Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለ40 ዓመታት ከነገዱበት በተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ እምባ ጠባቂ ለአስተዳደሩን ማሳሰቢያ ሰጠ

ለ40 ዓመታት ከነገዱበት በተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ እምባ ጠባቂ ለአስተዳደሩን ማሳሰቢያ ሰጠ

ቀን:

– የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔም ምላሽ እንዲሰጣቸው ለከንቲባው ደብዳቤ ጽፈዋል

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ አካባቢ ከ1968 ዓ.ም. ጀምሮ በንግድ ሥራ ተሰማርተው የነበሩ ከ32 በላይ ዜጎች፣ በልማት ምክንያት በመፈናቀላቸው  ባሰሙት አቤቱታ፣ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የከተማ አስተዳደሩ አቤቱታቸውን ተቀብሎ እንዲያስተናግዳቸው ማሳሰቢያ ሰጠ፡፡

ነጋዴዎቹ በአክሲዮን ተደራጅተው ከ40 ዓመታት በላይ ሲነግዱበት የቆዩትን ቦታ ለማልማት የጠየቁ ቢሆንም፣ አስተዳደሩ ‹‹ነባር አጠቃላይ ነጋዴዎች አክሲዮን ማኅበር›› ለሚባል ማኅበር እነሱ የሚሠሩበትን ቦታ ጭምር በሊዝ በመውሰዱ፣ ላለፉት ስምንት ዓመታት ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት አቤቱታቸውን እያሰሙ መሆኑ ታውቋል፡፡

በአቶ ኩማ ደመቅሳ ሰብሳቢነት ይመራ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በ2005 ዓ.ም. ባስተላለፈው የመሬት ጉዳይ ውሳኔ፣ በአብዛኛው ዕድሜያቸው ከ50 ዓመታት በላይ የሆኑ እናቶች የተካተቱበት አቤቱታ አቅራቢዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው አስታውቋል፡፡

አቤቱታ አቅራቢዎቹ በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ተጨማሪ ማስረጃ ለማግኘት ሞክረዋል፡፡ በመሆኑም 32ቱም ተበዳይ ነን የሚሉት ዜጎች፣ ሕጋዊ ነጋዴ መሆናቸውንና ግብር ከፋዮች እንደሆኑ የሚያረጋግጥ መረጃ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አቅርበዋል፡፡ ነጋዴዎቹ ግብር የከፈሉትም ሕጋዊ በሆነና ከመንግሥት ጋር ተዋውለው በሚሠሩበት የንግድ ሱቅ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሰነድ ለከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ቢሮዎች አቅርበዋል፡፡

ራሳቸው ተደራጅተው ማልማት እንደሚችሉ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አለማግኘቱን የተረዱት 32ቱ ተፈናቃዮች፣ ‹‹በራሳችን እንድናለማ የማይፈቀድልን ከሆነ የመሥሪያ ቦታቸውን በሊዝ ወስዶ እያለማ (እየገነባ) ከሚገኘው ‹‹ነባር አጠቃላይ አክሲዮን ማኅበር ውስጥ እንካተት›› በማለት አማራጭ አቅርበው ነበር፡፡ ከወረዳ እስከ ከተማ አስተዳደር ድረስ ምላሽ ያጡት ተፈናቃዮቹ፣ አቤቱታቸውን ወደ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ወስደውት ነበር፡፡

እነ ነዋብ ጀማል (32 ሰዎች) በሚል አቤቱታ የቀረበለት የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ አስፈላጊውን መረጃ ከተቀበላቸው በኋላ አስፈላጊ ማጣራቶችን ማድረጉን በሪፖርቱ በዝርዝር አካቷል፡፡

ተፈናቃዮቹ ለ40 ዓመታት ሲኖሩ ያደረጉትን ሕጋዊ እንቅስቃሴዎች በሚመለከት ያቀረቡት ማስረጃና ቃለ መጠይቅ ተከትሎ ማብራሪያ እንዲሰጡ፣ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መሬት ግንባታ ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ዋና የሥራ ሒደት አስተባባሪ በተደጋጋሚ በተቋሙ ቢጠየቁም ምላሽ አለመስጠታቸውን የተቋሙ ውሳኔ ያስረዳል፡፡

ተቋሙ ምላሽ በማጣቱ ሠራተኞቹ በስፍራው ተገኝተው እንዲያጣሩ በማድረጉ፣ ተፈናቃዮቹ የሱቅ ኪራይ ውል፣ የኪራይ ደረሰኝ፣ የንግድ ግብር ደረሰኝ፣ የታደሰ የንግድ ፈቃድና ሌሎች መስፈርቶችን አሟልተው የተገኙ መሆኑን ዘርዝሮ ጽፏል፡፡ አቤት ባዮቹ ‹‹ነባር አጠቃላይ አክሲዮን ማኅበር›› እየገነባው ከሚገኘው ሕንፃ ጀርባ ጊዜያዊ ሱቆች ተሰጥቷቸው በመሥራት ላይ መሆናቸውን የጠቆመው እንባ ጠባቂ ተቋም፣ አቤት ባዮቹ ነባር ተጠቃሚዎች መሆናቸውን አስተዳደሩ አምኖ ያደረገው ተግባር መሆኑ ብዙ ነገር እንዲገነዘብ እንዳደረገው ገልጿል፡፡

ተፈናቃዮቹ ንግድ ፈቃድ አውጥተው፣ ግብር እየገበሩና የቤት ኪራይ እየከፈሉ የሚሠሩ ከሆነ፣ በአክሲዮን ማኅበሩ ውስጥ ‹‹እንካተት›› ብለው ላቀረቡት ጥያቄ ‹‹ከሕግ አንፃር አስተዳደሩ ምን ምላሽ መስጠት ይኖርበታል?›› በማለት የሚጠይቀው ተቋሙ፣ አስተዳደሩ የከተማ ቦታን በሊዝ እስከመፍቀድ የወጣውን የአፈጻጸም መመርያ ቁጥር 1/2002 አንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ 10 ላይ በግልጽ የተደነገገውን ለአቤቱታ አቅራቢዎቹ ቅድሚያ የመስጠት መብትን እንደሚነፍግ አስታውቋል፡፡

በመሆኑም አቤት ባዮቹ በአፈጻጸም መመርያው አንቀጽ 34(10) መሠረት በማኅበሩ መካተት እንዳለባቸው ዝርዝር የመፍትሔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ለአክሲዮን ማኅበሩ ቦታው በሊዝ እንዲሰጥ የፈቀደው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሊዝ ቦርድ፣ ቦታውን ለማኅበሩ የሰጠው የአቤት ባዮች የአካቱኝ ጥያቄ ሳይረጋገጥ መሆኑን ግንዛቤ በመውሰድ፣ ተፈናቃዮቹ ነባር ነጋዴዎች በማኅበሩ ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡

የአቤት ባዮቹ እነ ነዋብ ጀማል አቤቱታ የደረሰው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትም፣ በምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ዶ/ር ታቦር ገብረመድኅን ፊርማ ለከንቲባ ድሪባ ኩማ ደብዳቤ ጽፏል፡፡ እንባ ጠባቂ ተቋም በሰጠው ውሳኔ መሠረትም አቤቱታ አቅራቢዎቹ ያቀረቡት ጥያቄ የሕግ መሠረት ካለው ተጣርቶ ምላሽ እንዲሰጣቸው በድጋሚ አሳስቧል፡፡

ለዓመታት ወዲያና ወዲህ ሲል የከረመው የአቤቱታ አቅራቢዎቹ ቅሬታ ሰሞኑን ለከተማ አስተዳደሩ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የደረሰው ሲሆን፣ በአሠራር ጥራት ኦዲት ቅሬታና አቤቱት አፈታት ዴስክ ኃላፊ በአቶ ገረመው ወርቁ በተፈረመ ደብዳቤ የክፍለ ከተማው ወረዳ አንድ ኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት መረጃ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ምላሹን ወዲያውኑ የሰጠ ቢሆንም፣ የቢሮው ውሳኔ ግን እስካሁን አልታወቀም፡፡ ሪፖርተር በአስተዳደሩ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ተገኝቶ የቢሮ ኃላፊውን ለማግኘት ያደረገው ጥረት፣ በጸሐፊያቸው አማካይነት ‹‹ይህ ጉዳይ እሳቸውን አይመለከትም፤›› የሚል ምላሽ ተሰጥቶታል፡፡ ይመለከታቸዋል የተባሉት የአሠራር ጥራት ኦዲት፣ ቅሬታና አቤቱታ አፈታት ዴስክ ኃላፊንም ለማነጋገር የተደረገው ሙከራ ‹‹ይህ ጉዳይ ከእሳቸው እጅ ወጥቷል፤›› በመባሉ፣ የአቤቱታ አቅራቢዎቹ የመጨረሻ ውሳኔ የትኛው ኃላፊ ዘንድ እንዳለ ለማጣራት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...