- የወረዳ አስተዳዳሪና የፖሊስ አዛዥ በክሱ ተካተዋል
አንዱ ወገን በሌላኛው ወገን ላይ የጦር መሣሪያ እንዲያነሳ በመስማማትና በሚያስከትለው የወንጀል ድርጊት ላይ ሙሉ በሙሉ ተካፋይ በመሆን፣ ከ55 በላይ የሌላ ብሔር ተወላጆችንና የፌዴራል ፖሊሶችን በመግደል ወንጀል የተጠረጠሩ፣ የደቡብ ክልል ቤንቺ ማጂ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ 18 ነዋሪዎች ላይ መጋቢት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተ፡፡
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ሟቾቹ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ወደ ደቡብ ክልል በተለይ በቤንች ማጂ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ በመሄድ፣ በአካባቢው ሰፍረው ለበርካታ ዓመታት ኖረዋል፡፡ የሌላ ብሔር ተወላጆች ወይም በተከሳሾቹ አጠራር ‹‹አማሮች›› የሚባሉት የአማራ ብሔር ተወላጆች፣ ‹‹መሬታችንን ለቀው ይውጡ›› በማለት ቀኑና ወሩ በትክክል በማይታወቅበት፣ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ይዘው የመጡትን ፌስታል ብቻ ይዘው እንዲወጡ የጉራፈርዳ ፖሊስ አዛዥና የወረዳው አስተዳዳሪ ጭምር ድርጊቱን መፈጸማቸውን ክሱ አካቷል፡፡
ለዓመታት ከአካባቢው ተወላጆች ጋር በሰላምና በፍቅር የኖሩትን የሌላ ብሔር ተወላጆች፣ ‹‹ይኼ ክልል የደቡቦች በመሆኑ ይዛችሁት የመጣችሁትን ፌስታል ይዛችሁ አገራችንን ለቃችሁ ውጡ፡፡ የማትወጡ ከሆነ ሌላ ኃይል ማደራጀት ሳያስፈልግ በራሳችን ኃይል እናስወጣችኋለን፤›› ብለው በስብሰባ ላይ በመናገር ከቤታቸው በኃይል እንዲወጡ ማድረጋቸውን ክሱ ያብራራል፡፡
ከተከሳሾቹ ውስጥ በቤንቺ ማጂ ዞን የጉራፈርዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ምፍሳፎ ጉይ ቡላመጉት፣ የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔተር ምስክር ደጅዋ ሉታ፣ የወረዳው የድርጅት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ተካልኝ ሽፈራው፣ የወረዳው አስተዳዳሪ አማካሪ አቶ ክፍሌ ሽፈራው፣ የወረዳው ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና ሌሎቹም ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም፣ የዞኑና የቀበሌው ነዋሪዎች ያቀረቡትን ‹‹ግጭት ይነሳል›› የሚል ሥጋት ወደ ጐን በመተው፣ ‹‹አማሮች እስከ 2007 ለቃችሁ ትወጣላችሁ›› በማለት በወሰዱት ዕርምጃ፣ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው በክሱ ተገልጿል፡፡
በአካባቢው የተፈጠረውን ግጭት ለማስቆምና ለማረጋጋት ወደ ዞኑና ወረዳው ያመሩት የፌዴራል ፖሊሶች አካባቢውን እንደማያውቁት የተረዱት ተከሳሾቹ፣ መንገዱን እየመሩዋቸው በመሄድ ላይ ሳሉ በጫካ ውስጥ ላሉ ግብረ አበሮቻቸው ስልክ በመደወል፣ ‹‹የፌዴራል ፖሊሶችን እየመራን ይዘናቸው እየመጣን ነው፤›› በማለት እንዲዘጋጁ ካደረጉ በኋላ፣ ሰመርታ የተባለው ሥፍራ ሲደርሱ ከፍተኛ ጉዳትና ግድያ እንደፈጸሙባቸው ክሱ ያብራራል፡፡
ተከሳሾቹ ባላቸው የተለያየ ተሳትፎ ከ55 በላይ ‹‹አማሮች›› እና የፌዴራል ፖሊሶችን መገደላቸውን፣ በሰባት ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ ግምታቸው 998,049 ብር የሆኑ 124 የሳር ጐጆዎችና አራት የቆርቆሮ ቤት አቃጥለዋል፡፡ ግምታቸው 9,857,058 ብር የሆኑ 23,272 እንስሳትን መውሰዳቸውን፣ ግምቱ 16,050,682 ብር የሆነ 19,390 ኩንታል የተለየ ዓይነት ሰብል ማውደማቸውን፣ 1,138 ሔክታር ማሳ ላይ የነበረ ሰብል ማውደማቸውን፣ ግምታቸው 896,945 ብር የሆኑ 12,912 የእርሻ መሣሪያዎችን መውሰዳቸውንና በተለያዩ የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ በስፋት ይተነትናል፡፡
ተከሳሾቹ በችሎት ቀርበው ማንነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ከሦስት ተከሳሾች በስተቀር ሌሎቹ የግል ጠበቃ ማቆም እንደማይችሉ ተናግረው፣ መሀላ በመፈጸም መንግሥት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ታዟል፡፡ አማርኛ ቋንቋ በደንብ መስማት የማይችሉ በመሆናቸው አስተርጓሚ እንዲመደብ ከታዘዘ በኋላ፣ የክስ ቻርጁ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ክስ ለመስማት ለመጋቢት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶ ተከሳሾቹም ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡