Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአቶ ሌንጮ ለታ ፓርቲ ማኒፌስቶ ከጦማሪያኖች ቤት በፍተሻ መገኘቱ ተመሰከረ

የአቶ ሌንጮ ለታ ፓርቲ ማኒፌስቶ ከጦማሪያኖች ቤት በፍተሻ መገኘቱ ተመሰከረ

ቀን:

በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ክስ በተመሠረተባቸው ጦማሪያን ቢሮና መኖሪያ ቤት አቶ ሌንጮ ለታ ያቋቋሙት አዲስ ፓርቲ ማኒፌስቶ መገኘቱን፣ ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸው ምስክሮች መጋቢት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው ተናገሩ፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት መጋቢት 30 ቀን የቀረቡት አምስት ምስክሮች ሲሆኑ፣ ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን ተቀጥራ በምትሠራበት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቢሮዋ ውስጥ ያለ መሳቢያ ሲፈተሽና ሲበረበር ሲዲዎች መገኘታቸውን፣ በኮምፒዩተሯ ውስጥ የነበሩ ሰነዶች ታትመው ሲወጡ ማየቱንና እሷም የራሷ መሆኑን አምና ከፈረመች በኋላ እሱም መፈረሙን የዓቃቤ ሕግ 14ኛ ምስክር ተናግሯል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ታትሞ የወጣውን ሰነድ ይዘቱ ምን እንደሚል ጠይቆት፣ አቶ ሌንጮ ለታ አዲስ ያቋቋሙት ፓርቲ [ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር] ማኒፌስቶን ማየቱን ገልጿል፡፡

ዓቃቤ ሕግ አስመስክሮ እንደጨረሰ ፍርድ ቤቱ መስቀለኛ ጥያቄ እንዳላቸው የተከሳሽ ጠበቆችን ሲጠይቃቸው፣ ‹‹የቀረቡት ምስክር በደንበኞቻችን ላይ ስላልመሰከሩ መስቀልኛ ጥያቄ የለንም፤›› በማለታቸው ዓቃቤ ሕግ ተቃውሞ አቀረበ፡፡

ቀደም ባሉት የችሎት ሒደቶች ጠበቆች ተመሳሳይ ምላሽ ሲሰጡ ፍርድ ቤቱ ዝም ማለቱ አግባብ አለመሆኑን ገልጾ፣ እንደዚህ እያሉ እንዲመልሱ የሚያስችላቸው የሕግ አግባብ ስለሌለ፣ በሕጉ መሠረት ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥለት አመለከተ፡፡ ፍርድ ቤቱም የምትጠይቁት መስቀልኛ ጥያቄ ከሌላችሁ ‹‹የለንም በሉ፡፡ በተከሳሾቹ ላይ መመስከር አለመመስከሩን የማረጋገጥ ጉዳይ የፍርድ ቤቱ ነው፤›› በማለት ብይን ሰጥቷል፡፡

ሌላው 15ኛ የዓቃቤ ሕግ ምስክር ቀርቦ በጦማሪ ማኅሌት ላይ በሰጠው ምስክርነት፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተጻፉ እስከ 40 ገጽ የሚደርሱ ሰነዶች ከኮምፒዩተር ታትመው ከወጡ በኋላ፣ የእሷ መሆናቸውን አምናባቸው ከፈረመች በኋላ እሱም መፈረሙን አስረድቷል፡፡ ስለፈረመባቸው ሰነዶች ይዘት እንዲናገር ዓቃቤ ሕግ ላቀረበለት ጥያቄም፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማኒፌስቶዎች መሆናቸውን ተናግሮ ጨርሷል፡፡

የተከሳሽ ጠበቃ ባቀረቡት መስቀልኛ ጥያቄ፣ ‹‹ሲዲውን ያመጣው ማነው? ፖሊስ ወይስ ማን? ሲዲው ባዶ ነበር ወይስ በውስጡ ምን ነበረበት…?›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡለት፣ ‹‹ሲዲው ባዶ መሆኑን አረጋግጠናል፤›› ብሏል፡፡ ‹‹ያየኸው የፖለቲካ ፓርቲ ማኒፌስቶ ስንት ነው?›› የሚል ጥያቄ ሲቀርብለትም፣ ‹‹አንድ ብቻ አይደለም፡፡ የማስታውሰው የአቶ ሌንጮ ለታን ብቻ ነው፤›› ብሏል፡፡ ጠበቃው አንድ ሰነድ አውጥተው፣ ‹‹ይኼ ሰነድ ዓቃቤ ሕግ በማስረጃነት ያቀረበው ሰነድ ነው፡፡ ምስክሩም ፈርሞበታል፡፡ እያየው እንዲመሰክር ይፈቀድልኝ፤›› በማለት ፍርድ ቤቱን ሲጠይቁ ተፈቀደላቸው፡፡ ሰነዱ ተሰጥቶት እያየው እያለ ለሚቀርብለት ጥያቄ ምስክሩ በደንብ ማስረዳት ባለመቻሉ፣ ዓቃቤ ሕግ ምስክሩ ለመመለስ ሊገደድ እንደማይገባ ተቃወመ፡፡ ጠበቃው በመቀጠል፣ ‹‹ዓቃቤ ሕግ እንደፈቀደ የሚጠይቅበት፣ ጠበቃ ደግሞ የሚከለከልበት የሕግ አግባብ ስለሌለ ልንከለከል አይገባም፤›› በማለት ለተቃውሞው ተቃውሞ አቀረበ፡፡ ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግን ተቃውሞ በማለፍ ጠበቃው እንዲቀጥሉ ፈቀደ፡፡ ምስክሩ በሰነዱ ላይ ያለው ፊርማ የእሱ መሆኑን አረጋገጠ፡፡ ይዘቱን እንዲገልጽ ሲጠየቅ፣ ‹‹ቅድም ከመሰከርኩት ጋር አይገናኝም፤›› አለ፡፡ ቀደም ብሎ ስለአቶ ሌንጮ ፓርቲ ማኒፌስቶ ከተናገረው ጋር እንደማይገናኝ ሲናገር፣ ፍርድ ቤቱ በመሀል ገብቶ ‹‹በ40 ገጹ ላይ በሙሉ አንብበህ ነው የፈረምከው?›› የሚል ጥያቄ አቀረበለት፡፡ በሲዲ ሲገለበጥ ማየቱን እንጂ አለማንበቡን ተናገረ፡፡ ‹‹በዚያን ቀን (ታዛቢ ሆኖ በቀረበበት ግንቦት 7 ቀን 2006 ዓ.ም.) ያየሁትና የፈረምኩበት ነው የሚለውም ክፍት የሥራ ማስታወቂያ ነው፤›› አለ፡፡

ፍርድ ቤቱ በድጋሚ ‹‹የትኛውን ነው ያነበብከው?›› ሲለው ረጅም ጊዜ ስለሆነው ማስታወስ እንደማይችል ተናገረ፡፡ የአቶ ሌንጮ ፓርቲ ማኒፌስቶ የተባለውን ሰነድ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱ አዘዘ፡፡ አገላብጦ ካየውና ፊርማው የእሱ መሆኑን ከገለጸ በኋላ፣ ስለማኒፌስቶው ግን ጦማሪ ማኅሌት ስትናገር መስማቱን በመግለጽ ምስክርነቱን አጠናቋል፡፡

ሌሎቹም የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ከጦማሪያን አጥናፍ ብርሃኔና ዘለዓለም ክብረት ላይ በተገኙ ማስረጃዎች ላይ መፈረማቸውን ያስረዱ ናቸው፡፡ በጦማሪ አጥናፍ ቤት ወደ 250 የሚደርሱ መጻሕፍት መገኘታቸውን፣ ከላፕቶፕና ከኮምፒውተር ላይ የታተሙ ሰነዶች፣ ሲዲዎችና ማስታወሻ ደብተሮች መገኘታቸውን እሱ አምኖ ሲፈርም እሱም መፈረሙን ምስክሩ ገልጿል፡፡ ‘ሴኪዩሪቲ ኢን ቦክስ’ የሚል በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈ ወደ 200 የሚደርስ ገጽ ያለው መጽሐፍም መገኘቱን ተናግሯል፡፡ በጦማሪ ዘለዓለም ቤትም ሐርድ ዲስክ፣ ላፕቶፕ፣ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ቋንቋዎች የተጻፉ ሰነዶች ታትመው ሁለቱም መፈረማቸውን መስክሯል፡፡ መጽሔቶችና ጋዜጦች መገኘታቸውንም ገልጿል፡፡ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ተሰምተው እንዳበቁ ዓቃቤ ሕግ ለመጨረሻ ጊዜ ቀሪ ምስክሮቹን አቅርቦ እንዲያሰማ ለግንቦት 18 እና 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ጠበቆች ተሟልተው እንዲቀርቡ ያመለከቱባቸውና ፍርድ ቤቱም ትዕዛዝ ሰጥቶበት የነበረው የሲዲ ማስረጃዎችን በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ ሰባት ብቻ አቅርቦ፣ ቀሪዎቹን ያላቀረበው ሲዲዎቹን የያዙት ኃላፊ ባለመኖራቸውና ለሥልጠና ወደ ውጭ መውጣታቸውን ገልጿል፡፡ ጠበቆች አጥብቀው በመቃወማቸው ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግን ምክንያት ውድቅ በማድረግ ለመጨረሻ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...