Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምሒላሪ ክሊንተን የመጀመርያዋ የአሜሪካ ሴት ፕሬዚዳንት ለመሆን ቆርጠው ተነስተዋል

ሒላሪ ክሊንተን የመጀመርያዋ የአሜሪካ ሴት ፕሬዚዳንት ለመሆን ቆርጠው ተነስተዋል

ቀን:

የአሜሪካ የቀድሞ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሒላሪ ሮድሃም ክሊንተን እ.ኤ.አ. በ2016 ለሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሊወዳደሩ ይችላሉ የሚል ትንበያ ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ሲነገር ከርሟል፡፡ አንዳንዶች ይወዳደራሉ ሲሉ አንዳንዶች አይወዳደሩም፣ ከዲሞክራቲክ ፓርቲ ወገን ፕሬዚዳንት የመሆን ፍላጐታቸው በወቅቱ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ድል አድራጊነት ተጠናቋል ያሉም ነበሩ፡፡ እሳቸውም ቢሆኑ ግልጽ አድርገው ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ አልተናገሩም ነበር፡፡ ሒላሪ ክሊንተን አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ2016 የምታደርገውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አስመልክቶ ባለፈው እሑድ በለቀቁት የቪዲዮ መልዕክት ግን፣ ‹‹ለ2016 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እወዳደራለሁ፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በአሜሪካ ታሪክ ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር በፓርቲያቸው ከፍተኛውን ድጋፍ ያገኙ የመጀመሪያዋ ሴት የሆኑት ሒላሪ ክሊንተን፣ ‹‹አሜሪካውያን በየቀኑ አሸናፊዎችን ይፈልጋሉ፡፡ እኔም አሸናፊ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ የእናንተን ድምፅ ለማግኘት መንገዱን ጀምሬያለሁ፡፡ ይህ የእናንተ ጊዜ ነው፡፡ እናንተም በጉዞዬ ሁሉ ከጐኔ ትሆናላችሁ፤›› በማለት በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው እንደሚወዳደሩ አብስረዋል፡፡ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወካይዋ ክሊንተን በፓርቲያቸው ቅድመ ውድድር ከዚህ ቀደም ከነበረው ታሪክ በተለየ ሁኔታ ያለ ብቁ ተወዳደሪ የሚያልፉ ናቸው ተብሏል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2008 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በእሳቸውና በባራክ ሁሴን ኦባማ መካከል የነበረው ዓይነት ትንቅንቅ በ2016 ምርጫ አይኖርም ተብሏል፡፡ ይህም የ2016 ምርጫን ከሰባት ዓመታት በፊት በዲሞክራት መሪዎቹ መካከል ከነበረው የዲሞክራቲክ ፓርቲ የውስጥ የቅድመ ምርጫ ሽኩቻ ተቃራኒ ያደርገዋል፡፡ ለፕሬዚዳንታዊ ዕጩነት ምርጫ ሲወዳደሩም ይኼኛው ለሁለተኛ ጊዜያቸው ይሆናል፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ እ.ኤ.አ. የ2016 የምርጫ ውጤት ምንም ይሁን ምን ሒላሪ ክሊንተን በአሜሪካ ታሪክ ትልቅ ሥፍራ አሏቸው፡፡ በተለይ ባለቤታቸው ቢል ክሊንተን እ.ኤ.አ. በ1991 በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመሳተፍ ፍላጐት ካሳዩበትና ከተመረጡም በኋላ በነበረው የአሜሪካ አስተዳደር ዋና ተዋናይም ነበሩ፡፡ በአሜሪካ ሴኔት የተመረጡ የመጀመሪያዋ ቀዳማዊት እመቤት የነበሩም ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2008 በነበረው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፓርቲያቸው የውስጥ ቅድመ ምርጫ በኦባማ የተረቱት ክሊንተን፣ በኦባማ የፕሬዚዳንትነት ዘመንም እ.ኤ.አ. እስከ 2013 ድረስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል፡፡ በዲፕሎማቲክ ክህሎታቸው ዓለምን ማስደመም የቻሉም ናቸው፡፡ ክሊንተን ከኦባማ ሥር ሆነው የአሜሪካን የውጭ ግንኙነት በማጠናከር ፓርቲያቸውን ያስገረሙ ናቸው ይባልላቸዋል፡፡ ዓለምን ያነጋገሩም ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን ያተረፉትና በተለይም በሴቶች ዘንድ ጠንካራ ድጋፍ ያላቸው ሒላሪ ክሊንተን፣ ለዋይት ሐውስ የሚያደርጉት ውድድር የመጨረሻቸው ሊሆን ይችላል የሚል መላምት ተሰንዝሯል፡፡ የክሊንተን የምረጡኝ ዘመቻ በትንሽ ደረጃ የሚጀምር ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የምረጡኝ ዘመቻ ወጥቶ በማያውቅ መጠን ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚፈስበት አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ሒላሪ ክሊንተን ለሚያደርጉት የምረጡኝ ዘመቻም ከዲሞክራት ፓርቲ አቀንቃኞች የ2.5 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህን ያህል ገንዘብ የሚያወጣ የምረጡኝ ዘመቻ ለማድረግ የታሰበውም፣ በአሜሪካ ታሪክ ሴት ፕሬዚዳንት ከመምረጥ ፍላጐት ጋር በተያያዘ ነው ተብሏል፡፡ አንዳንዶች ግን የሴት ፕሬዚዳንት ከመምረጥ ጋር የተያያዘ ሳይሆን በፓርቲው ውስጥ አማራጭ ባለመኖሩ ነው ይላሉ፡፡ የ67 ዓመቷ ክሊንተን ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት መወዳደር እንደሚፈልጉ ማሳወቃቸውን ተከትሎ፣ በኒው ሃምፕሻየርና በአዮዋ የምረጡኝ ዘመቻ ይኖራል፡፡ እነዚህ ሥፍራዎች በቅድሚያ የተመረጡትም ራሳቸውን መልሰው ለማስተዋወቅና ዳግም መሠረት ለመጣል እንደሆነ፣ የክሊንተን የምርጫ ዘመቻ ዋና አስተባባሪ ሚስተር ጆን ዲ ፖዴስታ ተናግረዋል፡፡ የክሊንተን አጀንዳም መካከለኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ኑሮ ማሻሻል፣ ደመወዝ ማሳደግና በአሜሪካውያን ዘንድ የሚታየውን የገቢ አለመመጣጠን ማቀራረብ ነው፡፡ ሕክምናና በተመጣጣኝ ዋጋ የሕፃናት ክብካቤ ማቅረብም ከክሊንተን አጀንዳዎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ክሊንተን እ.ኤ.አ. በ2013 መጀመርያ ላይ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሥልጣናቸው ሲለቁ፣ ለ2016 ምርጫ ይወዳደራሉ የሚል መላምት ተሰንዝሮ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ደጋፊዎቻቸው እስከ 2014 ማብቂያ ድረስ ለምርጫ ዘመቻ የሚውል ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማሰባሰብ ችለዋል፡፡ ክሊንተን እ.ኤ.አ. ለ2016 ፕሬዚዳንት ምርጫ እወዳደራለሁ ብለው ከመናገራቸው አስቀድሞም ቢሊየነሩ ዋረን ቡፌት፣ ‹‹የ2016 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን የምታሸንፈው ክሊንተን ናት፡፡ ለዚህም እወራረዳለሁ፤›› ሲሉ እ.ኤ.አ. በ2012 በተደረገው ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ጉባዔ ላይ ተናግረው ነበር፡፡ የሃፍፖስት መረጃ እንደሚያሳየው፣ ክሊንተን በዴሞክራቲክ ፓርቲያቸው ውስጥም የመሪነቱን ደረጃ እንደጨበጡ ነው፡፡ አሜሪካ በ2016 ማብቂያ ላይ ለምታደርገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የቴክሳሱ ሴናተር ሪፐብሊካኑ ቴድ ክሩዝ ዕጩ ፕሬዚዳንት መሆን እንደሚፈልጉ ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡ ሴናተር ክሩዝ በፓርቲያቸው ውስጥ በሚኖረው ቅድመ ምርጫ ፓርቲያቸው ከሚያሳልፋቸው ዕጩዎች አንዱ ይሆናሉ ተብሎም ተገምቷል፡፡ የ44 ዓመቱ ክሩዝ በወግ አጥባቂነታቸው የሚታወቁ ሲሆን፣ ‹‹አሜሪካ ተመልሳ ኃያል እንድትሆን አዲስ፣ ጠንካራና ወግ አጥባቂ ትውልድ ያስፈልጋታል፤›› በሚለው አቋማቸውም ይታወቃሉ፡፡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሕክምና መዋቅር መዘርጋት፣ የአገር ውስጥ ገቢ ክፍያን ማስቆም፣ ጋብቻን በቤተ ክርስቲያን ማድረግና ውጣ ውረድ የበዛበትን ኑሮ ማሻሻል ከአጀንዳዎቻቸው መካከል እንደሚሆኑም መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ሒላሪ ክሊንተን ለፕሬዚዳንትነት ምርጫው እንደሚወዳደሩ ከተሰማ ወዲህ ከፍተኛ ትኩረት ያገኙ ሲሆን፣ ነቃፊዎቻቸውም ደካማ ጎናቸውን እያነሱ እየተሟገቱ ናቸው፡፡ እሳቸው ግን የመጀመሪያዋ የሴት ፕሬዚዳንት ለመሆን የሚያስችላቸውን የአሜሪካዊያንን ድምፅ ለማግኘት ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጋቸውም እየተነገረ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...