Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዕጣ ፈንታ ሆኖ ከላይ ታች ይለናል!

ሰላም! ሰላም! ሲናገሩት ተረት በሚመስል መራር እውነታ ተከበን፣ ስቃይን እያፈንን በምን ተደረገና ተሰማ ሐተታ መቀባበል መቼም ሥራችን ሆናል። ዕድሜ ለ‘ቴክኖሎጂ’ እንዳትሉ ብቻ! ባሻዬ “እኔ እኮ! የማይገባኝ የሞት፣ የሁከትና የጦርነት መረጃ በደቂቃ ማከፋፈል ነው አሁን ‘ቴክኖሎጂን’ ዕድሜ የሚያስመኝለት? የመሠረታዊ ፍላጎቶች እጦትና ጉስቁልና እየተጫወተብን ለራሳችን ዕድሜ መመኘት ትተን ‘ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ’ እንመኝ? በእውነት የምንመኘውንማ አናውቅም። ጉድ እኮ ነው!” ሲሉኝ ነበር። ታዲያ አንድ ትልቅ ሰው መቼ ዕለት ደወሉልኝና ገና ላስቲኩ ያልተላጠ ሰላሳ አራት ‘ኢንች፣ ኤልሲዲ’ ቴሌቪዥናቸውን “ወዲያ ሽጥልኝ!” አሉኝ። እኔ ደግሞ አንዱን ሳናጣጥም በላይ በላዩ የሚጎርፍብንን የ‘ቴክኖሎጂ’ ትሩፋት እያሰብኩ ‘ከዚህ የተለየ ደግሞ ምን ዓይነት አስማተኛ ቴሌቪዥን ገዝተው ይሆን?’ ብዬ አሰብኩ። ሁኔታው ከንክኖኝ ስጠይቃቸው፣ “እኔማ ቴሌቪዥን የገዛሁ መስሎኝ ነበር። ደም መግዛቴን ሽብር ቤቴ ማስገባቴን ውሎ ካደረ አወቅኩ እንጂ፤” አሉኝ። “አንበርብር መደንገጥ አነሳኝ? ይኼ ቴሌቪዥንና ዲሽ ቤቴ ከመግባቱ በፊት የሞት ዜና እንዴት ያስደነግጠኝ እንደነበር ላስረዳህ አልችልም። እንኳን የሰው ለዓመት በዓል የማፈሰው የበግ ደም እንዴት እንደሚነዝረኝ እኔ ብቻ ነበርኩ የማውቀው። ይኼው አሁን ግን ሞት አያስደነግጠኝና ደም እያስበረገገኝ እንቅልፍ አጣሁ፡፡ ኧረ ወዲያ ውሰድልኝ፤” አሉኝ ፈርጠም ብለው። የገባውና ያወቀበት በጎ ፍርኃትና ድንጋጤን የሰውነቱ መጠለያው ሊያደርጋቸው ሲቆርጥ ሳይ፣ መላመድ የሠራለት ይኼን ሰምቶ የብልጥ አሳሳቅ እንጥሉን ሲቧጥጥ አሰብኩ። የዚህ ዓለም ነገር ደንቆኝ ‘ለካ በቁም ሞትም ይለመዳል’ ብዬ ተከዝኩ። ያልባሰበት የለማ!

እናላችሁ ይኼን አነጋጋሪ የ‘አልሰማም አላይም’ አሻፈረኝ ባይነት ለአንድ ደላላ ወዳጄ ነገርኩት። የመንገሬም ምክንያት ከእኔ ይልቅ እሱ እንዲህ ዓይነት ዕቃዎችን ፈጥኖ የማሻሻጥ ዕድል ስላለው ነበር። በከፊል እያዳመጠኝ ስልኩን ይነካካል። አንዷ ቆንጆ ሳያስበው፣ “በፍቅር ያልሞተ ይሁዳ ብቻ ነው” ብሎ የጻፈውን ‘ላይክ’ አድርጋለት ተወዳጅነቱን ሊጨምር ተጨማሪ አባባል ፍለጋ የደላላ አዕምሮውን እንደ ባለቅኔ ያስጨንቃል። ድርጊቱ አናዶኝ፣ “ደላላነቴን ትቼ ‘ብሎገር’ ሆኛለሁ በለኝና እንረፈው። ሥራ እኮ ነው የምሰጥህ፤” ስለው፣ “ብራቮ አንበርብር” ብሎ “ኮሚሽን የማይመጥነው ሥራ ፍቅር ብቻ ነው፤” የሚል ጥቅስ እያየሁት ጻፈ። መስመር ላይ የነበረችው ከፊል እርቃኗን የሚያሳይ ፎቶ የለጠፈችው እንስት ‘ላይክ’ በማድረግ ፈንታ ‘ሎግ አውት’ አደረገች። ፊቱ አመድ መስሎ፣ “ምን አደረኳት?” አለኝ። አጠገቡ ቆሜ እንደሌለሁ ቆጥሮኝ ስለነበር እኔም ብድሬን ልመልስ፣ “‘ኮሚሽን’ ብለህ ደላላነትህን አስፎግረህ ነዋ?” ብዬ በቆመበት ጥየው ሄድኩ። የፈለገውን ያህል ቢሆን በጥሬው ፍለጋ የሚሯሯጥ ደላላ ይወደዳል ‘ላይክ’ የሚቆጥር ሊወደድ ያስባል እንዴ? ቀልደኛ!

ብዙ ሥራዎች ስለነበሩብኝ ቴሌቪዥኑን ቶሎ ብዬ ማሻሻጥ ነበረብኝ። ስልኬን ጥቂት ነካካሁና ስደውል ሞባይሌ ባዶ ኪስ እንደሆነች በትህትና ተነገረኝ። ድህነትዎ በትህትና ሲነገርዎ ግን እንዴት ደስ ይላል? ደስ አይልም? ወዲያው የ50 ብር ካርድ ገዝቼ ሞላሁ። “ለምን እንደሆነ አላውቅም ካርድ ስሞላ ደስ እንደሚለኝ ሆዴን ስሞላ ደስ ብሎኝ አያውቅም፤” የሚል ወዳጅ አለኝ። ሲተርቡት፣ “ሆድህ መቼም ሞልቶ ስለማያውቅ ይሆናል፤” ይሉታል። የትረባ ተርቦች ፊት ከመናገራችሁ በፊት እስኪ ሁለቴ ሦስቴ እያሰባችሁ። ለጥላቻ ቅርብ ስለሆነ እንደሆነ እንጃ ጥሎብን ‘መንግሥት መንግሥት’ እንላለን እንጂ፣ የመናገርና የማሰብ መብታችንን መጫኑ በእነሱ ይብሳል። ምን እያልኩ ነበር? አዎ — ካርድ ሞላሁና ወዲያው ያወጣሁትን ቁጥር ደወልኩ። የደወልኩለት ወዳጄ ሌላ ቁጥር ሰጠኝ። ስደውል “ይቅርታ ሒሳብዎ አልቋል” አለችኝ። ድምጿ የእምዬን ባይመስል? . . . ማርያምን ቴሌ አልቆለት ነበር። ምናለበት ደግሞ በይቅርታው ምትክ፣ “ጥሩ ተዘራፊ ሆነው በመገኘትዎ ዕድሜዎን ያርዝምልዎ እናመሰግናለን፤” ወዘተ ብባል። መጮህ አማረኝ። ዙሪያ ገባዬን ለአንድ አፍታ ሳጤን ቆይቼ . . . ከአንዱ ሱቅ በደረቴ ሌላ ካርድ ገዛሁ። ጠላቴ ሰፍ ብሎ ይቅርና!

  ክፍት እያለኝ ደስተኛ ለመምሰል እያታገልኩ የቴሌቪዥኑን ጣጣ ለሌላ ምስኪን ደላላ ሰጥቼ አንድ ካሚዎን ላሻሽጥ ተጣደፍኩ። መረባበሼ የተፀነሰው ሞት መፍራት አቆምኩ ባሉኝ ሰውዬ፣ የፀናሁት በአካል ቆሜ መልክ ባመለከው ወዳጄ፣ ግራ የተጋባበት በቴሌ አይሠሩ ሥራ መሆኑ ገብቶኛል። ጥቂት ሩጫዬን ገታ አድርጌ የጥሞና ጊዜ ለመውሰድ አንድ ካፌ በረንዳ ላይ ተቀመጥኩ። ምን አማረህ በሉኝ — እኔ የማልተውንበት በሌሎች ረቂቅ ተውኔት ተመስጬ ገሃዱን ዓለም የምረሳበት የልቦለድ ዓለም አማረኝ። ምነው? ነፍሰ ጡር አፈር አማረኝ ስትል አፈር ዛቂ ሁላ ‘እንዴት ተረት ያምርሃል?’ ልትሉኝ ባልሆነ። እንዲያው እኮ! ሲሆን ፍቅር እስከ መቃብርን የሚያስረሱ ብዙ ጸሐፍት ለምን አልተነሱም ብላችሁ ልትቆጩ ይገባ ነበር። እውነቴን ነው! ለነገሩ ምን ታደርጉ? ይኼ ፈጣን ልማትና ዕድገት ለማስመዝገብ ያለልክ የምንጋልበው ፈረስ ለፀፀት ፋታ የሚሰጥ አልሆነም። ማለቴ የሥነ ጽሑፍ ዕድገትን ለአንድ ሰማይ ጠቀስ (ሰማዩ ግን እንኳን የፎቅ የሰው ጥቅሻም የሚያይ አልመሰለኝ) ከሚቆም ኮለን ጋር የሚያወዳድር አልመሰለኝ። በበኩሌ ግን እቆጫለሁ። ይኼን ቁጭቴን ለባሻዬ ልጅ ሳካፍለው “እውነት ነው! አንዳንዴ እኮ ኑሮ ሲያዝል የገሃዱ ነፀብራቅ የረሱትን እያስታወሰ፣ የምንሸሸውን እውነት አባብሎ እየከለሰ የሚሰጠን ፋታ ቀላል አይደለም፤” ይለኛል። “አይ የተማረ!” እላለሁ። ለነገሩ የተማረ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ‘ያበላል’ እያሉ ከተማሩት ትውልዶች መሀል ስላልሆነም ጭምር ነው የጥበብን ነገር ሲመዝን የሚያረካኝ። የምር!

እና ያዘዝኩትን ቡና ሳላጋምስ የምናብ ታሪክ ናፍቆቴ ቀልድ መፍተል አስጀመረኝ። ነውር አለው? ከጉንጭ አልፋ ዲስኩር ከማይዘሉ፣ የሰው ልጆችን ችግር ከማባባስ በቀር ምድራዊ ገነትን በመፍጠር ፍካሬ ሲኦል ካደራጁ ርዕዮተ ዓለሞች ይልቅ፣ የእኔ ስላቅ ሳይሻላችሁ አይቀርም። እናም ጥቂት ከምር ኑሯችንን አብረን እንፎርፍ። ብዙ ጊዜ እንዳጫወትኳችሁ የዚህን ዓለም ነገር ሳስበው የመንደር የቡና ‘ሴሬሞኒ’ ይመስለኛል። መቼቱን መንደር በሉት ከፈለጋችሁ። እናም የአሜሪካ፣ የጣሊያን፣ የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥትና የእኛ ሥራ ፈተው ሥራ ሊፈጥሩ ቡና እየጠጡ ተቀምጠዋል አሉ። (ከቴም ከኑሮ መፎረፍ እቴ!) አሜሪካ ታወራ ታወራና (ወሬ የሐበሻ ብቻ ነው ያለው ኧረ ማን ነው?) የመሀላ ሰዓት ደረሰባት። የወሬ ማኅተሙ መሀላ አይደል? “ጆርጅ ዋሽንግተንን ይንሳኝ፤” አለች። ጣሊያን ‘ይህቺ ሞሳ ትናንት ድክ ድክ ብላ እንዳላሳደግናት ደግሞ’ ዓይነት እየገላመጠቻት የተራገበ አሉባልታ አውርታ (ሮማም አሉባልታ ታውቃለች፣ ከአዲስ አበባ ራስ ውረዱ እሺ!) “ዳቪንቺ ይሙት!” ማለት። ጋሽ ኢሳያስ አፈርወቂ ተራቸው ይደርሳል። መቼም የጦርና የነገር ሰው ሆናችሁ አንዴ አለመፈጠር ነው። የሚወራ አጡ። ግን አልጨነቃቸውም። ጭንቀትና ሰውዬው በእርጅናም የሚተዋወቁ አይመስሉም። ስለዚህ ያለመንደርደሪያ  “ሳዋን ይንሳኝ! ማን ምሎ ማን ይቀራል?” ብለው ወደ እኛ ሲገላመጡ፣ የእኛዎቹ አቦሉን ሳይጨርሱ ቶና፣ ቶናውን ሳይቀምሱ በረካው እንዲቀዳ እየወተወቱ (ጊዜው የፈጣን ልማትና ዕድገት ጊዜ መሆኑን ልብ ይለዋል) የሚያስምል ጨዋታ ላለመጫወት ሲጠነቀቁ ቆይተው አልሳካ አላቸው። ሊምሉ አሰቡ፣ ዓለሙ። መማያቸው በሁለት ሰይፍ የተሳለ ሆነና ግራ ገባቸው። ‘አብዮቴ ይሙት!’ እንዳይሉ አይታሰብም። ‘ዴሞክራሲን ይንሳኝ!’ ቢሉ ይኼ የቡና ወሬ አፈትልኮ ቢወጣስ? 99.9ኙን የፓርላማ መቀመጫ ውኃ በላው ማለት አይደል? ደፋርና ጢስ መውጫ አያጣ ሲሆን፣ “መማል የትምክህተኝነትና የጠባብነት መገለጫ ስለሆነ ከዚህ ወዲያ መማል አይጠቅምም!›› አሉ፡፡ ይህቺን ስላቅ ለባሻዬ የነገርኳቸው ቀን ታዲያ ምንም ፈገግታ ሳላይባቸው “ይኼ ሥልጣን ከእግዜር ካልሆነ ከማን ሊሆን ይችላል ታዲያ?” ብለው አፈጠጡብኝ። እሳቸው ደግሞ አንዳንዴ የሚናገሩትን አያውቁም ልበል!    

እንሰነባበት። ካሚዮኑን በቶሎ ለማሻሻጥ ተጣደፍኩ። አልፎ አልፎ ቢሆንም ምርጫ እንደደረሰለት የፖለቲካ ፓርቲ ዕቁብ ከተበላ በኋላ የምጣደፈው ነገር አለኝ። ማንጠግቦሽ ይኼን ዘገምተኝነት እንዳሻሽል ደጋግማ ብትነግረኝም፣ የምርጫ ሰሞን የመቀስቀስ አዝጋሚ ልምዳቸውን እንዲተው ስንነግራቸው የማይሰሙንን ፖለቲከኞች ይመስል አልሰማኋትም። በረባ ባረባው በጭቅጭቅና በአጉል ጥርጣሬ የጠፋውን ጊዜ የሚክስ ‘ኮሚሽን’ አስገኝቶልኝ ካሚዮኑ ሲሸጥ ስልኬ ጠራ። የጠፋ ሃምሳ ብር ካርዴን አግኝተውልኝ መስሎኝ ሳነሳው የጎረቤታችን ጐረምሳ የቁጠባ ቤት ዕጣ ደርሶት ፌሽታ መደረጉን ሰማሁ። የባሻዬ ልጅ፣ “ዛሬ ቢራ በነፃ የምንራጭበት ቦታ ተገኝቷል፤” ሲለኝ ወደ ሠፈሬ ከነፍኩ። እኔ ስደርስ ዕድለኛው ጎረምሳ ከሥራ ሲመለስ አንድ ሆነ። ቤቱ እስኪገባ እንደ መሲሁ ዘንባባ ተነጠፈለት። በዕልልታው ድምቀት መንደራችን በፌዴራል ፖሊስና እሳት አደጋ ተከበበች። ይኼን ያየ አንድ ተናጋሪ፣ “ይኼኔ የአንዳችን ቤት እሳት ይዞት ቢሆን ነገም አይመጡ፤” አለ። ሌላው ቀበል አድርጎ፣ “ምን ታውቃለህ በቅናት ለሚቃጠሉት ከሆነስ የመጡት?” ይለዋል። የባሻዬ ልጅ፣ “ስማ! ዝም ብለህ አዳምጥ፤” ይለኛል። ነገሩ ሌላ መስሏቸው ሰግተው የነበሩ ሰላም አስከባሪዎች ጫጫታው በሌላ ጎኑ የደስታ መሆኑ ስለገባቸው የደስታው አድማቂ ወደ መሆን ተገልብጠዋል። ‹‹አትገለባበጡና ዝም ብላችሁ ከንፈር ንከሱ›› ያትን ብታውቋቸው ኖሮ እኔን አትጠይቁኝም ነበር፡፡

 ጭብጨባውና ዕልልታው የቀዘቀዘ የመሰላቸው አንዲት ወይዘሮ ደግሞ፣ “አዳሜ በደንብ አታጨበጭቢም? ነግሬያለሁ የዛሬ አምስት ዓመት እንኳን ለቤት ለጭብጨባውም ላትቆሚ ትችያለሽ፤” ይላሉ። “ምንድነው እርስዎ ደግሞ የሚያስፈራሩን? ከዚህ በላይ እጃችን ይቆረጥ?” ሲል አንደኛው ሌላው ደግሞ፣ “እንዴ ሁለተኛው ዙር ዕጣ የሚወጣው የዛሬ አምስት ዓመት ነው ማለት?” ሲል ግራ ተጋብቶ ግራ ያጋባል። እንዲያው በአጠቃላይ በትንሽ ትልቁ ነገሩን ፖለቲካዊ አንድምታ ሊሰጠው የማይጥር የለም። ግርግሩ በረድ ብሎ እኔና የባሻዬ ልጅ ወደ ዕድለኛው ቤተሰብ ቤት ስንገባ ከየት መጡ ሳንላቸው ባሻዬ ከኋላችን ከች አሉ፡፡ ‹‹ትሰማላችሁ ሰው የሚለውን? ወይ ዕጣና ቁጠባ! የማያናግረን የለም እኮ፤” ብለውን ወደ ጓደኞቻቸው ተቀላቀሉ። እኛም ተገኘ ብለን ልንጋተው የነበረው ቢራ ገና ሁለተኛውን እንዳጋመስን ራሳችን ላይ ወጣ። ዕጣና ቁጠባ አንዱን በጉጉት ሲንጠው፣ ዕጣና ዕጣ ፈንታ ደግሞ በነፃ የተገኘን ሳይጠግቡት ይሸኛል። የአንዱ ዕጣ ዕድልን አንጠልጥሎ ሲያመጣ፣ የሌላው ዕጣ ደግሞ ከእጅ የገባ ያስወጣል፡፡ ዕጣ ፈንታ ሆኖ ከላይ ታች ይለናል ማለት ይኼ ነው፡፡ መልካም ሰንበት!       

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት