Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራር በምርጫ ቦርድ ላይ የመሠረተው ክስ ውድቅ ተደረገ

የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራር በምርጫ ቦርድ ላይ የመሠረተው ክስ ውድቅ ተደረገ

ቀን:

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የቀድሞ አመራር፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሥርቶት የነበረው የፍትሐ ብሔር ክስ ውድቅ ተደረገ፡፡ የአንድነት የቀድሞ አመራር ምርጫ ቦርድን የከሰሰው በአቶ ትዕግሥቱ አወሉ የሚመራው አዲሱ አመራር ፓርቲውን የማይወክል ነው በማለት ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ አዲሱ አመራር ከቀድሞ አመራርና ከፓርቲው ዕውቅና ውጪ ያደረገውን ስብሰባ፣ የምርጫ ሪፖርትና ለተመራጭ ግለሰቦች ዕውቅና መስጠቱንም ተቃውሟል፡፡ ቦርዱ የአሁኖቹ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ጥር 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ያደረጉትን ስብሳባ፣ የምርጫ ሪፖርትና ተመራጮች ጥር 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ዕውቅና መስጠቱ ከሕግ አግባብ ውጪ መሆኑን የገለጸው የቀድሞ የፓርቲው አመራር ክስ፣ የቦርዱ ውሳኔ ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ድንጋጌዎችን የሚቃረንና የሚሽር መሆኑን ጠቅሷል፡፡ በመሆኑም የቀድሞ የፓርቲው አመራር ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ያሻሻለው መተዳደርያ ደንብን ቦርዱ ተቀብሎ እንዲመዘግብና አቶ በላይ ፈቃዱን የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡን ዕውቅና እንዲሰጥለት ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርቦ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ በሰጠው ምላሽ፣ በአሁኑ ጊዜ በቦርዱ ሕጋዊ ሰውነት ኖሮት ተመዝግቦ የምስክር ወረቀት ተሰጥቶት አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)ን እያንቀሳቀሰው የሚገኘው የእነ አቶ በላይ ፈቃዱ አመራር ሳይሆን፣ እነ አቶ ትዕግሥቱ አወሉ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ ከእነ አቶ በላይ ፈቃዱ ጋር የነበሩ የቡድኑ አባላት በፈጸሟቸው ሕገወጥ ድርጊቶች ቦርዱ ከጥር 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ዕውቅና የነፈጋቸው መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ እነ አቶ በላይ ፈቃዱ ዕውቅና በቦርዱ ሳይሰጣቸው በአንድነት ስም ሕጋዊ አስመስለው መክሰስና መከሰስም የማይችሉ መሆኑንም አክሏል፡፡ በመሆኑም መዝገቡ ተዘግቶ እንዲሰናበት ቦርዱ ጠይቋል፡፡ የቀረበው ክስ የፓርቲው አመራሮች ፊርማን እንዳልያዘም ቦርዱ ጠቅሷል፡፡ ክስ መመሥረት እንኳን የሚችሉ ቢሆን (እነ በላይ) 20 ቀናት ያለፈ በመሆኑ ይርጋ ስለሚያግደው፣ ክሱ ውድቅ ተደርጎ ማቅረብ የሚችሉት አቀራረቡ በይግባኝ መሆን ስላለበት ተቀባይነት እንደማይኖረው ገልጿል፡፡ ቦርዱ የሰጠው ውሳኔ የምርጫ ሕጉንና የፓርቲውን መተዳደርያ ደንብ ተከትሎ የፓርቲውን ህልውና ለመታደግ በመሆኑ የወሰደው ዕርምጃ ሕጋዊ እንደሆነ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ክስ የመሠረተው የቀድሞ የአንድነት አመራር በሰጠው የመልስ መልስ እንደገለጸው፣ ክሱን ያቀረበው በፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ቁጥር 573/2000 መሠረት በተሰጠው የምስክር ወረቀት ማስረጃነት ነው፡፡ በመሆኑም መክሰስም መከሰስም ይችላል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 7(2) መሠረት ከሳሽ አንድነት ፓርቲ እንጂ እነ አቶ በላይ ፈቃዱ እንዳልሆኑም አመልክቷል፡፡ በመሆኑም ቦርዱ የሰጠው ምላሽ የሕግ መሠረት እንደሌለው ገልጿል፡፡ ስለይርጋ ቦርዱ የሰጠው ምላሽን በሚመለከትም፣ ክሱ የቀረበው ከይርጋ ቀኑ በፊት መሆኑን ገልጿል፡፡ ክሱ በፓርቲው አመራሮች ሳይፈረም እንደቀረበ የተገለጸውን በሚመለከትም፣ በጠበቃ ተፈርሞ የቀረበ ስለሆነ የግድ የፓርቲው አመራሮች ተፈርሞ እንዲቀርብ የሚያስገድድ ሕግ አለመኖሩንም አስረድቷል፡፡ በመሆኑም የቦርዱ መቃወሚያዎች የሕግ መሠረት እንደሌላቸው የቀድሞ አመራር በጠበቃው አማካይነት የሰጠው የመልስ መልስ ያስረዳል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ምላሾች ከተመለከተ በኋላ፣ ‹‹ዕውን ከሳሽ ማነው? ከሳሽ ተብሎ የቀረበው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ወይስ ሌላ?›› የሚለውን ጭብጥ ይዞ መመርመሩን ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሲመረምር ያረጋገጠው ከሳሽ የአንድነት ፓርቲ ሆኖ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ነው፡፡ የተፈጥሮ ሰውነት ባህሪ የተላበሰ ባይሆንም፣ ሕጋዊ ውጤት ያለውን ተግባራት ለማከናወን ተቋሙ በራሱ እንደ ሰው ስለሚቆጠር ውል መዋዋልና ማፍረስ እንደሚችል አብራርቷል፡፡ ፓርቲው ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ከጊዜ በኋላ የፓርቲው አመራሮች በፈጠሩት አለመግባባት በእነ አቶ በላይ ፈቃዱና ሌላው ቡድን በማለት ለሁለት መከፈሉን ጠቁሟል፡፡ በሁለት በመከፈሉ የፓርቲውን ህልውና የሚፈታተኑ ችግሮች መፈጠራቸውን የተረዳውና በአዋጅ ቁጥር 573/2000 የተሰጠውን ፓርቲዎችን የመቆጣጠርና የማስተካከል ሥልጣን ያለው ቦርዱ፣ ቡድኖቹ የጋራ ጠቅላላ ጉባዔ በማድረግ ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱና ምርጫ እንዲያደርጉ ካደረገ በኋላ ጥር 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ክሱን ያቀረበውን (የእነ አቶ በላይ ቡድንን) ቡድን የአመራርነት ዕውቅና መንፈጉን ፍርድ ቤቱ አብራርቷል፡፡ ሰነዶችም ይህንኑ እንደሚያረጋግጡ አክሏል፡፡ ከሳሹ (የእነ አቶ በላይ ቡድን) ምርጫ ቦርድ የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ሰጥቶኛል የሚለው የምዝገባ ሰርተፊኬት ቢሆንም፣ ሕጋዊ ዕውቅና ተሰጥቶት ወደ ምርጫ ሒደቱ ገብቶ እየተንቀሳቀሰ ያለውን አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ /አንድነት ስም ‹‹ሕጋዊ ካባ›› ለብሶ ከመቅረቡ ውጪ፣ አንድም ሕጋዊ ሰብዕናና የሕጋዊ ውክልና ሥልጣን መሠረት እንደሌለው ፍርድ ቤቱ አትቷል፡፡ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 9 (2)፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 662/2002 አንቀጽ 6 (መ) እና አንቀጽ 7 ከመተላለፍ በተጨማሪ ሕጋዊ ውክልና ካለው ፓርቲ ውጪ የቀረበ ክስ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ በመሆኑም የእነ አቶ በላይ ቡድን የመክሰስ መብት የሌለው መሆኑን በማስታወቅ ክሱን ውድቅ አድርጎታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...