Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናሁለተኛ ደረጃ የካይዘን ፍልስፍና መተግበር ጀመረ

  ሁለተኛ ደረጃ የካይዘን ፍልስፍና መተግበር ጀመረ

  ቀን:

  – የፓርላማ አባላት ካይዘን ከቢፒአርና ከሌሎች አሠራሮች ጋር እየተጋጨ መሆኑን ገለጹ

  – በሦስት ዓመት ይገነቡ የነበሩ ቤቶች በካይዘን አንድ ዓመት ብቻ ይወስዳሉ ተባለ

  ካይዘን የተሰኘው የጃፓኖቹ የምርታማነትና የጥራት ፍልስፍና በኢትዮጵያ በተቋም ደረጃ መተግበር በጀመረ ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ጊዜ በኋላ፣ ኢትዮጵያ የመጀመርያ ደረጃ ካይዘንን በራሷ አቅም ማስኬድ መጀመሯና ከአፍሪካ ቀዳሚ ባለቤት የሆነችበት ምዕራፍ ላይ መድረሷ ተገለጸ፡፡

  የኢትዮጵያ ካይዘን (ካይዘን) ኢንስቲትዩት በሚል ስያሜ የተዋቀረው ተቋም በአገሪቱ ለካይዘን አተገባበር ኃላፊነት ተሰጥቶት እየሠራ ሲሆን፣ የዚህን ዓመት ስምንት ወራት አፈጻጸሙንና ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት ሊሠራቸው ያሰባቸውን ሥራዎች በማስመልከት፣ ለተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ለመንግሥት ተቋማት ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ 

  የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ታደሰ ለፓርላማ አባላት የተቋማቸውን ሥራዎች ሲያቀርቡ፣ የካይዘን ፍልስፍናና አሠራሩ ከመሠረታዊ ሥራ ሒደት ለውጥ (ቢፒአር)፣ ቤስት ስኮር ካርድና ከሌሎች አሠራሮች ጋር ሳይጣላና ሳይጋጭ እየተተገበረ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ ሆኖም የፓርላማ አባላት ይህ አባባላቸው ትክክል እንዳልሆነና በተግባርም ካይዘን ከተባሉት የአሠራር ሥርዓቶች ጋር እየተጋጨ ችግሮች መከሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህንን በማስመልከት የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ካይዘን ከአንድ ለአምስትና ከሌሎች የልማት ቡድን አደራጃጀቶች (ካይዘን ልማት ቡድን/ከልቡ የሚባል አደረጃጀት ይከተላል) ጋር እየተደራረበ ነው ያሉት አቶ ይድነቃቸው፣ ካሉት የአገሪቱ አሠራሮች ጋር አቀናጅቶ ማስኬዱ ላይ ሊታሰብበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

   ከዚህም ባሻገር የካይዘን ኢንስቲትዩት አደረጃጀት እስከ ታች እንዲወርድም አቶ ይድነቃቸው ጠይቀዋል፡፡ ካይዘን ‹‹እግር ሊኖረው ይገባል፤›› ያሉት አቶ ይድነቃቸው፣ የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ስምንት ቢሊዮን ብር የሚያንቀሳቅስ ተቋም መሆኑን ገልጸው፣ (የ40/60 ቤቶች ግንባታ ፕሮግራም ሲታከልበት አሥር ቢሊዮን ብር ይደርሳል) የካይዘን የአሠራር ፍልስፍና ለተቋሙ ከፍተኛ ለውጥ እያስገኘ መምጣቱንም አመልክተዋል፡፡

   በቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት የክትትል ኃላፊው አቶ  ተክሉ ፍቅሩ አማካይነት እንደተብራራው፣ ከዚህ ቀደም ምድር ቤቱን ጨምሮ ባለአራት ወለል የኮንዶሚኒየም ሕንፃዎችን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመት ይፈጅ ነበር፡፡ ካይዘን በሙከራ ደረጃ በተተገበረባቸው ፕሮጀክት 13 እና 14 በተባሉ ሁለት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችና የካ አባዶ በተባለው የግንባታ ቦታ ላይ፣ በካይዘን አሠራር አማካይነት ተሞክሮ ግንባታቸው አንድ ዓመት ብቻ የፈጁ ከ1,660 በላይ ቤቶች በቅርቡ ከተላለፉት 35 ሺሕ ቤቶች ጋር ለዕድለኞች መተላለፋቸውን ገልጸዋል፡፡

  አቶ ተክሉ እንዳብራሩት፣ ካይዘን ከመተግበሩ ቀደም ብሎ የነበሩት የንብረት አያያዝና አጠቃቀም ብክነቶች በካይዘን ትግበራ ቀንሰዋል፡፡ የጊዜ አጠቃቀም መቀየሩን ጠቅሰው ለአማካሪዎች፣ ለተቋራጮች፣ ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶችና ለሌሎችም በቤቶች ግንባታ ለሚሳተፉ አካላት የካይዘን አሠራር ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ ለቤቶች ግንባታ ከ530 በላይ ግብዓቶች ይቀርባሉ ያሉት አቶ ተክሉ፣ በካይዘን ምክንያት በእነዚህ የግንባታ ግብዓቶች ላይ ይታይ የነበረው ብክነት መቀነሱን አስረድተዋል፡፡

  አቶ ጌታሁን እንዳስታወቁት፣ በአገሪቱ ካይዘን መተግበር ከጀመረ ከሁለት ዓመት ተኩል ወዲህ በብክነት፣ በዕቃዎች ፍለጋና በመሳሰሉት ጊዜ አባካኝ አሠራሮች ሳቢያ በየፋብሪካው ይባክን የነበረው ገንዘብ እየቀነሰ መምጣቱን ጠቁመው፣ እስካሁን አንድ ቢሊዮን ብር ያህል ማዳን መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ዓመት ስምንት ወራት ውስጥም 143 ሚሊዮን ብር ያህል ማዳን እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

  ኢትዮጵያ የመጀመርያ ካይዘንን በመተግበርና የአሠራር ፍልስፍናውን ወደ ራሷ በማምጣት ከአፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን መብቃቷን ያስታወቁት አቶ ጌታሁን፣ በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን የካይዘን ማሠልጠኛ ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ይፋ አድርገዋል፡፡ በካይዘን አሠራር ላይ በአሁኑ ወቅት የመቐለ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በማስተርስ ዲግሪ ተማሪዎችን ማሠልጠን እንደተጀመረ፣ ወደፊት ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ዶክትሬት ደረጃ ባለው ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ካይዘንን በማካተት ለማሠልጠን እየታሰበበት መሆኑን አቶ ጌታሁን አስታውቀዋል፡፡

  በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ ከ135 ሺሕ በላይ አመራሮችንና ሠራተኞችን ለማሠልጠን ያቀደው ካይዘን ኢንስቲትዩት፣ እስካሁን ከ33 ሺሕ በላይ ሰዎችን በካይዘን አሠራር አሠልጥኗል፡፡ በአምስት ዓመት ውስጥ 135 ሺሕ ሰዎችን ማሠልጠን ‹‹የቁጥ ቁጥ›› ዕቅድ እንደሆነ በመግለጽ የተቸቱት የፓርላማ አባላት፣ ተቋሙ በሰው ኃይል የሚገኝበትን ደረጃ አልወደዱለትም፡፡ እስካሁን 35 በመቶ ነባር ሠራተኞቹ እንደለቀቁበት የካይዘን ኢንስቲትዩት ይፋ አድርጓል፡፡

  የመጀመርያ ደረጃ የካይዘን ፍልስፍናን በኢትዮጵያውያን አሠልጣኞችና ሙያተኞች መተግበር የሚችልበት አቋም ላይ የሚገኘው ካይዘን ኢንስቲትዩት፣ የጃፓኖች ድጋፍ በማያስፈልግ ደረጃ ላይ መደረሱን አቶ ጌታሁን አስረድተዋል፡፡ ይልቁንም በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ይተገበራል የተባለው የካይዘን ሥርዓት በአብዛኛው በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ ያተኮረ ከመሆኑም ባሻገር፣ በፒኮክ ጫማ ፋብሪካ፣ በማ ጋርመንት፣ በአዲስ መድኃኒት አክሲዮን ማኅበር፣ በወንጂ ስኳርና በመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎች ላይ ሁለተኛ ደረጃ የካይዘን ሥርዓት መተግበር መጀመሩ ታውቋል፡፡ በሁለተኛው ደረጃ ላይ ግን የፓጃኖች ድጋፍ እንደሚቀጥል፣ በ2012 ዓ.ም. ካይዘን ‹‹የላቀ ሥራ ባህል መገንቢያ፣ የፈጠራ አመራር ዕውቀት መቅሰሚያ የልቀት ማዕከል›› የመሆን ራዕይ ኢንስቲትዩቱ መቅረፁን አቶ ጌታሁን አስታውሰዋል፡፡ ይህም ቢባል ግን ሁለተኛ ደረጃ ወይም የላቀ ደረጃ ያለው ካይዘን በፋብሪካዎች ዙሪያ መገደቡንም የፓርላማው አባላት ተችተዋል፡፡ ይልቁንም በመንገድ ግንባታና በግብርና መስኮች ላይ መግባት እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡

   

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...