Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የአውሮፓ ኩባንያዎች ከመንግሥት የሚፈልጓቸው ለውጦች

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ውስጥ የሚገኙ 300 ያህል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ማድረጋቸውን ተከትሎ መንግሥት ማሻሻል አለበት ያሏቸው ጥያቄዎች ሲያቀርቡ ሦስት ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ 

  ለሦስተኛ ጊዜ በሒልተን በተካሄደው የአውሮፓ ኅብረት ኩባንያዎች ኮንፈረስ ላይ አራት መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ቀርበዋል፡፡ የታክስ አስተዳደር ላይ የሚታዩ ችግሮች፣ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓትና አተገባበር፣ የኢንቨስትመንትና የንግድ ፈቃድ ለማውጣት የሚጠየቁ የብቃት ማረጋገጫዎች ብዛትና የቢሮክራሲ መንዛዛት ወይም የአስተዳደራዊ ብቃት ችግሮች በዚህ ዓመት ጎልተው የወጡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዓበይት ችግሮች ናቸው ተብለዋል፡፡

  ኩባንያዎቹ የመሠረቱት የአውሮፓ ኅብረት ቢዝነስ ፎረም በኢትዮጵያ የተሰኘው ተቋም፣ በዘንድሮው ስብሰባው በጥናት ደረስኩባቸው ያላቸውን ችግሮችና ወደፊት ችግሮቹ ሊቀረፉ ይችላሉ ያለባቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች ያካተተ ፍኖተ ካርታ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አቶ ፍጹም አረጋ አስረክቧል፡፡

  ከስድስት ወራት በፊት ጥናት ተካሂዶና 80 ኩባንያዎች መጠይቅ ተደርጎላቸው እንደነበር ያስታወሰው ፎረሙ፣ እነዚህ ኩባንያዎች ባስቀመጡት መሠረት አሥር መሠረታዊ የሚባሉ ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው ለይቷል፡፡ ከአሥሩ መካከል አራቱ ነጥረው መውጣታቸውን ለሪፖርተር የገለጹት፣ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ አምባሳደር ቻንታልሔ በረከት ናቸው፡፡ አምባሳደሯ ከቴክኒክ ባለሙያዎቻቸው ጋር በመሆን እንዳብራሩት በጥናት የታወቁት ችግሮች የታክስ፣ የጉምሩክ፣ የአስተዳደር ብቃት ችግሮችና የፈቃድ አሰጣጥ ላይ የሚታዩ መንዛዛቶች ሲሆኑ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትም ዋናው የችግሮች አካል ነበር፡፡ ሆኖም የውጭ ምንዛሪ እጥረት የፖሊሲ ጥያቄ ያዘለ በመሆኑ ከሌሎች ጥያቄዎች ተነጥሎ እንዲወጣ መደረጉን፣ የተቀሩት ግን መፈታት የሚገባቸው ችግሮች ሆነው እንደተገኙ ገልጸዋል፡፡

  የአውሮፓ ኩባንያዎች በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ላይ ከሰነዘሯቸው አሳሳቢ ችግሮች መካከል የታክስ አስተዳደሩና የጉምሩክ አሠራሩን የተቹ ናቸው፡፡ በተለይ በታክስ አስተዳደር ላይ የሚታየው የይግባኝ አቀራረብና ምላሹ፣ የታክስ አጣጣልና የታክስ አጥኝዎች ችግሮች ጎልተው ተደምጠዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የታክስ ጉዳይ ላይ ይግባኝ ለመጠየቅ ቅድሚያ መከፈል ያለበት የ50 ከመቶ የታክስ መጠን መነሳት እንዳለበት የጠየቁ ሲሆን፣ በታክስ ቅሬታ ላይ እኩልና ወጥነት ያለው አስተዳደር አለመኖርም መሻሻል አለበት ተብሏል፡፡ ከጉምሩክ አሠራር ጋር በተያያዘም ተመሳሳይ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ወጥነትና አግባብነት ያለው የገቢ ዕቃዎች ቀረጥ አጣጣል እንደማይታይ ኩባንያዎቹ መናገራቸውን፣ የፎረሙ ጥናት ይጠቅሳል፡፡

  ከዚህ ባሻገር በኢንቨስትመንትና በንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ወቅት የሚታዩ ችግሮችም የአውሮፓውያኑ ጥያቄዎች ከሚነሱባቸው መካከል ይካተታሉ፡፡ በመሆኑም መንግሥት የውጭ ኢንቨስተሮች ፈቃድ ለማውጣት ሲመጡ በቅድሚያ 150 ሺሕ ዶላር በብሔራዊ ባንክ እንደሚያስቀምጡ፣ ይህም ዝቅተኛው የካፒታል መጠን ግዴታ ተደርጎ መታየቱን ፎረሙ እንዲያጠኑለት ያሳተፋቸው ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች ከተለያዩ አገሮች ተሞክሮ አኳያ በማነጻጸር ተችተዋል፡፡ ይህ መጠን እንዲነሳም ጠይቀዋል፡፡ አምባሳደር ቻንታልም ይህ የካፒታል መጠን አነስተኛ የሚባል ባለመሆኑ መነሳቱ ተገቢ እንደሆነ፣ ምን እንዲፈይድ ተፈልጎ ስለመውጣቱም ይጠይቃሉ፡፡

  የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ ማለት እንደዚህ ያሉ እክሎችን አስቀምጦ እንደማይቻል፣ ይልቁንም የተሻለ አማራጭ ወደሚሰጡ አገሮች ለማምራት ምክንያት እንደሚሆን ባለሙያዎቹ ለማስጠንቀቅ ሞክረዋል፡፡ ከፈቃድ ጋር በተያያዘ ሌላኛው ጥያቄ የብቃት ማረጋገጫ እንዲያወጡ የሚያስገድድ አሠራር መኖሩን የሚመለከት ነው፡፡

  በአገሪቱ 36 ያህል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የብቃት ማረጋገጫ በመስጠት የውጭም የአገር ውስጥም ኩባንያዎች የንግድ ፈቃድ እንዲያወጡ በቅድመ ሁኔታነት ያስገድዳሉ፡፡ ይህ አሠራር ግን በአውሮፓ ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆን በዓለም ባንክ ባለሙያዎችም ጭምር ትችት ቀርቦበታል፡፡ ይኸውም በሌሎች አገሮች እንዲህ ያሉ አሠራሮች የሚያስፈልጉት በተወሰኑ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ሲሆን፣ እነዚህም በሰዎችና በአካባቢ ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ በሚያሰጉ መስኮች ላይ በግዴታነት የሚጣል መሆኑን ካመላከቱት መካከል በዓለም ባንክ የፋይናንስ ክንፍ ለሆነው ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋም የኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ማሞ ምኅረቱ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ የብቃት ማረጋገጫ በሁሉም መስኮች ላይ እንዲተገበር መደረጉ አላስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ፡፡

  ይህ ብቻም ሳይሆን የውጭ ኢንቨስተሮች የሚጠየቁት ዝቅተኛው የካፒታል መጠን 150 ሺሕ ዶላር ተገቢነት እንደሌለው የሚገልጹት አቶ ማሞ፣ ቅድመ ሁኔታው ከዓለም አገሮች ተሞክሮ አኳያ ሲነጻጸርም ኢትዮጵያ በውጭ ኢንቨስትመንት ላይ የምትከተለውን አሠራር እንድትፈትሽ የሚያስገድዳት ነው፡፡

  አውሮፓውያኑ ብዙ ፈላጊ ናቸው?

  ይህንን ጥያቄ በተዘዋዋሪ ከሚመልሱት መካከል አቶ ማሞ አንዱ ሲሆኑ አውሮፓውያኑ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች መሠረታዊ የኢንቨስትመንት ችግሮች ቢሆኑም፣ መንግሥት ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ያከናወናቸውን ሥራዎችና የወሰዳቸውን ለውጦች መመልከት እንደነበረባቸውም አስታውሰዋል፡፡ ለአብነትም መንግሥት አዲስ የጉምሩክ አዋጅ አውጥቶ ትግበራ መጀመሩ፣ የአንድ መስኮት አገልግሎት 19 መሥሪያ ቤቶችን በማቀናጀት ለመዘርጋት መዘጋጀቱ ከሚጠቀሱለት የለውጥ ዕርምጃዎች መታየት እንደነበረባቸው አቶ ማሞ አስረድተዋል፡፡ የዓለም ባንክ ለእነዚህ ተግባራት ድጋፍ መስጠቱንም ጠቅሰዋል፡፡

  ይህ እንዳለ ሆኖ የአውሮፓ ኩባንያዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ከሚያደርጓቸው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች አኳያ ተገቢነት እንዳላቸው፣ የአውሮፓውያኑን ያህል በይፋ አይሁን እንጂ ቱርኮችና ህንዶችም ተመሳሳይ ጥያቄዎችን እንደሚያነሱ የጠቀሱት የፎረሙ ሰብሳቢ ክሪስ ደ ሙዬንክ ናቸው፡፡ ካለፉት ዓመታት አኳያ ከመንግሥት አካላት ጋር በሚደረጉ ውይይቶች ላይ የሚታየው አወንታዊነትና የጥያቄዎች ምላሽ አሰጣጥ ላይ የሚታየው ፍጥነት መልካም የሚባል መሆኑን ሙዬንክ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡

  ከሦስት ዓመታት በፊት የአውሮፓ ኩባንያዎች በመሠረቱት ፎረም አማካይነት ጥያቄ ማቅረብ ከጀመሩባቸው መስኮች መካከል የመልቲ ሞዳል አተገባበር፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አሠራርና ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቁ መሆናቸው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡Anchor

  የዓለም ባንክ በቅርቡ የ189 አገሮችን ኢኮኖሚ በማጥናት በእነዚህ አገሮች ቢዝነስ መሠራት ምን ያህል ቀላል መሆኑን የሚያመላክት መረጃ ይፋ አድርጐ ነበር፡፡ ባንኩ ባወጣው መረጃም መሠረት እ.ኤ.አ. በ2015 በኢትዮጵያ ውስጥ ቢዝነስ ለመሥራት ምን ያህል ቀላል ነው በሚለው መስፈርት፣ አገሪቱ ከ184 አገሮች 132ኛ ላይ መቀመጥ ችላለች፡፡ ዓለም ባንክ “Doing Business” በሚል ባወጣው በዚህ መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ አዲስ ቢዝነስ ለመጀመር በሚለው መስፈርት 168ኛ፣ ንብረት ለማስመዝገብ 104ኛ፣ ብድር ለማግኘት 165ኛ፣ ግብር ለመክፈል 112ኛ እንዲሁም ውል ለማስፈጸም 50ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ በአጠቃላይ አገሪቱ 132ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ፣ ባለፈው ዓመት ካስመዘገበችው በሦስት ደረጃ ዝቅ ብላለች፡፡  

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች