቻችን ስለሚቆጠሩም ከቤታችን ውጪ ሁሉም ትላልቅ ሰዎች በእኛ ሕይወትና ደኅንነት ላይ የወላጆቻችንን ያህል የመወሰን  መብት ነበራቸው፡፡

ተልከን ስንመለስ ልዩ ልዩ ጉርሻ ይሰጠን ነበር፡፡ መላላኩ ከመደጋገሙ የተነሳ ጉርሻቸው ምን እንደሚሆን ከወዲሁ እናውቀዋለን፡፡ የአንዳንድ ጉርሻ የሚናፈቅ ነበር፡፡ እማማ አመለወርቅ ከጅሩ ዘመዶቻቸው በሚጭኑላቸው ጥቁር ስንዴ የሚጋግሩት ሙልሙሉ አሁንም ሳስበው ምራቄን እውጣለሁ፡፡

የኃይሉ ዶሮ እናት እማማ ሸጊቱ በውብ ቋንቋቸው ሲመርቁን እዚያው በዚያው አድገን እንዲታየን እያደረጉ አሹቁን በኪሳችን ያጭቁታል፡፡ እማማ ቀለሚቱ….ከተላላክንላቸው በኋላ ከዕለታት አንድ ቀን የወሰዱብንን የጨርቅ ኳስ ይመልሱልናል፡፡

በእኔና በእማዬ ብቻ የሚታወቅ የጋራ ምስጢር አለን፡፡ ልትልከኝ ስትፈልግ ትጠራኝና መልዕክቱን ነግራኝ ‹‹ስትመለስ እማደርግልህን አታውቅም›› ካለችኝ ስመለስ በጣም በሚጣፍጠኝን የቅንጬ ፍቅፋቂ እንደምትሰጠኝ አውቃለሁ፡፡

  • ዘነበ ወላ ‹‹ልጅነት›› (2001)

*****

የጨዋታው ፈላስፋ

ደስታ ተክለወልድ አጫዋች የሚለውን ቃል ሲፈቱት ‹‹የሚያጫውት፤ አነጋጋሪ፤ አስቂኝ፤ ጥርስ የማያስከድን፤ አለቃ ገብረሐናንና አባ ምን ይዋብ ከሉን የመሰለ የጨዋታ ፈላስፋ›› ይሉታል፡፡ ቀልዱን ሁሉ ሰብስቦ ለአንድ ታዋቂ ሰው መስጠት ወይም ማውረስ የተለመደ ስለሆነ ነው እንጂ አገራችን የነበሩት አስቂኝ ሰው አለቃ ገብረሐና ስለሆኑ ብቻ አይደለም ‹‹አለቃ ገብረሐና እንዲህ አሉ›› እየተባለ የሚወሳው፡፡ ከጨዋታ ‹‹ፈላስፋነታቸውም›› በላይ አለቃ ገብረሐና የፍትህ ነገሥቱ፤ የመጻሕፍቱና የአቡሻክሩ ሁሉ አዋቂ ነበሩ፡፡ ‹‹አለቃ ገብረሐና እጅግ የተማሩ የጎንደር ሊቅ ነበሩ›› ሲሉም ብላታ ህሩይ ወልደ ሥላሴ ይህንኑ መስክረውላቸዋል፡፡

ይሁንና አለቃ ገብረሐና በዘመናችን የሚታወቁት በምሁርነታቸው ብቻ ሳይሆን በሃይለ ቃላቸውና በቀልዳቸው ነው፡፡ በርግጥም አለቃ ተረበኛ፤ ብልህና ጥርስ አያስከድኔ ነበሩ፡፡ ተማሪ ገብረሐና በሃያ ስድስት ዓመታቸው ጎንደር ውስጥ ሊቀ ካህናት ሆነው ተሾሙ፡፡ በዚህ ጊዜ አንዲት ጎንደሬ ዘንድ ጠበል ተጠርተው ቢሄዱ የሚወጡት ሰዎች ሁሉ ‹‹ጠላው ጥሩ አይደለም›› ሲሉ ይሰሙና ተመልሰው ወደቤታቸው ይሄዳሉ፡፡ ሴትየዋም በመቅረታቸው አዝና ቤታቸው ሄዳ ‹‹ምነው አለቃ ጠበል ጠርቼዎት ሳይመጡ ቀሩ?›› ብትላቸው፤ ‹‹ኧረ መጥቼ ሰው ግም፤ ግም ሲል ጊዜ ነው የተመለስኩት›› አሉዋት ይባላል፡፡

አንዲት አጠር፤ ደልደል ያለች ደባካ መሳይ ጎረቤታቸው ደግሞ ‹‹አባ ሰው ሁሉ ድንቼ፤ የኔ ድንች እያለ ያቆላምጠኛል›› ብትላቸው፣ ‹‹አዬ ሞኝት፣ እውነት መስሎሽ ነው? ድንቼ የሚሉሽ ሊልጡሽ እንጂ ነው አሉዋት፡፡››

ከጥቂት ቀናት በኋላም ያቺው ገልቱ ሴት ምሣ ትጋብዛቸዋለች፡፡ ሊቀ ካህናት እግራቸውን አንፈራጠው ዶሮአቸውን ሲኰመኩሙ ነበር የደረሱት፡፡ አለቃን የዶሮው ጭንቅላት ድስቱ ውስጥ እንዳለ ዓይኑ ፈጦ ታያቸው፡፡ ይኼኔ አጅሬ ሳቅ ብለው፤ ‹‹ዶሮ ምን እኔ ላይ ታፈጥብኛለህ? እኔ አላረድኩህ›› አሉት፡፡ ገበታው ከፍ እንዳለም ጠላ ቀርቦላቸው ሲጠጡ ቢያጣጥሙት ቀጭን ሆነባቸው፡፡ ታዲያ ይህነኑ እያቅማሙ ሳሉ ሴትዬይቱ መጥታ ‹‹ኧረ ይጠጡ፣ አንድ ተይዞ ቁጭ አይባልም›› እያለች ብታጣድፋቸው፤ ‹‹እሺ እጠጣለሁ፡፡ ለመሆኑ ይህን እህል ውኃ ያደረግሺው አንቺ ነሽ?›› አሉዋት፡፡

  • አረፈዓይኔ ሐጐስ ‹‹አለቃ ገብረሐና›› (1986)

*****

‹‹አንቺው ቀናቃኝ አንቺው ተቀባይ››

‹‹በዛብህ ሰብለን ይደክማታል እስቲ እረፍና ጨዋታ አምጣ!›› ስትል ሁኔታዋን እያዩ በዛብህና ሰብለ ሳቃቸውን መግታት አቃታቸው፡፡

‹‹እንዲያውም ዛሬ ማጫወቱ የኔ ፈንታ ይሁን፡፡ የዚያ የገበሬ አንዲር ልቤን በደስታ ሞልቶ ድምፄን ለዘፈን ቃኝቶ ሰዶኛል!›› አለችና ከወዲህ ወዲያ ከወዲያ ወዲህ እዬተንጎራደደች

‹‹ሌሊቱ እያጠረ እንዲህ ካስቸገረ

አንተናኔ

አንቺናኔ

ሳንሞት እንቀበር ተኝተን እንድኖር›› ብላ በዚያ መሰል በሌለው ውብ ድምጽዋ ዘፈነችና ከዚያ ቀጥላ እየተንበረከከችም እየቆመችም ባንገትዋ ዘፍና ሲደክማት ወድቃ ከላይ እየተነፈሰች ትስቅ ጀመር፡፡

‹‹አንቺው ቀናቃኝ አንቺው ተቀባይ አንቺው ደላቂ አንቺው አድማቂ ሆነሽ የብዙ ሰው ሥራ ብቻሽን ሠርተሽ ደከመሽ!›› አለ በዛብህ እየሳቀ፡፡

  • ሐዲስ ዓለማየሁ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› (1958)
- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች