Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅ‹‹ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ ታክሲም እንደ ሰው ይናፍቃል ወይ››

‹‹ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ ታክሲም እንደ ሰው ይናፍቃል ወይ››

ቀን:

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት የሔደው የአዲስ አበባ የትራንስፖርት እጥረት ኅብረተሰቡን ከሥራው፣ ከትምህርቱ እና ከጉዳዩ እያስተጓጐለው ነው፡፡በፎቶው ላይ የሚታየው ከወትሮው የተለየ ረዥም ሠልፍ በካዛንቺስ አካባቢ መጋቢት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. የታየ ነው፡፡ እስከ ረፋዱ 4፡00 ሰዓት ብዙዎች ወደ ትምህርት ቤት፣ መሥሪያ ቤት እና ወደጉዳያቸው ለመንቀሳቀስ አልቻሉም፡፡ በሌሎችም የአዲስ አበባ አካባቢዎች ሜክሲኮ አደባባይ፣ ተክለሃይማኖት፣ ፒያሳ፣ ሳሪስ አቦ ወዘተ. ተመሳሳይ ችግሮች ታይተዋል፡፡ መፍትሔው መቼ ይሆን!? 

********

አልመጣም

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

      ምንም ያህል ብርሃን ቢሆን

            መቅረዝ ባይለይም ከእጄ

      የማይነጋ ቀን አለ

            ልምጣ ብል እንኳ ፈቅጄ

      የማላቋርጠው በዋና

            የማልሻገረው በታንኳ

      የማላልፈው ባህር አለ

            ምንም ብወድህ እንኳ

      ዓይኖችህን ማየት ብናፍቅ

            አንተነትህ ከ’ኔ ርቆ

      ላልችል አልሞክር  ለማለፍ

            ከፊቴ ያለውን ሸለቆ

      በምኞት ፈረስ ስሰግር

            ልደርስብህ ስንጠራራ

      መንገዴ ላይ ተጋረጠ

            ችዬ የማልወጣው ተራራ

      የቱንም ያህል ብወድህ

            የኔ ላደርግህ ብሻ

      ብገባ የማልወጣበት  

            ይታየኛል ትልቅ ዋሻ

አትጠብቀኝ ውዴ!

ይቅር አትጠብቀኝ

ችዬ አልመጣም እዚያ ማዶ

እግሬ ቢሄድ ወደ ሌላ

ልቤ ይኑር አንተን ወ‘ዶ፡፡

ሜሮን ጌትነት ‹‹ዙረት›› (2006 ዓ.ም.)

*******

የመግቢያ ዋጋ

የእንግሊዝና የስኮትላንድ እግር ኳስ ቡድኖችን ግጥሚያ ለመመልከት ተመልካቹ ወደስቴዲየም እየገባ ነበር፡፡ ስኮትላንዳውያኑ ወንድማማቾች ውድድሩን ለመመልከት ስለፈለጉ ትኬት ቆራጩን፣ ‹‹የመግቢያ ዋጋው ስንት ነው?›› ሲሉ ጠየቁት፡፡

‹‹ሃያ ፓውንድ ነው››

‹‹እኔ እንደምታየው አንድ ዓይና ስለሆንኩ አሥር ፓውንድ ነው የምከፍለው ማለት ነው›› አለ አንደኛው፡፡ ትኬት ቆራጩ ስላዘነለት አስገባው፡፡

ይኸኔ ታናሽ ወንድምየው ተከትሎ፣ ‹‹እኔም አሥር ፓውንድ ነው መክፈል ያለብኝ›› አለ፡፡

‹‹አትቀልድ እንጂ፣ ሰውዬ! ሁለት ዓይንኮ ነው ያለህ፡፡››

‹‹ልክ ነህ ሁለት ዓይኖች ነው ያሉኝ፡፡ ሆኖም የምገባው የስኮትላንድ ቡድንን ብቻ ለመመልከት ነው፡፡››

********

ዓሳ ጐርጓሪ

ውሻው ደንዲ ከተማ (ስኮትላንድ) የሚገኝ ሥጋ ቤት ዘሎ ገብቶ ሊቆረጥ ከተደረደረው ሥጋ በቅርቡ ያገኘውን መንትፎ ይሄዳል፡፡ ውሻው፣ የጠበቃው ጎረቤቱ መሆኑን ያወቀው ባለ ሥጋ ቤት ስልክ ደውሎ ‹‹ውሻህ ከልኳንዳዬ ለጥብስ የሚሆን ምርጥ ሥጋ በመስረቁ ለደረሰብኝ ኪሳራ ተጠያቂ ትሆናለህ ወይ?›› ሲል ይጠይቀዋል፡፡

‹‹በሚገባ እንጂ፤ ለመሆኑ የሥጋው ዋጋ ስንት ነው?››

‹‹ሰባት ፓውንድ ነው›› አለ ባለሥጋ ቤቱ ተደስቶ፡፡

ከጥቂት ቀናት በኋላ ለባለ ሥጋ ቤቱ በፖስታ ቤት በኩል የሰባት ፓውንድ ቼክ ደረሰው፡፡ ከቼኩ ጋርም ‹‹ለምክር አገልግሎት የተጠየቀ ሒሳብ፤ 150 ፓውንድ›› የሚል ኢንቮይስ ተያይዞ ነበር፡፡

  • አረፈዓይኔ ሐጐስ ‹‹የስኮትላንዳውያን ቀልዶች›› (2005)

*******

ፍሎሪዳን ያሰጋ ምስጥ

በዓለም በአጥፊነታቸውና በፈጣን ተመጋቢነታቸው ከሚታወቁት ምስጦች መካከል በሳይንሳዊ መጠሪያቸው ካፕቶትሪመስ ፎርምሳነስ እና ካፕቶትሪመል ጀስትሮይ የተባሉ ዝርያዎች በአሜሪካ ለፍሎሪዳ ግዛት ሥጋት መፍጠራቸው ተሰምቷል፡፡

ምስጦቹ እየተባዙና የራሳቸውን (Colony) በቡድን የመኖር ሥርዓት እየዘረጉም ነው፡፡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ምስጦችም ለ20 ዓመታት ያህል በቡድን መኖር የሚችሉ ሲሆን ይህም በፍሎሪዳ ውስጥ የሚገኙ ቤቶችን ሥጋት ውስጥ የሚጥል ነው ተብሏል፡፡ በፍጥነት የሚራቡትና ቡድናቸውን የሚመሠርቱት ምስጦች የሚያደርሱት ጥፋት ከባድ መሆኑ ለፀረ ተባይ ባለሙያዎችም ሥጋት መሆኑን በፍሎሪዳ ፎርት ላውልራዳል የትምህርትና የጥናት ማዕከል ዘግቧል፡፡

********

የማስታወስ ችሎታን ለማሻሻል

በጀመርመን ሰርላንድ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች በቀን ከ45 እስከ 60 ደቂቃዎች መተኛት የማስታወስ ችሎታን በአምስት እጥፍ እንደሚያሳድግ በጥናት ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ኒውሮሎጂ ኦፍ ለርኒንግ ኤንድ ሚሞሪ›› በሚል ጆርናል ላይ የሰፈረው ጥናት እንደሚያሳየው ሰዎች በሥራ ቦታ ለአንድ ሰዓት ያህል ቢተኙ በሥራቸው የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ በትምህርት ቤቶች ውስጥም ተማሪዎች ጥቂት የመተኛ ሰዓት ቢኖራቸው የመማርና የማስታወስ ችሎታቸው በአምስት እጥፍ የሚያድግ ይሆናል፡፡

*********

በምግብ ሥጋ የሚከማች ፀረ ተዋህስያን መድኃኒት

ፀረ ተዋህስያን (አንቲባዮቲክስ) በሰዎች ላይ መለማመድ እየፈጠሩ መሆኑ ከተነገረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በናሽናል አካዳሚ ኦፍ ሳይንስ ጆርናል እንደሰፈረው ደግሞ በቀጣዮቹ 15 ዓመታት አገሮች ለከብቶች የሚጠቀሟቸው ፀረ ተዋስህያን በእጅጉ የሚጨምሩ ሲሆን ይህም ሥጋ ለሚመገቡ ሰዎች አደጋ ነው፡፡ ቀድሞውንም በሰው ልጆች ላይ መለማመድ እየፈጠረ የሚገኘው ፀረ ተዋህስያን መድኃኒት ሥጋ ከመመገብ ጋር ተያይዞ በሰዎች ላይ የሚያደርሰውንም አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድገዋል፡፡

ለከብቶች የሚሰጥ መድኃኒት በዓለም አቀፍ ደረጃ በፈዋሽነታቸው የሚመሰከርላቸውን ፀረ ተዋህስያን የበለጠ እንዲለማመዱና የሰው ልጆችን አደጋ ላይ እንዲጥሉ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የዩፒአይ ዘገባ ያሳያል፡፡

********

እሳት ውኃ እውነትና ሐሰት

በመርጋ ደበሎ የተተረከ የኦሮሞ ተረት

እሳት፣ ውኃ፣ እውነትና ሐሰት ጓደኞች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሐሰት በዚህ ጥምረት ደስተኛ ስላልነበረ አንድነታቸውን ማበላሸት ፈልጎ እንዲህ አለ “ለምን ወደ አንድ ሥፍራ ተጉዘን እያንዳንዳችን የራሳችንን ግዛት አንመሠርትም? ስለዚህ ተነስተን አብረን እንጓዝ፡፡”

ሁሉም በሐሳቡ ተስማምተው ሲሄዱ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሐሰት ወደ ውኃ ጠጋ ብሎ “እሳት ሳሩን፣ ደኑንና ቁጥቋጦውን የሚያቃጥል ቀንደኛ ጠላታችን ስለሆነ ለምንድነው ከእርሱ ጋር ግዛት ፍለጋ የምንሄደው?” አለው፡፡

ውኃም “ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?” አለ፡፡

ሐሰትም ቀበል አድርጎ “ልንገድለው እንደሚገባ ግልጽ ነው፡፡ እሳትን የማጥፋት ብቸኛ ኃይል ያለህ ደግሞ አንተ ነህ፡፡ እናም ቁጭ ሲል ጠብቀህ እላዩ ላይ ራስህን በመርጨት አጥፋው፡፡” አለው፡፡

ውኃም “ራሴን መሬቱ ላይ ከረጨሁ ተመልሼ ውኃ መሆን አልችልም፡፡” አለ፡፡

ሐሰትም “ችግር የለውም፡፡ ተረጭተህ እንዳትበታተን የተወሰኑ ድንጋዮች በዙሪያህ አኑርና በኋላ እሰበስብሃለሁ፡፡” አለው፡፡

በዚህ ጊዜ ያልጠረጠረው እሳት መጥቶ ቁጭ ሲል ውኃው አንድ ጊዜ በላዩ ላይ ሲረጭ ሐሰት ድንጋዮች ዙሪያውን አድርጎ ውኃውን ከሰበሰበውና እሳትን ካስወገዱ በኋላ

አብረው መጓዝ ጀመሩ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሐሰት ውኃውን “ለምን እዚህ ገደል አፋፍ ላይ ቁጭ ብለህ በተፈጥሮ ውበት አትዝናናም?” አለው፡፡

ውኃም አፋፉ ላይ ቁጭ ሲል ሐሰት ቀስ ብሎ ተነስቶ ውኃ የተቀመጠባቸውን ድንጋዮች ከሥሩ ሲለቅማቸው ውኃው በመረጨት በዚያው ተበታትኖ ጠፋ፡፡

በመጨረሻም ሐሰት እውነትን ማጥፋት ነበረበትና ወደ አንድ ትልቅ ተራራ በተቃረቡ ጊዜ ሐሰት እውነትን ከተራራው ግርጌ ቁጭ በል ብሎት ከተራራው አናት ላይ ትልቅ አለት ቁልቁል በመልቀቅ እውነትን ሊጨፈልቀው ሲል እውነት ቀልጠፍ ብሎ ማምለጥ በመቻሉ አለቱ ተንከባሎ ሲፈረካከስ ከውስጡ አልማዝ፣ ወርቅና ልዩ ልዩ የከበሩ ማዕድናት ወጡ፡፡ ሐሰትም የእውነትን አስከሬን ሊመለከት በመጣ ጊዜ እነዚህን ሁሉ የከበሩ ድንጋዮች አየ፡፡

እናም “እነዚህ ሁሉ ከየት መጡ?” ብሎ ጠየቀ፡፡

እውነትም “አለቱ እላዬ ላይ ሲወድቅ እነዚህ ማዕድናት ወጡ፡፡” አለው፡፡

በዚህ ጊዜ ሐሰት “አሁን ደግሞ እኔ ከተራራው ግርጌ ልቀመጥና አንተ አለቱን በላዬ ላይ ልቀቅብኝ፡፡” አለው፡፡

እናም እውነት ወደ ተራራው ጫፍ ወጥቶ ትልቅ አለት ወደታች በለቀቀ ጊዜ አለቱ የሐሰት አናት ላይ አርፎ ሐሰትን ጨፈላልቆ ገደለው፡፡ ይህ የሚያሳየው እውነት ፈተና ቢገጥመውም በመጨረሻ አሸናፊ መሆኑን ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...