Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የተገኙ የዝሆን ጥርሶች፣ ከዝሆን ጥርስ የተሠሩ ጌጣጌጦች በመጋቢት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል ተቃጥለዋል:: ለመቃጠል ከተዘጋጁት ጌጣጌጦች በከፊል

ትኩስ ፅሁፎች

ላልታወቀው ኩርፊያ

ከሰዎች መሀል ተቀምጬ

ልዕልትነትዋን ስጠብቅ

ናፍቆትዋ ልቤን እያደማው

እሰቃያለሁ በድብቅ፡፡

መምጣትዋ ልደት ሆነና-

የናፍቆት ጧፎች ተመዘዙ

ተቀጣጠሉ ሳቆች-

ፈገግታዎች ተያያዙ፡፡

ቤቱም በደስታ ደመቀ-

በድምቀቱም እኔ ጠፋሁ

በፊትዋ እምለይበት-

መንገድ አጥቼ ተከፋሁ፡፡

በሁካታቸው ግርግር-

ልቤን አፍነው አስጨንቀው

ወሰዱት ሳቄን ወሰዱት-

ከጥርሴ መሀል ፈልቅቀው፡፡

የድፍረታቸው ብዛት-

ይኸው ቆመዋል ከፊቴ

ምን ብዬ ልጩህ ለዳኛ-

ከቶ ላይሰምር ሙግቴ

ብሄድላቸው ይሻላል-

ደህና እደሪልኝ ልዕልቴ፡፡

ታገል ሰይፉ፣ ‹‹ቀፎውን አትንኩት›› (1986)

* * *

የአፍታ እንቅስቃሴን የሚያበረታታው ዘመቻ

ሙሉ ቀን በሥራ የደከመ አካልዎን ዘና ለማድረግ ወደ ጅምናዝየም ጐራ ይሉ ይሆናል፡፡ በጅምናዝየም አካልዎን ለማፍታታት መሄድዎ ጠቀሜታ ቢኖረውም፣ በሥራ ምክንያት ለረጅም ሰዓት በመቀመጥዎ በጤናዎ ላይ የደረሰውን ጉዳት ግን አያካክሰውም፡፡

ለረጅም ሰዓት በሥራ ተጠምዶ መቀመጥ አካል እንዳይንቀሳቀስ ማድረጉም የጤና ሥርዓትን ያቃውሳል፡፡ ሰዎችን የበሽታ መናኸሪያ ያደርጋል ሲልም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ለረጅም ሰዓት ተቀምጦ መሥራት በጤና ላይ እያደረሰ ያለውን ውስብስብ ቀውስ ለመታደግ በእንግሊዝ ‹‹ጌት ብሪቴን ስታንዲንግ›› እና የሚል ዘመቻ የተጀመረ ሲሆን፣ ዓላማውም የቢሮ ሠራተኞች በሥራ መሀል፣ ስልክ ሲያናግሩ ወይም ስብሰባ ሲያደርጉ ቆመውና አካላቸውን እያፍታቱ እንዲሆን ለማስቻል ነው፡፡

ለረጅም ሰዓት ተቀምጦ መሥራት በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን፣ የደም ግፊት ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆን ከማድረጉም በተጨማሪ በሰውነተ ውስጥ ስብ እንዲከማች ያደርጋል፡፡

ብዙዎች ተቀምጠው በመሥራታቸው ወይም መኪና ሲያሽከረክሩ በመዋላቸው ምክንያት ሰውነታቸውን ለማፍታታት ሲሉ ወደ ጂምናዚየም ይሄዳሉ፡፡ በብሪቴን በጉዳዩ ላይ ጥናት እንዳደረጉት የ‹‹ጌት ብሪቴን ስታንዲንግና›› የብሪትሽ ኸርት ፋውንዴሽን ገለጻ፣ ጂምናዚየም መሄዱ በቂ አይደለም፡፡ በየሥራ መሀል እየተነሱ ሰውነትን ማፍታታት የሰውነት የውስጥ ሥርዓት በአግባቡ እንዲከናወን ያግዛል፡፡

ለዚህም ወደ ቢሮ ሲገቡ ከአሳንሰር ይልቅ ደረጃዎችን መጠቀም፣ ምግብ ሲበሉ በሥራ የቆዩበት ጠረጴዛ ላይ አለመብላት፣ ከሚሠሩበት ኮምፒዩተር፣ ማሽን ወይም ወረቀት ላይ በየ30 ደቂቃው በመነሳት ሰውነትን ማፍታታት፣ ለቢሮ ባልደረባ ስልክ ከመወደል ወይም መልዕክት ከመላክ ይልቅ ራስ መሄድን ሰውነትን በየሰዓቱ ለማፍታታት ይረዳል፡፡ እንደ ጥናቱ ከሆነ የሥራ ሰዓትን በእንቅስቃሴ በማጀብ በሰዓት እስከ 50 ካሎሪ ድረስ ማቃጠል ይቻላል፡፡

ማዶናን ለመምሰል የተከፈለ 50 ሺሕ ፓውንድ

የ31 ዓመቱ አዳም ዳኔል አሜሪካዊቷን ታዋቂ አቀንቃኝ፣ የቲያትር ባለሙያ፣ የዘፈን ግጥም ጸሐፊና ነጋዴ የሆነችውን ማዶናን የመምሰል ፍላጐት ያደረበት የ15 ዓመት ታዳጊ እያለ መሆኑን ይናገራል፡፡ በታዳጊነቱ ያደረበትን ማዶናን የመምሰል ፍላጐት ያሳካው ደግሞ 31 ዓመት ሲሞላው ነው፡፡ ለዚህም 50 ሺሕ ፓውንድ ወጭ አድርጓል፡፡

ዳኔል ማዶናን ለመምሰል ጉንጩን፣ አገጩንና የላይኛውን የፊቱን ክፍል በተደጋጋሚ የፕላስቲክ ሰርጀሪ ያደረገ ሲሆን፣ የፊቱ ቅርጽ ማዶናን እስኪመስል ድረስም ፊቱ ላይ የፕላስቲክ ሙሌት ተደርጓል፡፡

አሜሪካዊውን ዳኔልን ጠቅሶ ኤክስፕረስ እንደዘገበው፣ ዳኔል ማዶናን ለመምሰል ሲል ሲያገኝ የነበረውን ገንዘብ በሙሉ ለፕላስቲክ ቀዶ ሕክምናው አውሏል፡፡   

የእባብ ስርቆት

ልብስ፣ ምግብ ወይም ዕቃ ሰርቆ መሰወር የተለመደ ነው፡፡ እባብ ሲሰረቅ ግን በተለይም ለብዙኃኑ ነዋሪ ግር ሊያሰኝ ይችላል፡፡ በእንግሊዝ ሰሜን ምሥራቅ በምትገኘው ሜርሲሳይድ ከተማ 40 ሮያል ፋይቶን እባቦች መዘረፋቸውን ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡

ሁለት ግለሰቦች 40 መርዛማ ያልሆኑ ሮያል ፋይቶን የእባብ ዝርያዎችን ይዘው በመሰወራቸው የከተማዋ ፖሊስ በማደን ላይ ይገኛል፡፡

ዘራፊዎቹ ምንም ዓይነት አደጋ በሰዎች ላይ የማያደርሱትን ፋይቶን እባቦች ለገበያ ያቀርቧቸዋል የሚል ጥርጣሬ መኖሩን መርማሪ ኮንስታብል ኔል ሄንሪ ለስካይ ኒውስ ገልጸዋል፡፡

ጐዳና ያጨናነቁ ዓሣዎች

አምስት ቶን የሚመዝኑ ‹‹ካትፊሽ›› ዓሣዎች የተጫኑበት መኪና የኋለኛው ክፍል ድንገት በመከፈቱ ተዘርግፈው በደቡብ ምዕራብ ቻይና የምትገኘዋን የጉዋዛ ከተማን ጎዳና ያጨናነቁት ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡

በዝውውር ላይ የነበሩትንና ከነሕይወታቸው የተጫኑትን ዓሣዎች ሕይወት ለመታደግ የአካባቢው እሳት አደጋ ብርጌድ መሳተፉን ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች