Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የምግብ ዋስትናና ሥርዓተ ምግብ በአፍሪካና በኢትዮጵያ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የአፍሪካ ኢኮኖሚ ዕድገት፣ የምግብ ዋስትናና የሥርዓተ ምግብ መስኮች ውጤታማ ጉዞ እንዲያደርጉ በማሰብ፣ የአፍሪካ መሪዎች ሁሉን አቀፍ የአፍሪካ የግብርና ልማት ፕሮግራም (በአጽህሮተ ቃሉ ካድፕ) እየተባለ የሚጠራውን መርኃ ግብር በመላው አፍሪካ አገሮች ለመተግበር የተስማሙት፣ እ.ኤ.አ. በ2003 ነበር፡፡

   የፕሮግራሙ አፈጻጸም ወጣ ገባ ለመሆን አልፎ ስምምነት የፈጸሙ አገሮች በተስማሙበት ልክ ፕሮግራሙን ለመተግበር የነበራቸው ተነሳሽነት ላይ ጥያቄ ሲነሳ ቢቆይም፣ የዓለም የምግብ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት ዓመታዊ ሪፖርት ግን ፕሮግራሙ ለአፍሪካ አገሮች ያስገኘውን አወንታዊ ውጤት አሳይቷል፡፡

  ከጥቂት ቀናት በፊት በአዲስ አበባ፣ ሲኤምሲ አካባቢ በሚገኘው የዓለም የቁም እንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ቅጥር ግቢ ውስጥ በተካሔደ ሥነ ሥርዓት ላይ ሪፖርቱ ይፋ ሲደረግ፣ ፖሊሲ አውጪዎችና የምግብ ዋስትና ባለሙያዎች ውይይት አድርገውበታል፡፡ 

  በሪፖርቱ መሠረት ሁሉን አቀፍ አፍሪካ የግብርና ልማት ፕሮግራም መተግበር ከጀመረ በኋላ ተገኙ ከተባሉት ለውጦች ውስጥ፣ የመላው አፍሪካ የግብርና ዘርፍ ዕድገት ጠንካራ እንደነበር ያትታል፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ 2012 በነበሩት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ የአፍሪካ ግብርና ዘርፍ በ5.1 ከመቶ ዕድገት ሲያዝመገዝብ ቆይቷል፡፡ እርግጥ ይህ ዕድገት ግን ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም ከመምጣቱ ቀደም ብሎ በነበሩት ዓመታት ይዘመገብ ከነበረው ዕድገት አኳያ አነስተኛ ሆኖ እንደሚገኝ ሪፖርቱ ያምናል፡፡ በሁሉን አቀፍ የአፍሪካ ግብርና ልማት ፕሮግራም በያመቱ ይመዘገባል የተባለው የግብርና ዕድገነት ስድስት ከመቶ ነበር፡፡ ከ30 በላይ በሚቆጠሩ አገሮች ዘንድ ይህ ግብ ሊተገበር ሳይችል ቀርቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር የአፍሪካ መንግሥታት ከአጠቃላይ የመንግሥት ወጪያቸው ውስጥ እስከ አሥር በመቶ ለግብርና ያውላሉ የሚል ስምምነት ተደርጎ የነበረ ሲሆን፣ ይህም በበርካታ አገሮች ዘንድ ሳይተገበር ቀርቶ፣ የፕሮግራሙ መተግበሪያ አሥር ዓመታትም ተገባደዋል፡፡

   ይህም ሲባል ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ ቡርኪና ፋሶ፣ ጋና፣ ጊኒ፣ ማዳጋስካር፣ ማሊና ማላዊን የመሳሰሉት ሰባት አገሮች ከስድስት ከመቶ በላይ ዓመታዊ የግብርና ዕድገት ያስመዘገቡ አገሮች መኖራቸውን፣ የኢንስቲትዩቱ ዓመታዊ የዓለም ምግብ ፖሊሲ ሪፖርት አስፍሯል፡፡ ሰባቱ አገሮች በግብርና መስክ ያስመዘግቡ ዘንድ ይጠበቅባቸው ከነበረው ስድስት በመቶ በሻገር፣ ለግብርና ዘርፍ የመደቡት የመንግሥት ወጪያቸውም በአማካይ እስከ 7.7 ከመቶ ሊያድግ መቻሉም ተረጋግጧል፡፡ ይህ ዕድገት ተመዝግቦ የነበረው ፕሮግራሙ ይፋ ከተደረገበት እ.ኤ.አ. ከ2003 እስከ 2008 በነበሩት አምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ነበር፡፡ ፕሮግራሙ ይፋ ከሆነ ከአምስት ዓመታት በኋላ ማለትም እ.ኤ.አ. በ2008 የተከሰተው የዓለም የፋይናንስ ቀውስን ተከትሎም የተነሳው የምግብ ቀውስ የአፍሪካ ግብርና ዕድገት ላይ ተፅዕኖ እንደነበረው ታይቷል፡፡ አገሮች ማውጣት ከነበረባቸው አሥር ከመቶ ዓመታዊ የግብርና በጀት ውስጥ በርካቶቹ ሲቀንሱ፣ ጥሩ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ የነበሩትም ቢሆኑ እየቀነሱ መምጣታቸው ተረጋግጧል፡፡ እስካለፉት ሁለት ዓመታትም ከጠቅላላ የመንግሥት በጀት ውስጥ ለግብርና ይመደብ የነበረው የ3.7 ከመቶ በጀትም ይብሱን እየቀነሰ መምጣቱን የዓለም የምግብ ፖሊሲ ሪፖርት አትቷል፡፡

  አፍሪካውያኑ ያቀዱትን ፕሮግራም ቢያንስ በበጀት አመዳደብ ላይ ባሰቡት መጠን ለማሳካት የሚያስችላቸው አጋጣሚ ግን ተፈጥሮላቸው ነበር፡፡ ይህም ከውጭ የሚገባው የኢንቨስትመንት መጠን ነው፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት ወደ አፍሪካ አገሮች የገባው የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን 52 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ተመዝግቧል፡፡ ካቻምና የተመዘገበው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን ከ56 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱ ሲታወቅ፣ ዓምና ወደ አፍሪካ የገባው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን ከ60 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ምንም እንኳ ከውጭ የሚገባው ኢንቨስትመንት በዚህ መጠን እየጨመረ ቢመጣም (በአብዛኛው በተፈጥሮ ሀብትና በጥሬ ዕቃ የበለፀጉ አገሮች ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ቢታይም፣ አነስተኛ የተፈጥሮ ሀብት ባላቸው አገሮች ዘንድም ቀላል የማይባል የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን መመዝገቡን ልብ ይሏል) ድህነትና ረሃብ በአፍሪካ እየነሰ ያለበት ፍጥነት አዝጋሚ እንደሆነ ይገኛል ተብሏል፡፡ በመላው አፍሪካ በቀን ከ1.25 ዶላር በታች ገቢ በማግኘት ከድህነት ወለል በታች ከሚኖረው 45 ከመቶ ሕዝብ ውስጥ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የታየው መሻሻል እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የተመጣጠነ ምግብ የማግኘት፣ የረሃብና የድህነት መጠን ቅነሳ ዕርምጃዎች የተንቀራፈፉ ሆነው መገኘታቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ 

  አፍሪካ ከምታገኘው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን ባሻገር ከዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላት ድርሻ አነስተኛ መሆንም የድህነት ቅነሳውንም ሆነ የሥርዓተ ምግብ መሻሻሎች ላይ ተፅዕኖ እንዳላቸው ይታሰባል፡፡ ከአፍሪካ የሚላኩ ምርቶች መጠን በአራት እጥፍ መጨመራቸው ቢታወቅም፣ የገቢ ንግድ መጠኑ ከ2.5 እጥፍ በላይ በፍጥነት እያደገ በመሆኑ፣ የግብርና ውጤቶች ንግድ ላይ የሚታየውን የንግድ ጉድለት ማለትም ወደ ውጭ ከሚላኩት በላይ ወደ አፍሪካ የሚገቡት የግብርና ምርቶች ከፍተኛ መሆን ለሚታየው አዝጋሚ የድህነት ቅነሳና የምግብ ዋስትና ማሻሻል ዕርምጃዎችን ይበልጥ አዝጋሚ አድርገዋል፡፡

  ላለፉት አሥር ዓመታት ሲተገበር የቆየው ሁሉን አቀፍ የአፍሪካ የግብርና ልማት ፕሮግራም በጣት በሚቆጠሩ አገሮች ዘንድ ስኬታማ መሆኑን ተከትሎ፣ ዓምና በማላቡ በተደረገ የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ፣ የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ማስመዝገብ የተሳነው የአሥር ዓመቱ ሁሉን አቀፍ የአፍሪካ የግብርና ልማት ፕሮግራም ለቀጣዮቹ ዓመታት እንደገና እንዲተገበር ስምምነት አድርገዋል፡፡

  በስምምነታቸው መሠረት ከሚቀጠቀሱት መካከል በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ረሃብን ከአፍሪካ ለማጥፋት፣ የመቀንጨር መጠንን ወደ አሥር ከመቶ ዝቅ ለማድረግ፣ ከአምስት ዓመት በታች የሚገኙ ሕፃናት መጠንን ወደ አምስት ከመቶ ዝቅ ለማድረግ መሥራት ከሚጠቀሱት መካከል ሲሆኑ፣ ግብርና ከሃምሳ በመቶ በላይ የድህነት ቅነሳ ላይ ሚና እንዲኖረውና ዓመታዊ የግብርና ዘርፍ ዕድገትም ከስድስት በመቶ በታች እንዳይሆን መስማማታቸውና በማላቡ ስምምነት ውስጥ የሰፈረ ሰነድ ሆኖ መመዝገቡም ይታወሳል፡፡

  ኢትዮጵያና ካድፕ

  ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የአፍሪካ ግብርና ልማት ግቦችን ካሳኩት አገሮች ተርታ ተሰላፊ መሆኗ ቢመሰከርም፣ በርካታ ቀዳዳዎች ይታያሉ፡፡ በቅርቡ ተካሒዶ በነበረው ዓመታዊ የሥርዓተ ምግብ ግምገማ ላይ እንደተገለጸው ከሆነ ግን አገሪቱ ብዙ መጓዝ ይጠበቅባታል፡፡ የአገሪቱ ባለሙያዎች እንዳብራሩት ከሆነ 44 ከመቶ የአገሪቱ ሕፃናት በዕድሜያቸው ልክ በአካል ማደግ ከሚገባቸው እጅግ ዝቅተኛ በሆነ መጠን እያደጉ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሕፃናቱ የተመጣጠነ፣ የንጥረ ነገር ይዞታው የተሟላ ሥርዓተ ምግብ በአግባቡ ስለማያገኙ እንደሆነ የኢትዮጵያ የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያዎች የሚስማሙበት ነው፡፡

  በእነዚህ ችግሮች ሳቢያ በአገሪቱ የሚታየው የመቀንጨር ችግር 44 ከመቶ ላይ ይገኛል፡፡ እርግጥ ይህ አኃዝ ቀደም ባሉት ጊዜያት 58 ከመቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የአገሪቱን ሕፃናት የመቀንጨር ችግር ወደ 30 ከመቶ ለማውረድ መንግሥት አገር አቀፍ የሥርዓተ ምግብ ፕሮግራሞችን እየተገበረ እንደሚገኝም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

  በአንፃሩ የአገሪቱ የግብርና ዘርፍ የኢኮኖሚው ወሳኝ ክፍል ሆኖ ከአገልግሎትና ከኢንዱስትሪ ዘርፎች በመከተል ዓመታዊ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡ በአንፃሩ በኢኮኖሚው ላይ ያለው ድርሻ ግን ከፍተኛው ሆኖ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያና መሰሎቿ የካድፕ ስምምነት ያሟሉ አገሮች ለግብርና መስክ ቅድሚያ በመስጠት ያስመዘገቡትን ዕድገት እንዲያስቀጥሉ የሚመክረው፣ ለአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት (ኔፓድ) ያለፉት አሥር ዓመታት የካድፕ አፈጻጸም ውጤቶችን በገመገመበት ሪፖርቱ ነበር፡፡

  በሌላ በኩል በአፍሪካ አገሮች ዘንድ መደረግ የማይገባቸው ካላቸው አብነቶች መካከል፣ አፍሪካውያኑ ከዓለም የምግብ ተመጽዋችነት እንዲታቀቡ፣ ለም መሬቶቻቸውን ለነዳጅ ሲሉ በመሸጥ ሕዝባቸውን ከማጎሳቆል እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡ ኔፓድ በስመ የግብርና ኢንቨስትመንት ስም መሬት ጠብ የማይሉ የይምሰል አሠራሮችን እንዲያቆሙ አፍሪካውያኑን ጠይቋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ የአግሪ ቢዝነስ ሥራዎችና የሥራ ፈጠራዎች ላይ በመሳተፍ ከአገር ውስጥ ባሻገር በዓለም ገበያዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ የሚችሉ ኢንቨስተሮችን ለማፍራት የአፍሪካ መንግሥታት ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች