Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊ​​​​​​​በመኖርያ ቤቶች ግንባታ ለመሳተፍ ጥያቄ ያቀረቡ የውጭ ኩባንያዎችን ለማስተናገድ የፖሊሲ ጥናት እየተካሄደ...

​​​​​​​በመኖርያ ቤቶች ግንባታ ለመሳተፍ ጥያቄ ያቀረቡ የውጭ ኩባንያዎችን ለማስተናገድ የፖሊሲ ጥናት እየተካሄደ ነው

ቀን:

የውጭ ግዙፍ ኩባንያዎች በአዲስ አበባ ከተማ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ጥያቄ እያቀረቡ ቢሆንም፣ መንግሥት የውጭ ኩባንያዎችን ለማሳተፍ የፖሊሲ አቋም ባለመውሰዱ ኩባንያዎቹ መሳተፍ የሚችሉበት የፖሊሲ ጥናት እየተካሄደ መሆኑ ታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት የውጭ አገር ኩባንያዎች የሚያቀርቡትን ጥያቄ ለማስተናገድ የሚያስችለው የፖሊሲ ጥናት እያካሄደ ነው፡፡

‹‹የፖሊሲ ውሳኔ ለመወሰን በአገር አቀፍ ደረጃ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጥናት እየተካሄደ ነው፤›› ያሉት ከንቲባ ድሪባ፣ የኩባንያዎቹ ጥያቄ ጥናቱ እንደተጠናቀቀ እንደሚስተናገድ አስታውቀዋል፡፡

- Advertisement -

ከንቲባ ድሪባ እንዳስረዱት፣ እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ራሱን የቻለ ከተማ የመገንባት ፍላጎት አላቸው፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ኩባንያዎች ሕዝቡ ምን ይጠቀማል? የቤቶቹ ገዥ ማነው? ሽያጩ እንዴት ይከናወናል? ሕዝቡስ የመግዛት አቅም አለው ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ሊያገኙ ይገባል ብለዋል፡፡

‹‹መንግሥት የፖሊሲ ውሳኔ ካሳለፈ አዲስ አበባ ከተማ ለኩባንያዎቹ ምላሽ በመስጠት የመጀመርያ ይሆናል፤›› ሲሉ ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

ከንቲባው ጨምረው እንዳሉት፣ እስካሁን እየተካሄዱ ባሉት የመኖርያ ቤቶች ልማት ፕሮግራሞች ውስጥ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል አገር በቀል ኩባንያዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

መንግሥት አገር በቀል ኩባንያዎች በሪል ስቴት ዘርፍ ተሰማርተው ትርፍ ካገኙ በኋላ ያገኙትን ትርፍ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፉ እንዲያውሉት የማድረግ ፍላጎት አለው፡፡ ‹‹የከተማ አስተዳደሩም ፍላጎት ይህ ነው፤›› ብለዋል ከንቲባው፡፡

ሪፖርተር በተደጋጋሚ እንደዘገበው አሥር ያህል የቻይና፣ የአውሮፓ፣ የአሜሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ ግዙፍ ኩባንያዎች በአዲስ አበባ ከተማ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ቤቶችን ለመገንባት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ኩባንያዎቹ የመጀመርያ ጥያቄ እንዲያቀርቡ የተመቻቸላቸው በከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በኩል ነው፡፡ ሚኒስቴሩ በሥሩ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አማካይነት የኩባንያዎቹን የቴክኖሎጂ ብቃትና የፋይናንስ አቅም ከመረመረ በኋላ ቦታ እንዲሰጣቸው ለአዲስ አበባ ከተማ ድጋፉን ሰጥቶ ነበር፡፡

ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እነዚህን ኩባንያዎች ለማስተናገድ የፖሊሲ አቅጣጫ እንዲሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ አቅርቧል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ከራሱ፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርና ከከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተውጣጡ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ኮሚቴ አቋቁሞ ጉዳዩን በማጥናት ላይ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዚህ ጎን ለጎን በራሱ አቅም በሚያካሂደው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ዘርፍ የውጭ ኩባንያዎችን ለማሳተፍ ውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡ ከንቲባ ድሪባ እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ በየዓመቱ መኖርያ ቤቶች የመገንባት ፍላጎቱ ጨምሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓመት 65 ሺሕ ቤቶች የመገንባት አቅም ቢፈጥርም፣ በ2005 ዓ.ም. የቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ከተካሄደ በኋላ የነዋሪዎች እውነተኛ የቤት ፍላጎት በመለየቱ፣ የውጭ ኩባንያዎችን በማሳተፍ በፍጥነት ችግሩን መፍታት እንደሚገባ ውሳኔ ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡

እነዚህን ኩባንያዎች የመምረጡ ኃላፊነት ለቤቶች፣ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተሰጠ ሲሆን፣ ሚኒስቴሩ በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አማካይነት ባወጣው ጨረታ 28 ኩባንያዎች ተሳትፈዋል፡፡ ጨረታው በሒደት ላይ ሲሆን፣ የተመረጡትን ኩባንያዎች በፍጥነት ወደ ሥራ ለማስገባት መታሰቡን ከንቲባው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...