Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዝንቅበዓላትን ተከትለው በመዲናችን ዋና ዋና ጎዳናዎች የሚዘጋጁ ባዛሮች የእግረኛ መንገዶችን ሲያጨናንቁ ይስተዋላል...

በዓላትን ተከትለው በመዲናችን ዋና ዋና ጎዳናዎች የሚዘጋጁ ባዛሮች የእግረኛ መንገዶችን ሲያጨናንቁ ይስተዋላል (አራት ኪሎ አካባቢ)

ቀን:

ዝሆንና አውራ ዶሮ

አንድ ዝሆንና አንድ አውራ ዶሮ ነበሩ፡፡ ዝሆኑም ሁልጊዜ በትልቅነቱና በጥንካሬው በመኩራራት ተወዳጅ ለመሆን ይሞክር ነበር፡፡ ሆኖም ምንም እንኳን አውራ ዶሮው በመጠን ትንሽ ቢሆንም በጣም ብልጥ ነበር፡፡

ታዲያ አንድ ቀን ዝሆኑን “አንተ ትልቅ ብትሆንም ምንም ማለት አይደለም፡፡ አንጎል አንጂ መጠን ምንም አያደርግም፡፡” አለው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ዝሆኑ ግን “አይደለም አንተ ደደብና ትንሽ እንስሳ ነህ፡፡ ከእኔ ጋር ልትወዳደርም ሆነ ልትስተካከል አትችልም፡፡” አለው፡፡

ዶሮውም “እንግዲያው እንወዳደርና ብዙ ውኃ ማን መጠጣት እንደሚችል እንመልከት፡፡” አለው፡፡

ስለዚህ ወደ አንድ ትልቅ ወንዝ ምናልባትም ወደ ባሮ ወይም አኮቦ በመሔድ ሌሎች እንስሳት ሁሉ አንዲፈርዱ ጠየቋቸው፡፡

ውድድሩም ሲጀመር ዶሮው ምንቃሩን ዝሆኑም ኩምቢውን ውኃው ውስጥ ከተው መጠጣት ጀመሩ፡፡ ሆኖም ዶሮው ግን እየጠጣ አልነበረም፡፡ ምንቃሩን ብቻ ውኃው ውስጥ አድርጎ እየከፈተ ይዘጋው ነበር፡፡ ዝሆኑ ግን ውኃውን ጠጥቶ ጠጥቶ ሆዱ አበጠ፡፡

በመጨረሻም በጠጣው ውኃ ብዛት ፈንድቶ ሞተ፡፡

ይህ የሚያሳየው መጠን ሳይሆን ብልጠት መሻሉን ነው፡፡

  • (በኒያል ጋትች የተተረከ የኑዌር ተረት ከኢትዮጵያ ተረቶች ገጽ)

**************

ሕይወት ቅኔ

ሕይወት ማለቅ ቅኔ

ለእኔ ማለት የእኔ፡፡

 ወይም ሕይወት ሞፎ

የእኔነት ቀፎ፡፡

በራሴ ውስጥ ያለ ያገር ፍቅር ወኔ

ባህል ኪነ ጥበብ ማህሌተ ቅኔ፡፡

በመብላት … በማግሳት … ሕይወት ከታመነ

ጓዱ በዓለም የለም አካሉ ካልሆነ፡፡

ካለዚያም መቀመጥ … መወዘፍ በሶፋ

ከሆነ የሕይወት እሷነት ይጥፋ፡፡

ወይም እኔነቴ በእኔ ዘንድ አይኖርም

ወደ ኋላ አይሔድም … ወይ ወደላይ አይበርም

እሱም … እኔም … ግጥሜም ..

     እንድንቆይ ባንድ ዕድሜ

እኔ ግጥም ልጻፍ … ታግሎ ይኑር ግጥሜ

ካሊያ ግን አልገፋም ኑሮን በዝም ትርጉም

ኑሮ እራሷ ትሁን የረከበች እርጉም

ሕይወት ከነምኗ . . .

ትበል እልም … ድርግም

  • አያልነህ ሙላቱ ‹‹ከድጡ ወደ ማጡ! የግዛተ – ደርግ ግጥሞቼ ፲፱፻፷፰-፹፪›› (2004)

***************

ወርቃማው ሕግ

ክርስትና

እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና፡፡ (ማቴ 7÷12)

እስልምና

ለራሳችሁ የምትመኙትን ለሌሎችም እንዲሆን እስካልተመኛችሁ ድረስ በትክክል አላመናችሁም፡፡ (የነብዩ መሐመድ ተግባራትና ንግግሮች)

የአይሁዶች እምነት

አንተ የምትጠላውን ነገር በባልጀራህ ላይ አታድርግ ይህ ነው እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ሕግ ሲጠቃለል፡፡ (ሒላል ታልሙድ ሻባት 31)

የባሃኢ እምነት

በአንተ ላይ ሊጫንብህ የማትፈልገውን በሌላ ላይ አታድርግ በራስህም ላይ እንዲደርስብህ የማትሻውን ለማንም አትመኝ፡፡ (ባሀኡላህ)

ቡዲሂዝም

ራስህን የሚጎዳ የሚመስልህን ነገር በሌሎች ላይ አታድርግ፡፡

ሒንዱዝም

አንተ ላይ ቢደረግ የሚያስከፋህ ከሆነ አንተም በሌሎች አታድርግ የተግባር ሁሉ ማጠቃለያ ይህ ነውና፡፡ (ማኅበራታ 51517)

ጃኒዝም

ማንም ሰው ለራሱ እንዲደረግለት የሚሻውን እርሱም እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ላሉ ፍጡራን ሁሉ ያድርግ፡፡ (ማሃቪራ ሱትራክሪታንጋ)

ሲኪሂዝም

ለማንም ባይተዋር አይደለሁም ማንም ለእኔ ባይተዋር አይደለም የሁሉም ወዳጅ ነኝ፡፡ (ጉሩ ግራንትዝ ሳሂብ ፒጂ.1299)

ዩኒታሪያኒዝም

ሁላችንም አካል የሆነበትን የፍጥረታት አንድነትና ትስስር በጽኑ እንደግፋለን እንዲሁም ልዩ አክብሮት እንዲሰጠው እንተጋለን፡፡ (የዩኒታሪያን መርሆ)

ታኦዝም

ጎረቤትህ ሲያተርፍ አንተ እንዳገኘህ ቁጠር ጎረቤትህ ሲከስር አንተ እንዳጣህ አድርገህ ውሰድ፡፡ (ቲአይ ሻንካ ካንዩንግ ፒዮን 213-218)

ኮንፉሺያኒዝም

የመልካም ሥነ ምግባር መሠረት ማጠቃለያ የሆነ አንድ ቃል ነው እሱም ሩህሩህ መሆን በአንተ ላይ ሊደረግ የማትፈልገውን በለሎች ላይ አታድርግ፡፡ (ኮንፍሺየስ አናሌክትስ 15.23)

ዞሮአስትሬይኒዝም

አንተን የሚጎዳ ነገር ሁሉ በሌሎች ላይ አታድርግ፡፡ (ሻያስት-ና-ሻያስት 13.29)

ኔቲቭ ስፒሪቹአሊቲ

የኛ ሕልውና የሚረጋገጠው የምድራችን ተፈጥሮ ይዞታ ሲጠበቅ ነው፡፡ (ቺፍ ዳን ጆርጅ)

  • ኢንተርፌዝ ፒስ ቢዩልዲንግ ኢንሽየቲቭ

**************

የሞትና አጋፋሪ እንደሻው ጥንስስ

ተረት ሰፈር ስንኖር ሴቶቹ እማሆይ ጣዲቄ የሚሏቸው ባልቴት ነበሩ፡፡ “ያጋፋሪ እንደሻው” ምንጭ እሳቸው ናቸው፣ እና በበኩላቸው ከተራው ሰው ለየት ያሉ ናቸው፣ እንደ ገፀ-ባህሪያችን፡፡ ገና ስንነሳ፣ እማሆይ ቢሉዋቸውም መነኩሲት አይደሉም፣ ለማኝ ናቸው፡፡ ነብሳቸው እንደ አጋፋሪነታቸው ተጓዥ በመሆኗ፣ ለልመና ጧት (ለማኝ ሳያራ ሊሆን ይችላል) ኦቶቡስ ተሳፍረው እስከ መጨረሻ ፌርማታ ተጉዘው ይወርዳሉ፡፡

ቀኑን ሲለምኑ ውለው (ትዕዛዙ “በግንባርሽ ላብ ትበያለሽ” ስለሆነባቸው) በኦቶቡሳቸው ወደ ተረት ሰፈራችን ይመለሳሉ፡፡ ሴቶች በተለያየ አጋጣሚ ለቡና ይጠሩዋቸዋል (ባልተቤቴ ስትልክባቸው “ጣት የምታስቆረጥም” ቁርስ ታዘጋጃለች)

ጀበናም ሲወርድ እማሆይ ጣዲቄ የራሳቸውን ሲኒ አውጥተው (ከየት እንዳወጡት አላየሁም) እጃቸውን ሲዘረጉላት፣ ካዳሚዋ ረኮቦቱ ላይ ከመሰሎቹ ሲኒዎች ትደረድረዋለች…

…. አንድ ከሰዓት በኋላ፣ እማሆይ ጣዲቄ ከሚስቴ ጋር ከቀብር ተመልሰው፣ እጣኑ እየጤሰ ቡናው እየተጠጣ፣ ለረዥም ጊዜ ሳውቃት ሞት በጭራሽ የማያስፈራት ሚስቴ

“ውይ ሲያሳዝኑ መሞት እንደዚያ ሲፈሩ መሞታቸው!” ስትል በቁጭት

“ምን ለሳቸው ታዝኛለሽ አሉ እማሆይ “ቀኛዝማች ሳህለ ጆርጊስ አሉልሽ አይደለም?”

(ይኸውላችሁ እንግዲህ አንባብያን ሆይ! አጋፋሪን ፃፋቸው ሲለኝ ይመስላል፣ በዚያች ደቂቃ “ጆሮዬ ቆመ” – ባህላዊ ጥቅሶቼን እያስተዋላችሁልኝ አደራ)

“ቀኛዝማች ሳህለ ጆርጊስ?” በጉጉት እማሆይ ጣዲቄን ጠየቅኳቸው

“ይኸውላችሁ፣ ዛሬ እዚህ ሊሴ ፈረንሳይ ተማሪ ቤት ያለበት ቦታ፣ በዘበኑ ዙሪያውን የቀኛዝማች ሳህለ ጆርጊስ ቤተሰቦች ነበረ፡፡ እና እሳቸው ከዘመዶቻቸው ሁሉ የተለየ ሞትን የመፍራት አባዜ ተጠናውቷቸው ነበር

“የትም ሄደው ይመለሱ፣ ከበቅሎዋቸው ሳይወርዱ አሽከሮቹን

“ሰፈር ደህና ነው?” ይሉዋቸዋል…”

…እንግዲህ ወጣት ደራሲያን “ሞትና አጋፋሪ እንደሻው” እማሆይ ጣዲቄ እንደነገሩኝ ሆኖ (ያውም ቃል በቃል)

የመጀመሪያዋ አረፍተ ነገር ብቻ የኔ ነች (ለትረካው እንዲያመች) ከዚያ የሚቀጥሉት ምዕራፎች (“ቆሪጥና አጋፋሪ…”) እማሆይ የነገሩኝ እንደ እርሾ እየሆነ፣ እኔ እያቦካሁ እየጋገርኩ፣ ይህ መድበል እንደ አገልግል ተከድኖ ተለጉሞ ደርሷችኋል፣ ለሚቀጥለው የራሳችሁ የፈጠራ ጉዞ እንደ ማደፋፈሪያ እንደ “አይዞን!” ሊሆናችሁ ይችላል በሚል ተስፋ፣ በሄዳችሁበት ይቅናችሁ!

  • ስብሐት ለአብ ገብረ እግዚአብሔር

ለ “አምስት ስድስት ሰባት” አጭር ልቦለዱ የፃፈው መግቢያ (2004)

**********

 

የኢትዮጵያ ምስክሯ ፈረንጅ!

‹‹ዱሮም አንተ ምግብ የት ታውቃለህ? ይሄኮ በአውሮፓ በጣም ተወዳጅ ምግብ ነው›› የሚባባሉ ሰዎች ሰምቼ አውቃለሁ፡፡ በርካታ ድርጅቶችም ‹‹ይህ ምርታችን በአውሮፓና በአሜሪካ የማንትሴን ድርጅት ሽልማት ያገኘ ነው›› በማለት ምርቶቻቸውን ብንገዛ እንደሚበጀን ሲነግሩን የምንሰማው ነው፡፡ እንትን የሚባለው ዕቃ ‹‹የስልጡኖች ምርጫ ነው›› በማለት ከኋላ ቀርነታችን እንድንላቀቅ የሚገፋፉንም ማስታወቂያዎች አሉ፡፡ ‹‹ጣፋጭነቱ በአውሮፓ የተመሰከረለት›› ኬክ ቢገጥመንም ታዝበን ዝም ከማለት በላይ ለአንድ ቂጣ የሚሰጠውን አርባ ስም ስናይ እናዝን ይሆናል ፒሳን ልብ በሉ፡፡

ይህ ልማድ ወደ ግለሰቦች ሕይወት ታሪክም እየገባ ይመስላል፡፡ በዚህ ዕውቀታቸው ወይም ግኝታቸው የአሜሪካን ማንትስ ዩኒቨርስቲ ሽልማት ያገኙ ናቸው፡፡ እንትን የሚባለው አካዳሚ ወይም አሶሴሽን ሸልሟቸዋል፤ የክብር ስፍራም ሰጥቶአቸዋል፡፡ የመጀመሪይው ጥቁር፣ የመጀመሪያው አፍሪካዊ፣ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ እየተባለም ብዙ ነገር መባላቸው ይሰማል፡፡ አንዳንድ ምሁራንም እንዲህ ነኝ እንዲህ የተባልኩ ነኝ ሲሉን እንሰማቸዋለን፡፡

ይህ ሁሉ ይሁን፡፡ አገራችን ከእነዚህ ሰዎች ያገኘችው ምንም ነገር የሌለ ከሆነ ታዲያ ምን ይጠበስ? ማለት ተገቢም ላይሆን የችላል፡፡ ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ፈረንጅ የሾመው ያዳነቀውን ሁሉ መቀበልና ማድነቅ አለብን? ወይስ ቢቻል ለአገሩ የፈየደውን እሱ ካልሆነ የተደነቀበትን ነገር መርምረን ማድነቅ አለብን? ፈረንጆቹ ‹‹ጥቁር ይህን ያህል ካሰበ መች አነሰው?›› እያሉ የማርክና የማዕረግ ቁልል እንደሚያሸክሙ አልፎ አልፎ እንሰማለን፡፡ ደግሞ ደርሰውስ እዚህ ስሙንም እንኳ በቅጡ የማናውቀውን ድርጅት የአውሮፓ ተሸላሚዎች ብለው ሾመው ሲልኩብን ምን አስበው ነው?

ይልቅ የራሳችንን ማድነቂያ መስፈርት ብናበጅ አይሻል ይሆን? እኛ ገዝተን የምንጠቀመውን ምርት ጥራት ማረጋገጥ ካልቻልን ‹‹ጥራቱ በመላ ኢትዮጵያ የተረጋገጠ›› ምርት የሚል ማስታወቂያ መስማት ካልቻልን በእጅ አዙር ቅኝ ወደመሆን ማምራታችን እንዳይሆን፡፡ ይህ ብስኩት በአሜሪካ የተወደደ ነው ስለተባለ ብቻ የጣዕም ባለቤትነታችንን አሳልፈን በሌላው ስሜት ማጣጣም ከወደደን አደጋ ነው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ይህን ፕሮጀክት ‹‹ሰውጭ አገር ኤክስፐርቶች ነው ያስጠናነው›› እያሉ ሲፎክሩ ዝም ብለን ከሰማን ነገሩ እያሰጋ ሊሄድ ይችላል፡፡ በራስ ማፈር በገዛ ምሁርና ዜጋ አለመተማመንንም ያመጣል፡፡ ካለበለዚያ ነገ ይህች ኢትዮጵያዊት ኮረዳ በማንትስ አገር ውበቷ የተመሰከረላት ናትና እንዳታመልጣችሁ ማለትን እንዳያመጣ ያሰጋል፡፡

  • (ሪፖርተር መጽሔት ጥር 1992)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...