Tuesday, December 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ዶሮ በላቾች

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የከተማ አኗኗር ዘዴ እየተቀየረ ሲመጣ፣ የሰውም ነባር ልምዶች በአዳዲስ ፍላጎቶች እየተቀየሩ፣ የቆዩ ልማዶች በአዳዲሶቹ እየተተኩ ይሄዳሉ፡፡ አንዳንዴም በወዲያኛው ዘመን እንደነውር ወይም እንደጸያፍ የሚታዩ ልማዶች በዚህ ወቅት ተራ፣ የዕለት ተዕለት የአኗኗር ሥርዓት አካል ይሆናሉ፡፡

  ለዚህ አባባል መነሻ የሆነው ቄራ አካባቢ የተጀመረ የንግድ አሠራር ነው፡፡ በተለምዶ ቄራ በረት ወይም ግቢ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ዶሮ በመሸጥ ይተዳደሩ የነበሩ ነጋዴዎች አዲስ አሠራር አምጥተዋል፡፡ ዶሮ አርዶና በልቶ፣ ቆዳ መልስ ለደንበኛው ማስረከብ፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነጋዴዎች እንደሚገልጹት፣ ዶሮውን አርዶና ላባውን አራግፎ የማስረከብ ሐሳቡን ያመጡት ዶሮ ገዥዎች ናቸው፡፡ በተለይ የኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች፣ በየቤታቸው ዶሮ አርደውና ላባ ገንጥለው ወጡን ለመሥራት መቸገራቸውን በተደጋጋሚ ከመግለጽ ባሻገር፣ ነጋዴዎቹ አርደው ብልቱን የሚረከቡበትን ዘዴ እንዲፈጥሩላቸው ይወተውቷቸው እንደነበር የገለጹት አቶ ድሉ መሐመድ ናቸው፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት በዶሮ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ድሉ፣ ከዚህ ቀደም እዚያው መደባቸው ላይ ሌላ ሥራ ይሠሩ የነበረ ቢሆንም አካባቢው ላይ ካለው የዶሮ ገበያ አኳያ ፊታቸውን ወደዚያው ማዞራቸውን ይናገራሉ፡፡ 

  ወደ ቄራው ዶሮ መሸጫና ማረጃ ቦታ የሚያቀናው ገበያተኛ፣ ከዚያው አካባቢ ጀምሮ ከበቅሎ ቤት፣ ከጎተራ፣ ከለቡ፣ ከመብራት ኃይል፣ ከጀሞና ከመካኒሳ አካባቢዎች እየመጣ እንደሆነ ሻጮቹ ይገልጻሉ፡፡ ዶሮውን ከመሸጥ ባሻገር አርዶ ለደንበኛው ለመስጠት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ፈቃድ እንደሰጣቸውና ይህንን ሥራ የሚሠሩት ፈቃድ ያላቸው ነጋዴዎች ዘጠኝ ያህል መሆናቸውን ከነጋዴዎቹ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የዶሮ ዕርድ የሚካሄድበት ቦታ ከተለመደው የዶሮ መሸጫ የሚለየው፣ ዶሮዎቹ የሚታረዱበትና ደማቸው በቱቦ በኩል ውኃ እየተቀላቀለበት እንዲወርድ የሚያስችል ሥርዓት ነጋዴዎቹ መገንባት መቻላቸው ነው፡፡

  ቀደም ሲል የዶሮ ዕርዱን ሲጀምሩ እንዲሁ ለትብብር ያህል የነበረ በመሆኑ፣ የጤና ቢሮ ዕርድ ለማካሔድ መከተል ያለባቸውን የንጽሕና አሠራር ሲያስቀምጥና ለወጪ የሚዳርጋቸው መሆኑን ሲረዱ፣ ነጋዴዎቹ የዕርድ አገልግሎት አቋርጠው እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም ዶሮ ታርዶላቸው ይገዙ የነበሩ ደንበኞች ቅሬታ በመበራከቱ በንግድ ቢሮ መሥፈርት መሠረት ማረጃ ቦታ አሰናድተው ለመሥራት መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡ 

  አቶ ድሉ ለሪፖርተር እንዳብራሩት ከሆነ፣ አንድ ዶሮ አርዶና ቆዳውን አራግፎ ለደንበኛው ለመስጠት የሚያስከፍሉት አሥር ብር ነው፡፡ ሆኖም ይህ ገንዘብ ከዶሮ አራጆችና ከጽዳት ወጪዎች አኳያ ጥቅም የሚሰጥ አይደለም ይላሉ፡፡ እንዲህ መሥራቱ ደንበኛውን ለመሳብ ሲባል እንጂ ጥቅም ኖሮት አይደለም የሚሉት አቶ ድሉ፣ በተለይ እንደ ፋሲካ ባለው በዓል ወቅት ዶሮ አርዶና በልቶ መስጠቱ፣ ከሚኖረው ዶሮ ገዥና  ከሠራተኛ አኳያም የሚፈለግ ሥራ አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ ደንበኛው ግን ዶሮ ታርዶ ቆዳው ተገፎ እንዲሰጠው ከጠየቀ አማራጭ  የለም ይላሉ፡፡ በተለይ የኮንዶሚኒየም ተከራዮች በብዛት ዶሮ ገዝተውና አሳርደው የሚወስዱት ከሚኖሩበት ቤትና አካባቢ አኳያ እንደሆነ ሲናገሩ፣ ሌሎች በኮንዶሚኒየም የማይኖሩ ተከራዮች ደግሞ ከዚህም የባሰ ምክንያት እንደሚያቀርቡላቸው አቶ ድሉ ገልጸዋል፡፡ አከራዮች ተከራዮቻቸው ዶሮ ሲያርዱ ላባውና ሌሎችም ቆሻሻዎችን የሚጥሉበት በማጣት ከአከራዮች የሚደርስባቸውን ወቀሳ ለማምለጥ ጥሩ መፍትሔ እንደሆናቸው እንደሚነግሯቸው ነጋዴዎቹ ይገልጻሉ፡፡

  አንድ ዶሮ አርዶ ለመግፈፍ ስንት ሰዓት ይፈጃል? አቶ ድሉ እንደሚገልጹት፣ እንደ አራጁ ቅልጥፍና የሚለያይ ሲሆን፣ ልምድ ያለው ከሆነ አርዶ ለመግፈፍ አሥር ደቂቃና ከዚያም በታች ይበቃዋል፡፡ ቀልጣፋ ካልሆነና ልምዱም ያን ያህል ከሆነ እስከ 30 ደቂቃ ሊፈጅበት ይችላል ብለዋል፡፡ የዶሮ ዕርድ አገልግሎቱና የሚጠየቅበት ዋጋ ለደንበኛው ከሚያስገኘው አኳያ ክፍያው እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ የሚሞግቱት አቶ ድሉ፣ ደንበኞች ቤታቸው ወስደው ቢያርዱት የሚያስወጣቸውን ወጪ መመልከት ይገባል ይላሉ፡፡ አንድ ዶሮ አርዶ ብልቱን ለማውጣት፣ በተለምዶ በፈላ ውኃ ላባውን ማስወገድ፣ ላባው ከተላቀቀ በኋላ የሚቀረውን ፀጉር ከቆዳው ለማጽዳት፣ በቀሰም ዶሮውን ነፍቶ፣ በእሳት መለብለብ የመሳሰሉት አድካሚ ሥራዎች ከገንዘብና ከሚወስዱት ጊዜ አኳያ በዋጋ ቢተመኑ ምን ያህል እንደሚሆኑ ይጠይቃሉ፡፡ ዶሮ አራጆቹ ጋር የሚያሳርድ ደንበኛ ጊዜና ገንዘቡን ቢቆጥብም፣ አንድ የሚያጣው ነገር ግን አለ፡፡ ይኸውም የዶሮ ቆዳ ነው፡፡ የዶሮውን ቆዳ መመገብ የሚፈልግ ደንበኛ ዶሮውን ከነነፍሱ ቤቱ ወስዶ ራሱ መበለት ይጠበቅበታል፡፡

  በቀን እንደ ገበያው ሁኔታ በአማካይ ከአሥር እስከ 50 ዶሮ አርደውና በልተው የሚያስርክቡ ነጋዴዎች በቄራ ገበያ እንዳሉ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከዚህ ባሻገርም በርካታ ሱፐር ማርኬቶችና ሆቴል ቤቶች ዶሮ አስበልተው እንደሚወስዱ ነጋዴዎቹ ይገልጻሉ፡፡ ይህንን ሥራ በመሥራታቸው ምክንያት ያላሰቡት ነገር ውስጥ መግባታቸውን በመግለጽ ቃለ ምልልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑበትን ምክንያት በብስጭት አስታውቀው ነበር፡፡ ስማቸው እንዲገለጽ የማይፈልጉት እኚህ ነጋዴ፣ መንግሥት ይህንን አገልግሎት መስጠታቸውን በሚዲያ ተከታትሎ በሌሎች አካባቢ ዶሮ ነጋዴዎች ላይ የማያደርገውን የታክስ መጠን እንደጣለባቸው ይናገራሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የተርንኦቨር ታክስ በየሦስት ወሩ እንዲከፍሉና የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ እንዲይዙ እየተገደዱ መምጣታቸውን ይናገራሉ፡፡ በዕድሜ የገፉት እናትም እንዲሁ በሥራው ደስተኛ አለመሆናቸውን፣ እንዲሁ ብቻ ደንበኞች እንዳይሸሹ ሲባል ብቻ የዕርድ አገልግሎት እንደሚሰጡ ይገልጻሉ፡፡ እሱም ቢሆን አራጁ አካባቢው ላይ ካለና የማረጃውን ሒሳብ አሥር ብር በሙሉ ልውሰድ ካላላቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡

  ይህም ሆኖ ደንበኞቻቸው አገልግሎቱ እንዳይቋረጥባቸው እንደሚፈልጉ የሚገልጹት ነጋዴዎቹ፣ እነሱም ቢሆኑ አሁን ላይ የዶሮ ዕርድ ሥራውን ለማቆም አይከጅሉም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የዕርድ አገልግሎት የሚሰጡ ነጋዴዎች ዶሮዎቻቸውን እንደልብ ለመሸጥ ስለሚያችላቸውና የመወዳደሪያ አቅም ስላስገኘላቸው ነው፡፡

  በፋሲካ በዓል ዋዜማ ቀናት እንደታዘብነው ደህና ሥጋ ያለው ዶሮ ከ180 ብር በላይ ይሸጣል፡፡ የገበያው ቀናት፣ ከዕለተ ፋሲካ ቀደም ብለው የነበሩት ዓርብና ቅዳሜ ሲሆኑ በእነዚህ ቀናት የዶሮ ዋጋ በድርድር የሚወሰን ቢሆንም፣ ነጋዴዎቹን ባነጋገርበት ቀን (ረቡዕ መጋቢት 30 ቀን 2007 ዓ.ም.) የነበረው ዋጋ ውድ የሚባል እንደሆነ ታዝበናል፡፡ ነጋዴዎቹም ይስማማሉ፡፡ የዶሮ ዋጋ እስከ 200 ብር የደረሰው ገበሬው ገና ወደ ገበያ ማምጣት ስላልጀመረ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ በዓሉ በተቃረበ ቁጥር ቀድሞ የነበረው ዋጋ እየጨመረ ሲመጣም ታይቷል፡፡ በአንድ ቀን ብቻ 30 ብር ድረስ መጨመሩን አቶ ድሉ ገልጸዋል፡፡

  ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተጠቃሚዎች ሁለት ዓይነት አመለካከት አንፀባርቀዋል፡፡ ወይዘሮ ኃያልነሽ አድማሱ መካኒሳ አካባቢ የሚኖሩ የዘወትር ደንበኛ ናቸው፡፡ ኮንዶሚኒየም ተከራይተው የሚኖሩ በመሆናቸው ዶሮ ታርዶ፣ ላባው ተገፎ ወደ ቤት መውሰዳቸው እፎታ እንደሆነላቸው ይገልጻሉ፡፡ አራጅ ፍለጋ መባዘኑ፣ ቆሻሻ አወጋገዱ፣ ውኃ ማፍላቱ የመሳሰለውን ጫና እንዳስቀረላቸው በመግለጽ ዶሮ  ነጋዴዎቹ የሚሰጡትን አገልግሎ በአወንታ ይገልጹታል፡፡

  ያለፉትን ሁለት ወራት በጾም ያሳለፉትና ዕድሜ የተቸራቸው ወይዘሮ አረጋሽ ተክሉ በአንፃሩ ይጠየፉታል፡፡ በእሳቸው አገላለጽ የአራጁ እምነትና ተያያዥ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ያለው አቋም ተደማምረውበት የገዙትን ዶሮ እዚያው አሳርደው መውሰዱን ፈጽሞ አይፈልጉትም፡፡ ‹‹ቢቻል ቄስ ባርኮት ካልተገኘም የሚጾም ሰው ካላረደልኝ በቀር ምን መጣብኝ ልጄ?›› ያሉት ወይዘሮ አረጋሽ፣ ከዚህም በላይ የዶሮ ደንቡ በቤት ሲታረድና ደሙ ሲረጭ እንደሆነ ይሞግታሉ፡፡

  ለወይዘሮ ኃያልነሽና መሰሎቿ ግን አማርጠው ከነነብሱ የገዙትን ዶሮ፣ ፊት ለፊታቸው አሳርደው፣ ሲያስፈልግም በብልቱ አስገንጥለው መግዛታቸውን በጥሩነቱ ይገልጹታል፡፡ ከዚህ ባሻገር በየሱፐር ማርኬቱ ማን ይረደው የማያውቁትን ዶሮም ገዝተው አብስለው መመገብ የዘመናዊ አኗኗር ሥርዓት ተጋሪዎች ዘይቤ በመሆኑ የሚያስጨንቃቸው ነገር የለም፡፡  

   

   

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች