Friday, December 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ኖህ ሪል ስቴት የሰባት ሚሊዮን ብር ቪላዎችን አስረከበ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ኩባንያው ከተመሠረተ ገና አምስት ዓመት እንደሆነው ቢነገርም፣ ከወዲሁ በመኖሪያ ቤትና በሕንፃ ግንባታ ሥራዎች ላይ እየተስፋፋ መምጣቱ ይነገርለታል፡፡ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ባለ13 ፎቅ አቢሲንያ ፕላዛ በሚል ሥያሜ ለሆቴልነት ካዋለው ሕንፃ ባሻገር ከቀናት በፊት 16 ቪላ ቤቶችን ሠርቶ ያስረከበበትን ሥነ ሥርዓት አከናውኗል፡፡

  የአንዱ ቪላ ዋጋ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነበትና ‹‹ጀምበር መንደር›› የሚል መጠሪያ በሰጠው በሲኤምሲ አካባቢ ግንባታው፣ በራሱ ወጪ የገነባቸውን ቤቶች ካጠናቀቀ በኋላ ለገዥዎች ማስረከቡን የኖህ ሪል ስቴት ሥራ አስኪያጅ አቶ ብዙነህ ታደሰ ገልጸዋል፡፡ መጋቢት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲኤምሲ፣ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ጀርባ የተገነቡት ቤቶች ለገዥዎች መተላለፋቸውን በማስመልከት የተካሔደ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው 16ቱም ቪላዎች ተሸጠው አልቀዋል፡፡

  ኖህ ሪል ስቴት እስካሁን ከተለመደው የቤት አልሚዎች ከሚጠይቁት የአከፋፈል ስልት የተለየ አካሔድ መከተሉን አቶ ብዙነህ ይናገራሉ፡፡ ይኸውም በራሱ ገንዘብ ቤቶቹን ገንብቶ ካጠናቀቀ በኋላ ለሽያጭ በማቅረብ አቅሙ ያላቸው ወዲያውኑ ከፍለው እንዲረከቡ ማድረጉ ነው፡፡ እስካሁን በአብዛኞቹ ሪል ስቴቶች ዘንድ የሚተገበረው አሠራር በቤቶቹ ግንባታ አካሔድ ደረጃ የሚጠየቅ የክፍያ ሥርዓት መኖሩ ነው፡፡ መሠረት ሲወጣ፣ መሠረት ሲጠናቀቅ፣ ግንባታው አጋማሽ ሲደርስ፣ ሊያልቅ ሲሦ ሲቀረውና፣ ፊኒሺንግ ወዘተ. ደረጃዎች ላይ የሚከናወን የክፍያ ሥርዓት ሲኖር፣ ሌሎች ጥቂት የማይባሉት ደግሞ ሙሉ ክፍያ ወይም ግማሽ ክፍያ አስቀድመው በመሰብሰብ ግንባታ እንደሚያከነውኑ ይታወቃል፡፡ ይህ አሠራር ግን በቅርቡ በወጣው የሪል ስቴት ግንባታ ሕግ መሠረት የተወሰነ ለውጥ እንዲደርግበት ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡ ይኸውም ማንኛውም ቤት አልሚ ቢያንስ መሠረት ሳያወጣ መሸጥ እንዳይጀምር የሚያስገድድ ሕግ በመምጣቱ ምክንያት ነው፡፡ መንግሥት ወደዚህ ዕርምጃ የመጣው፣ በሪል ስቴት ኢንዱስትሪው ላይ የታዩ ችግሮች ስላስገደዱት ነው፡፡ በርካታ ቤት ገዥዎች ቅድሚያ ክፍያ ፈጽመውም ለዓመታት ቤት ማግኘት ሳይችሉ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡

  በዚህ ምክንያት ይመስላል ጥቂት ቤት አልሚዎች በራሳቸው ገንዘብ ግንባታ አካሒደው ካጠናቀቁ በኋላ ቤቶቹን ለገዥዎች እጅ በእጅ መሸጡን የመረጡት፡፡ ከእነዚህ ሪል ስቴቶች አንዱ የሆነው ኖህ ሪል ስቴት ‹‹ያልተገነባ አንሸጥም፤›› የሚል መፈክር እያስተጋባ ይገኛል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ግንባታቸው ተጀምሮ የተጠናቀቁትንና በአንድ ወጥ ዲዛይን የገነባቸውን ቪላዎች አስረክቧል፡፡ በአማካይ ከ200 እስከ 250 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፉ ቤቶች ገንብቶ ከመሸጥ ባሻገር፣ አትላስ ሆቴል፣ ለንደን ካፌ አካባቢ የ200 አፓርታማ ቤቶችን ሕንፃ ግንባታን በቅርቡ ዕውን እንደሚያደርግ አቶ ብዙነህ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ቀደምም ቦሌሚኒ አካባቢ ግንባታ አከናውኖ ያስረከባቸው ቤቶች እንዳሉም ሥራ አስኪያጁ አስታውሰዋል፡፡

  ኖህ ሪል ስቴት በግሬት አቢሲንያ ኩባንያዎች ባለንብረቶች የተመሠረተ የግል ኩባንያ ነው፡፡ ግሬት አቢሲንያ ከሚያቅፋቸው ኩባንያዎች መካከል አቢሲንያ ውኃ፣ አቢሲንያ ቡና፣ አቢሲንያ ሻይ እንዲሁም ቴክኖ ፕሪንተርስ ይካተታሉ፡፡ ፕሪጋት ጁስን ጨምሮ ልዩ ልዩ ለስላሳ መጠጦችን በማምረት ላይ የሚገኙት የግሬት አቢሲንያ እህት ኩባንያዎች  የሆቴል ንግድ ሥራንም እየተቀላቀሉ ነው፡፡

   

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች