Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ኢትዮጵያ በአሜሪካ በሚካሄደው የልዩ ቡና ጉባዔ ትልቁን ቦታ ይዛ ትቀርባለች ተባለ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በየዓመቱ የሚካሄደው የአሜሪካ የልዩ ቡና ጉባዔ በአሜሪካ ስፔሺያሊቲ ኮፊ አሶሲዬሽን አማካይነት የሚሰናዳ ሲሆን፣ በመጪው ሳምንት በሲያትል ለሚካሔደው 27ኛው ዓለም አቀፍ ጉባዔ ኢትዮጵያ ዋና የልዩ ቡና መገኛ ሆና እንደምትቀርብና ትልቁን ቦታ እንደምታገኝ ተገልጿል፡፡

  መጋቢት 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በሒልተን በተካሔደ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት፣ የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ ምክትል ልዑክ ፒተር ቭሩማን ከመንግሥት ኃላፊዎችና ከቡና መስክ ባለድርሻዎች ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ ወቅት እንዳስታወቁት፣ ኢትዮጵያ በመጪው ሳምንት በአሜሪካ ሲያትል በሚካሄደው የልዩ ጣዕም ቡና ጉባዔ ላይ የምትቀርበው፣ ዘጠኝ ሺሕ አባላት ባሉትና ከ40 አገሮች በተውጣጡ የልዩ ቡና ጣዕም ማኅበር አባላት በሚሳተፉበት ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ለአገሪቱ የገበያ ዕድሎችንና አዳዲስ የገበያ ግንኙነቶችን ለመፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

  በንግድ ሚኒስቴር የወጪ ንግድ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጄነራል አቶ አሰፋ ሙሉጌታ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ባገኘችው ዕድል አማካይነት ከገበያ ትስስር ባሻገር በጉባዔው ላይ አገሪቱ የቡና አፈላል ሥነ ሥርዓት፣ ልዩ ልዩ የቡና ዝርያዎችን በሚመለከት ገለጻዎችና ማብራሪያዎች እንደሚሰጡ አስታውቀዋል፡፡ 40 ያህል ልዑካንም ከቡና ዘርፍና ከመንግሥት ኃላፊዎች ተውጣጥተው ወደ አሜሪካ እንደሚያቀኑ ገልጸዋል፡፡ የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ልዑኩን እንደሚመሩትም ይጠበቃል፡፡

  ኢትዮጵያ ከአራት ሺሕ በላይ የቡና ዝርያዎች እንዳሏት ያስታወሱት፣ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ሁሴን አርጋው ናቸው፡፡ አቶ ሁሴን እንዳሉት በዓለም ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ የቡና ዘርፍ ተዋናዮች በሚገኙበት መድረክ ላይ መገኘት ለአገሪቱ ቡና ላኪዎች ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አስታውሰዋል፡፡

  አፍሪካ ፋይን ኮፊስ አሶሲዬሽንን በሰብሳቢነት የሚመሩት አቶ አብደላ ባገርሽ በበኩላቸው፣ የአገሪቱ ቡና የገዥዎች ችግር ሳይሆን የማስተዋወቅና እሴት የመጨመር ችግር እንደሚታይበት ይናገራሉ፡፡ ለዓለም ገበያ የሚቀርበው ቡና አገሪቱን ባህላዊ እሴቶች እንዲያንፀባርቅ ተደርጎ ለገበያ አለመቅረቡም ወደፊት ሊሠራበትና ሊለወጥ የሚገባ መስክ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ 

  ይህ ይባል እንጂ ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ቡና ውስጥ የልዩ ጣዕም ቡና መጠን እጅግ ዝቅተኛ ከመሆኑም ባሻገር ሊያስገኝ የሚገባውን ፕሪሚየም ክፍያ ወይም የተሻለ ክፍያ እንደሚፈለገው መጠን በማስገኘት ላይ የሚገኝ አይደለም፡፡ በዓለም ላይ በየዓመቱ 500 ቢሊዮን ስኒ ቡና እንደሚጠጣ ሲታሰብ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ አስተዋጽኦ ዝቅተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡ ለዓለም ገበያ ከሚቀርበው 130 ሚሊዮን ኬሻ ቡና ውስጥ ኢትዮጵያ የምታቀርበው ስድስት ሚሊዮን ኬሻ ወይም 300 ሺሕ ቶን ያልሞላ የቡና መጠን እንደሆነ አቶ አሰፋ ያስታውሳሉ፡፡ በአንፃሩ እንደ ብራዚል ካሉ አገሮች ጋር ብቻም ሳይሆን በዓለም ቡና ኢንዱስትሪ ውስጥ መጤ ከሆኑት ኮሎምቢያና ቬትናም ጋር በመወዳደር በዓለም ሁለተኛዋ የአረቢካ ቡና አምራች ለመሆን ኢትዮጵያ መነሳቷን አቶ አሰፋ አስታውቀዋል፡፡

  ኢትዮጵያ የቱንም ያህል የተፈጥሮ ቡና ለዓለም ገበያ እንደምታቀርብ ብትገልጽና የቡና መገኛነቷን ብታስታውቅም፣ በውጤቱ ግን ዝቅተኛውን የቡና ገቢ በማግኘት ከሚጠቀሱ አገሮች ውስጥ አንዷ ናት፡፡ ከዓለም ገበያ አኳያ የሦስት በመቶ የገበያ ድርሻ እንዳላት ይነገራል፡፡ በአንፃሩ ከ200 ሺሕ ቶን በላይ ቡና ለአገር ውስጥ ፍጆታ እንደሚውል ሲታወቅ፣ አቶ አሰፋ እንደሚገልጹትም ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለአገር ውስጥ ገበያም መቅረብ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ የአገር ውስጥ የቡና ገበያ እንደ ውጭው የጥራት ደረጃው የተጠበቀና፣ እንደ ይርጋጨፌ፣ ሲዳማና ሐረር የተመረተበት አካባቢ እየተገለጸ ለሸማቹ ባይቀርብም እንደ ኬንያ ካሉ አገሮች በተሻለ ለቡናው ኢንዱስትሪ ትልቅ አስተዋጽኦ በማድረግ ረገድ የአገር ውስጥ ገበያ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ከዚህ ባሻገር 15 ሚሊዮኖች በቡና መስክ ተሰማርተው የዕለት ጉርሻቸውን እንደሚያገኙበት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

  በአሜሪካ በሚካሔደው የልዩ ጣዕም ቡና ኮንፈረንስ ላይ ተጨማሪ ገበያዎችና ገዥዎች ከተገኙ አገሪቱ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ለማስመዝገብ የምትችልበትን ዕድል ያመጣላታል ተብሎ ሲጠበቅ፣ በአሜሪካ በዓመት 150 ቢሊዮን ስኒ ቡና የሚጠጡ በመኖራቸው፣ የገበያው ዕድል ሰፊ መሆኑን ቭሩንማን አስታውሰዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች