Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምአልሸባብ ቁም ስቅሏን የሚያሳያት ኬንያ

አልሸባብ ቁም ስቅሏን የሚያሳያት ኬንያ

ቀን:

በአፍሪካ በኢኮኖሚ ዕድገታቸው ከሚጠቀሱ አገሮች ከቀዳሚዎቹ ተርታ የምትሠለፈውና በቱሪዝም መስህቧ የምትገለጸው ኬንያ፣ የአልሸባብ ጥቃት ሰለባ መሆን ከጀመረች ከአራት ዓመታት በላይ አስቆጥራለች፡፡ ለወትሮው በጐብኚዎች ይጨናነቁ የነበሩት ሞምባሳ፣ ማሊንዲ እንዲሁም የተለያዩ ፓርኮቿ አሁን የጐብኚዎች ቁጥር ቀንሶባቸዋል፡፡ በሆቴልና በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ተስፋ ቆርጠዋል፡፡ የቱሪስት መዳረሻ በሆኑ ሆቴሎች የሚሠሩ ኬንያውያን ባለሙያዎች ተስፋ በቆረጠ ስሜት ያለሥራ መቀመጣቸው ይነገራል፡፡ ለሥራቸው እንቅፋት፣ ለአገራቸው የሽብር ጥቃት ጦስ የሆነው አልሸባብ ብቻ ሳይሆን፣ በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ አመለካከት በጥልቅ መከፋፈል፣ በዘር ተቧድኖ ፖለቲካውን ለመምራት ወይም ለመጣል የሚደረገው ሽኩቻ እንደሆነም ኬንያውያን ይገልጻሉ፡፡ አንዳንዶች ‹‹ችግሩ አልሸባብ ሳይሆን፣ የራሳችን ዜጐች ናቸው፤›› ሲሉም በተለያዩ ሚዲያዎች ተደምጠዋል፡፡

አልሸባብ በኬንያ ያደረሳቸው ጥቃቶች

ኬንያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአልሸባብ ጥቃት የደረሰባት እ.ኤ.አ. በ2011 ጥቅምት ወር ነው፡፡ በወቅቱ በናይሮቢ በአንድ ቀን ውስጥ በደረሱ ተከታታይ ሁለት ፍንዳታዎች፣ በመጀመሪያው አንድ ሰው ሞቶ 20 ሲቆስሉ፣ በሁለተኛው ጥቃት ደግሞ 59 ወንዶችና 10 ሴቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ አምስት መሞታቸውም ታውቋል፡፡ ኬንያ በዚህ ወቅት ከዘጠኝ ያላነሱ የሽብር ጥቃቶች ያስተናገደችው፣ አሜሪካ ሽብርተኞችን ባስጠነቀቀች ማግሥት ነው፡፡ የኬንያ መንግሥት አሸባሪዎችን ለመያዝ ባደረገው ጥረት ከሽብር ጥቃት ጋር ግንኙነት አለው ያለውን ኬንያዊ ይዞ የዕድሜ ልክ እስራት ወስኖበታል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እ.ኤ.አ. በ2012 ከጥር እስከ ሰኔ ባሉት ጊዜያት በኬንያ የሚገኙ የስደተኞች ካምፖችን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች ኬንያውያን የሽብር ጥቃት ሰለባ ሆነዋል፡፡ በናይሮቢ፣ በካሊፊ፣ በሞምባሳና በሌሎችም ሥፍራዎች በተጠመዱ ቦምቦችና በተተኮሱ ጥይቶች ከአሥር በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከ100 በላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በዚሁ ዓመት ከሐምሌ እስከ ታኅሳስ ባሉት ጊዜያት በጋሪሳ አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ በተለያዩ ሥፍራዎች በደረሱ የአልሸባብ ጥቃቶች የፖሊስ አባላትና ሲቪሎች ተገድለዋል፡፡ በወቅቱ ለተፈጸመው የሽብር ጥቃት የኬንያ ፖሊስ አንድ ተጠርጣሪ ይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ተጠርጣሪው ከሽብር ጥቃቱ ጋር ግንኙነት ስላልነበረው በነፃ ተሰናብቷል፡፡

ኬንያ እ.ኤ.አ. በ2013 በደረሰባት የአልሸባብ የሽብር ጥቃት ከ15 ያላነሱ ዜጎቿ ሲሞቱባት ከ40 ያላነሱ ደግሞ ቆስለዋል፡፡ በጥቃቱ በተለይ የፖሊስ አባላት ሰለባ ሲሆኑ፣ ከሶማሊያ ድንበር 140 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘውና በአብዛኛው የኬንያ ሶማሊያውያን መኖሪያ የሆነው ጋሪሳ በርካታ ጥቃቶችን አስተናግዷል፡፡ ጋሪሳ፣ ዋጂር እንዲሁም ዳዳብ የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሥፍራዎች ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 ኬንያ አስደንጋጭና ዓለምን ያነጋገረ የሽብር ጥቃት ያስተናገደችበት ዓመትም ነበር፡፡ በናይሮቢ በሚገኘው የዌስትጌት የገበያ ማዕከል ብቻ 69 ሰዎች በአልሸባብ ታጣቂዎች ተገድለዋል፡፡ ከ75 በላይ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በወቅቱ የቅርብ ዘመዳቸውን በሞት የተነጠቁት የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ አሸባሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውለው ለፍርድ እንደሚያቀርቡ ቢያስታውቁም እስካሁን የተያዘም ሆነ የተፈረደበት አሸባሪ የለም፡፡

እ.ኤ.አ. 2014 ለኬንያ ሰላም የሰፈነበት ዓመት አልነበረም፡፡ ሕዝቦቿ እንደ ወትሮአቸው በሥጋት ተወጥረው ነው ያሳለፉት፡፡ አልሸባብ ክርስቲያኖችን እየነጠለ መግደሉም በይፋ የተነገረው በዚህ ወቅት ነበር፡፡ በዌስትጌት ጥቃት ወቅት ክርስቲያኖች ተነጥለው ስለመገደላቸው ከዓይን እማኞች የተሰማ ቢሆንም፣ በ2014 የሽብር ጥቃት ወቅት በይፋ ወጥቷል፡፡ በአውቶቡስ ላይ በተወረወረ ቦምብ፣ በመኪናዎች ላይ በተጠመዱ ቦምቦች እንዲሁም በተኩስ ልውውጥ ከ15 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ብዙዎች መቁሰላቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2011 እስከ 2014 በነበሩት ዓመታት ለደረሱ የአልሸባብ ጥቃቶች የኬንያ መንግሥት ይህ ነው የሚባል እስራት፣ ቅጣትም ሆነ የሞት ፍርድ ሲፈጽም አልተስተዋለም፡፡ ከሽብር ጥቃቱ ጋር ተያያዥነት አለው የተባለ ኬንያዊ የዕድሜ ልክ እስራት ሲፈረድበት በናይሮቢ የኢስሊ ነዋሪዎች የሆኑ ሁለት ግለሰቦችም  ተጠርጥረው ታስረዋል፡፡ በሞምባሳና በሌሎች አካባቢዎች ለደረሱ የሽብር ጥቃቶች መሣሪያ በቤት ውስጥ በማምረት፣ በማቀባበልና በማዘዋወር አጋዥ ነበሩ የተባሉ ከ60 የሚበልጡ አሸባሪዎችም ታስረዋል፡፡

የኬንያ መንግሥት የሽብር ጥቃትን በመከላከልም ሆነ በመመከት ደካማ ነው እየተባለ ይወቀሳል፡፡ የደካማነቱም ውጤት ኬንያውያንን የሽብር ጥቃት ሰለባ አድርጓል፡፡ ኢኮኖሚውንም እየገደለ ነው፡፡ በመሆኑም የኬንያ መንግሥት በሽብር መከላከሉ ረገድ ከአሜሪካ ጋር እንደሚሠራ፣ ከኢትዮጵያ ልምድ ወስዶ እንደሚተገብር አሳውቆ ነበር፡፡ ሆኖም ሽብርን እከላከላለሁ ያለውን ያህል አልተሳካለትም፡፡ ይልቁንም ዘግናኝና ዓለምን ያስደነገጠውን የሽብር ጥቃት ባለፈው ሳምንት አስተናግዷል፡፡

አልሸባብ እስካሁን በኬንያ ባደረሰው ጥቃት ከሆቴል፣ ከመዝናኛ ሥፍራዎች፣ ከመገበያያ ቦታዎችና መኪና ላይ ቦምብ ከማጥመድና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጥቃት ከመፈጸም ባለፈ ትምህርት ቤትን ዒላማ አድርጐ አያውቅም ነበር፡፡ ሆኖም ባለፈው ሳምንት ከሶማሊያ ድንበር 140 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ጋሪሳ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በፈጸመው ጥቃት፣ 148 ተማሪዎችና መምህራን እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ተገድለዋል፡፡ ከ70 ያላነሱም ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የደረሰው ጥቃት ሙስሊም ተማሪዎችን ዓላማ ያደረገ አልነበረም፡፡ ከዓይን እማኞች የሚወጡ መረጃዎች የሚያሳዩትም ሙስሊም ተማሪዎች አልተገደሉም፡፡ ከእነሱ ውጪ ግን ሴት፣ ወንድ፣ ተማሪ፣ መምህር ሳይባሉ ሁሉም የጥቃት ሰለባ ሆነዋል፡፡ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ጨምሮ እስላምና ክርስቲያኑ ድርጊቱን ቢያወግዙትም፣ አልሸባብ ጥቃቴን እቀጥላለሁ ሲል ዝቷል፡፡ የአሁኑን ጨምሮ ከዚህ በፊት ለደረሱ ጥቃቶችም ኃላፊነቱን እንደሚወስድ አሳውቋል፡፡

አልሸባብ ለምን ኬንያን ዒላማ አደረገ?

ላለፉት 20 ዓመታት መረጋጋት የተሳናት ሶማሊያ ለራሷም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ ሥጋት ሆናለች፡፡ ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሶማሊያ መንግሥት የተመሠረተ ቢሆንም፣ ሶማሊያን ማስተዳደር አለብኝ የሚለውና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው አልሸባብ በሶማሊያ ሰላምን አሳጥቷል፡፡ ለጐረቤት አገሮችም ሥጋት ሆኗል፡፡ በመሆኑም ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ ከኡጋንዳና ከሌሎችም አገሮች የተውጣጡ ወታደሮች በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በመሆን በሶማሊያ ሰላም ለማስፈን እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በሶማሊያ ይገኛሉ፡፡ በሶማሊያ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) አልሸባብ በሶማሊያ የነበረውን ጠንካራ ይዞታ አስለቅቋል፡፡ የአልሸባብን ተቀባይነት አሳጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሶማሊያውያን ቀድሞ ከነበራቸው የጦርነት ሥጋት በአንፃራዊ በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡ መንግሥትም ተመሥርቷል፡፡ ለዚህም አሚሶም ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይህ ያልተዋጠለት አልሸባብ የአሚሶም አባል አገሮች ወታደሮች ላይ በሶማሊያ ጥቃት በመሰንዘር፣ ከአገር ውጪ ደግሞ ሽብር በመፍጠር እንደሚንቀሳቀስ ዝቷል፡፡ ለዛቻው ማስፈጸሚያ ደግሞ ኬንያና ኬንያውያን ምቹ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ አልሸባብ በኬንያ የደኅንነት አካላትና ወታደሮች ቁጥጥር ሥር መዋል አልቻለም፡፡ ቀድሞውንም የጦርነትና የሽብር ጥቃት ልምድ ላልነበራት፣ የተጠናከረ የመከላከያ ሠራዊት አደረጃጀትና የደኅንነት ሥርዓት ላልዘረጋችው ኬንያ አልሸባብ ዱብ ዕዳም ነበር፡፡

አልሸባብ ከኬንያ ጋር ጦርነት መግጠሙን ይፋ ያደረገው የኬንያ ወታደሮች አሚሶምን በተቀላቀሉ ማግሥት ነበር፡፡ አሸባሪ ቡድኑ እ.ኤ.አ. በ2011 ባሰራጨው መግለጫ፣ ኬንያ ወታደሮቿን ከሶማሊያ ካላስወጣች የጦርነት ቀጣና እንደምትሆን ዝቶ ነበር፡፡ ኬንያውያን ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታን መምረጣቸውን ተከትሎም ‹‹ከሶማሊያ ጋር ጦርነት የገጠመን መንግሥት የመረጡ ሕዝቦች የሽብር ሰለባ ይሆናሉ፤›› ብሎም ነበር፡፡ የአልሸባብን ዛቻ ከቁብ ያልቆጠረው የኬንያ መንግሥት አሁን አመድ አፋሽ ሆኗል፡፡ አልሸባብ ጥቃት ባደረሰ ቁጥር የተወሰኑ ሥፍራዎችን ከማጥቃት ውጪ ጥቃት ሳያደርስ መመከት ተስኖታል፡፡ ለዚህም የደኅንነት አካላቱ በሙስና መዘፈቅ፣ ኅብረተሰቡ በጎሳ ተከፋፍሎ አሁን ላለው የፖለቲካ ሥርዓት አለመታመንና የወታደሩ ልምድ ማጣት በር መክፈታቸው ይነገራል፡፡

በሌላ በኩል አልሸባብ ኬንያውያንን ለሽብር ጥቃቱ እየመለመለና ገንዘብም እየከፈለ ነው፡፡ በቅርቡ አልሸባብ የለቀቀው ፊልም እንደሚያሳየውም፣ አልሸባብን የሚቀላቀሉ ሙስሊምና ሙስሊም ያልሆኑ ኬንያውያን ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ነው፡፡ የሶማሊያ ተወላጅ ያልሆኑና ሶማሊኛ የማይናገሩ ሆኖም የኬንያ ብሔራዊ ቋንቋ የሆነውን ኪስዋህሊ ብቻ የሚናገሩ ኬንያውያን አልሸባብን ተቀላቅለዋል ይባላል፡፡ ከክርስትናም ወደ እስልምና እየተለወጡ መሆኑ ይነገራል፡፡

ኬንያ ሽብርን በመከላከል ረገድ ምን ደረጃ ላይ ትገኛለች?

ኬንያ በተለይ እ.ኤ.አ. በ2013 በዌስትጌት የገበያ ማዕከል የደረሰባትን የሽብር ጥቃት ተከትሎ ዓለም አቀፍ እገዛ አግኝታለች፡፡ አሜሪካ በሽብር መከላከሉ ከጐኗ ቆማለች፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራትም መክራለች፡፡ የደኅንነት ክንፉን ለማጠናከር እየሠራችም ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ የወታደርና የደኅንነት አካላት ጥንካሬ ላይ ትገኛለች፡፡ ሆኖም የደኅንነት አካላት፣ ወታደሩ እንዲሁም ፖሊሶች ተቀናብረው አይሠሩም፡፡ ይህም ለሽብር ጥቃት ሰለባ አድርጓቸዋል፡፡

ኬንያ የሽብር ጥቃቱን ትወጣው ይሆን?

አልሸባብ በኬንያ እያደረሰው ያለው የሽብር ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምሯል፡፡ በተለይ ሙስሊም ያልሆኑት ላይ ማነጣጠሩ በአገሪቱ የሃይማኖት ጦርነት ያስነሳል የሚል ሥጋት አጭሯል፡፡ የኬንያ መንግሥት የሶማሊያ ስደተኞች ወደ ካምፕ እንዲገቡ አዟል፡፡ ይህም በሶማሊያውያን ተቀባይነትን አላገኘም፡፡ ከሶማሊያ ከአሥር ዓመታት በፊት የተሰደዱ ከ500 ሺሕ በላይ ሶማሊያውያን በኬንያ ይገኛሉ፡፡ ኬንያ ሶማሊያውያኑን ሥርዓት ባለው መንገድ የመመዝገብና ካምፕ የማስገባት ሥራ ይጠብቃታል፡፡ በሌላ በኩል በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የብሔርተኝነት ውጥረት ማርገብ፣ በጎሳ ላይ የተመሠረተውን የፖለቲካ ምኅዳር ማምከን ይጠበቅባታል እየተባለ ነው፡፡ የደኅንነት ክፍሏን ከሙስና ማፅዳትም ሌላው ከባዱ ሥራዋ ነው፡፡ ይህንን የቤት ሥራ መወጣት ከቻለች ኬንያ የአልሸባብን ጥቃት ታመክናለች፡፡ ለዚህም በተለይ በፖለቲካው ምክንያት የተከፋፈሉት ዜጐቿ ትልቁን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል ነው የሚባለው፡፡ ኬንያ አሁን በጋሪሳው ጥቃት አንጀቷ እንደነደደ ናት፡፡ በዚህም ምክንያት ሶማሊያ ውስጥ የአልሸባብን ይዞታ በአየር እየደበደበች ነው፡፡ ነገር ግን ውስጧን ካላፀዳች ልፋቷ ሁሉ ከንቱ ነው እየተባለ ነው፡፡      

        

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...