Saturday, April 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ወጣቱ ከተመሪነት ወደ መሪነት ይሸጋገር!

ስለወጣቱ ትውልድ የአገር መሪነት በርካታ ዲስኩሮች ይሰማሉ፡፡ የነገ የአገር ተረካቢነቱ በብዙዎች ይለፈፋል፡፡ በተግባር የሚታየው ግን ወጣቱ በብዛት እየተፈለገ ያለው ለመሪነት ሳይሆን ለአጃቢነት ነው፡፡ ወጣቱን ትውልድ አስተምሮ ማብቃት የቤተሰብ፣ የማኅበረሰቡና የመንግሥት ኃላፊነት መሆኑ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ወገኖች በወጣቱ አገር ተረካቢነት ላይ ይነጋገራሉ ወይ? ይግባባሉ ወይ? እርግጠኛ ሆነው ወጣቱን ከተመሪነት ወደ መሪነት ለማሸጋገር ይሠራሉ ወይ? በፍፁም! ከንድፈ ሐሳብ የዘለለ ተግባራዊ እንቅስቃሴ አይታይም፡፡

ወጣቶችን ለማብቃት ቁርጠኛ አቋም ያስፈልጋል ሲባል በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ በርካታ ሴሚናሮች፣ ሲምፖዚየሞችና መድረኮች ወጣቱን ስለማብቃትና ስለማሳተፍ ብዙ ተብሎባቸዋል፡፡ ነገር ግን ወጣቱን ደረጃ በደረጃ እያሳደጉ ወደ አመራር ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ምን ይመስላል? ለመሆኑ እምነቱስ አለ ወይ? ተብሎ ሲጠየቅ መልሱ አሉታዊ ነው፡፡ ከመነባንብ ያለፈ ተግባር እየታየ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ አገሪቱን እየጎዳት ነው፡፡

ወጣቱ በዙሪያው የከበቡት በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከመኖሪያ አካባቢው እስከ ትምህርት ቤት ድረስ በጫት፣ በአደንዛዥ ዕፆች፣ በመጠጥና በመሳሰሉት አደናቃፊ ነገሮች ተከቧል፡፡ በተለይ ዕድሜያቸው ለአቅመ አዳምና ሔዋን ያልደረሱ በርካታ ታዳጊዎች በቀን ጭፈራ ቤቶችና አልባሌ ድርጊቶች በሚፈጸሙባቸው ሥፍራዎች ታጥረዋል፡፡ ትምህርታቸውን ጨርሰው ሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች በቂ ክፍያ ስለማያገኙ ኑሮአቸው ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡ በርካቶች ሥራ አጥ በመሆናቸው ለቤተሰብ ተጨማሪ ሸክም ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች የከበቡት ወጣቱ ትውልድ አመርቂ የሆነ ፖሊሲ ተቀርፆለት ለነገ አገር ተረካቢነት ካልተዘጋጀ ውጤቱ አስከፊ ነው፡፡

መንግሥት በፖሊሲ ደረጃ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶችን በተመለከተ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ነገር ግን ዓለማችን አሁን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ፖሊሲው ምን ያህል አዋጭ ነው ተብሎ መገምገም የግድ ነው፡፡ ወጣቶችን ትምህርት ቤት መላክ ብቻ ሳይሆን የትምህርት ጥራቱ መገምገም አለበት፡፡ በርካታ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ሲገነቡ ለተማሪዎቻቸው ጥራት ያለው ትምህርት እየሰጡ ነው ወይ? በጭራሽ! በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ችግሮች ካሉ ደግሞ በፍጥነት ወደ መፍትሔው ማተኮር ጠቃሚ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶቹና ዩኒቨርሲቲዎቹ ከሚሰጡዋቸው አገልግሎቶች በተጨማሪ አካባቢያቸው ለተማሪዎች ምቹ ናቸው? ኃላፊነት የማይሰማቸው ወገኖች በዙሪያቸው ምን እያከናወኑ ነው? ሱስ ከሚያሲዙ ደባል ነገሮች ጀምሮ እስከ ልቅ ወሲብ ድረስ ይፈጸምባቸዋል የሚባሉ ሥፍራዎችን ማን ይቆጣጠራል? ምን ዓይነት ዕርምጃ ይወሰዳል? በቃል ከሚነገረው በላይ በተግባር የተገኘ ምን ዓይነት ውጤት አለ? ይህም በጣም አሳሳቢ ነው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ወጣቱን ለአባልነት መልምለው የሠልፍና የመፈክር አድማቂ ከማድረግ ባሻገር ለማብቃት የሚያደርጉት ጥረት የት አለ? ወጣቶችን መፈክር ከማሸከምና ተላላኪ ከማድረግ ባለፈ የሚሰጡዋቸው ኃላፊነት በግልጽ ይታያል ወይ? የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የሚመሩበትን ርዕዮተ ዓለም ወጣቱ ውስጥ በሚገባ አስርፀው ለመሪነት እያዘጋጁ ነው? ወይስ ያው የተለመደውን የጽንፍ ፖለቲካ እያጋቡባቸው ነው? መከራከር፣ መጠየቅ፣ ለለውጥ የሚረዱ ሐሳቦችን ማፍለቅና ለመሪነት ዝግጁ መሆንን የሚያሳዩ ወጣቶችን ያቀርባሉ ወይስ ያሸሻሉ? ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለት ይቻላል ለወጣቶች የሰጡት ትኩረት ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ ወጣቱን ለመምራት እንጂ ለመሪነት የማዘጋጀቱ ጉዳይ ተረስቷል፡፡ ተተኪን ከማዘጋጀት ይልቅ በአዛውንቶች መንገታገት የተመረጠ ይመስላል፡፡ ይኼ ማንን ይጠቅማል? ማንንም!

የብዙዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ወጣቶች የማኅበራዊ ድረ ገጽ እንቅስቃሴ ሲቃኝ ይህንን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ በቁጥር በጣም ውስን ከሆኑ ወጣት ፖለቲከኞች በስተቀር አብዛኞቹ ስሜታዊ ናቸው፡፡ በደመነፍስ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የፓርቲያቸውንም ሆነ የአገራቸውን ጥቅም እየጎዱ መሆናቸውን እንኳ አያውቁም፡፡ ሌላው ቀርቶ ትግል የሚያደርጉለትን ፓርቲ ዓላማና ግብ ለይተው ካለማወቃቸውም በላይ፣ ሕግጋቱን የተረዱም አይመስሉም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ችግር የሚመነጨው የፓርቲ አመራሮች ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ነው፡፡ ወጣቶችን ኮትኩተው ከማሳደግ ይልቅ ሌላ ተግባር ላይ ያሰማሩዋቸዋል፡፡ በጥላቻና በመፈራረጅ ከንቱ ጉዳዮች ውስጥ እየዘፈቁዋቸው ያደነዝዙዋቸዋል፡፡ ይኼ ራሱን የቻለ አደጋ ነው፡፡ ዛሬ ታርሞና ተኮትኩቶ ያላደገ ወጣት ፖለቲከኛ ነገ ለአገር እንዴት መፍትሔ ያመነጫል? የተሻለ አማራጭ ይዞ ይቀርባል? በጣም አሳሳቢ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ የመላው ዓለም ሥጋት የሆነው ሽብርተኝነት ዋነኛ ምንጩ የወጣቶች ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚና ከማኅበራዊ ጉዳዮች መገለል ነው እየተባለ ነው፡፡ ወጣቶች የአገራቸው ጉዳይ እንደ ራሳቸው ጉዳይ ሊያገባቸው ሲገባ በተገለሉ ቁጥር የአሸባሪዎች ቀላል ዒላማ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ዘመን በማኅበራዊ ድረ ገጾች ወጣቶችን የሚያጠምዱ አሸባሪዎች ደካማ ጎኖቻቸውን በመነካካት ላልተገባ ዓላማ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ ከአውሮፓና ከአሜሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የተጠመዱት በማኅበራዊ ድረ ገጾች ነው፡፡ በርካታ ወጣት ሴቶች ሳይቀሩ ተቀላቅለዋቸዋል፡፡ ወጣቱ በሞባይል ስልኩ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ዓለምን ሲያካልል እነዚህ ወገኖች በቀላሉ ያጠምዱታል፡፡ ሁልጊዜም ለተመሪነትና ለተላላኪነት የሚፈለገው ወጣት በሽብርተኞች አደንዛዥ ቅስቀሳ የሽብር ዓላማ አራማጅ ይሆናል፡፡ መገለሉና አለመፈለጉ የሚፈጥረው ሥነ ልቦናዊ ጫና በቀላሉ እጁን እንዲሰጥ ያደርገዋል፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ  እስከ መንግሥት ድረስ ይኼ ጉዳይ አሳሳቢነቱ እንቅልፍ ካልነሳ ምን የተለየ ትልቅ ብሔራዊ አጀንዳ ይኖራል? በእጅጉ ይታሰብበት!

ወጣቱ ሲታሰብ ከፍ ብሎ ያለው የአገር ብሔራዊ ጥቅም ነው መታየት ያለበት፡፡ በአልባሌ ሱሶች የደነዘዘ፣ በአገሩ ተስፋ የቆረጠና ነገን በተስፋ አሸጋግሮ ማየት የተሳነው ወጣት ተይዞ አገር ለመገንባት መነሳት ትርፉ ልፋት ነው፡፡ በወጣቱ ጉዳይ ሁሉም ወገን በአንክሮ ማሰብ ያለበት የነገዋን ኢትዮጵያ ማን ይረከበታል የሚለውን ነው፡፡ ከአገሪቱ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች የተገለለ ወጣት በንድፈ ሐሳብ ብቻ ድጋፍ እየተደረገለት እየበቃ ነው ቢባል ራስን ማታለል ነው፡፡ ወጣቱ እየተገለለና ኩርፊያው እንዲበዛ በተደረገ ቁጥር በተስፋ ቢስነት ስሜት ችግር ውስጥ ይወድቃል፡፡ አገሪቱንም ችግር ውስጥ ይከታል፡፡ ተስፋው በተሟጠጠ ቁጥር ከሰላም ይልቅ ለነውጥ ይነሳሳል፡፡ ይልቁንም ለአገሪቱ አስተማማኝ ህልውናና ዘለቄታዊ ጥቅም ሲባል ወጣቱ ከተመሪነት ወደ መሪነት እንዲሸጋገር መሥራት ጊዜ ሊሰጠው አይገባም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...