Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊለነዋሪዎች በሚተላለፉ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ተደረገ

ለነዋሪዎች በሚተላለፉ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ተደረገ

ቀን:

በኮንስትራክሽን ግንባታ ዋጋ ንረት ምክንያት መጋቢት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ለተጠቃሚዎች በሚተላለፉ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ቀድሞ በነበረው ዋጋ ላይ ከ15 እስከ 20 በመቶ ጭማሪ ተደረገ፡፡

በኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ የተደረገው የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ዋጋ ከፍ በማለቱና የሰው ኃይል ክፍያ በመጨመሩ ምክንያት እንደሆነ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ገልጸዋል፡፡

መጋቢት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. 35 ሺሕ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ለተጠቃሚዎች እንደሚተላለፉ ከንቲባ ድሪባ ባለፈው ዓርብ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 7,000 ኮንዶሚኒየም ቤቶች በልማት ምክንያት ለሚፈናቀሉ ነዋሪዎች እንደሚሰጡ ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

ለተጠቃሚዎች የሚተላለፉት ቤቶች ከ95 በመቶ በላይ የተጠናቀቁ መሆናቸውን፣ ለተጠቃሚዎች እስኪተላለፉ ድረስ ባለው አጭር ጊዜ ግንባታቸው መቶ በመቶ እንደሚጠናቀቅ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተገልጿል፡፡ ቤቶቹ የተገነቡት በስምንት ሳይቶች ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ባሻ ወልዴ ችሎት፣ የካ አባዶ፣ ቱሉ ዲምቱ፣ ልደታና ቃሊቲ ገነት መናፈሻ ይገኙበታል፡፡

ዕጣው በአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቴአትር አዳራሽ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት የሚወጣ ሲሆን፣ በኮምፒዩውተር የታገዘ ዘመናዊ የዕጣ አወጣጥ ሥርዓት መዘርጋቱን ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

የኮንዶሚኒየም ቤቶቹ ዕጣ በሚወጣበት ወቅት 20 በመቶ ለመንግሥት ሠራተኞች፣ 30 በመቶ ለሴቶች እንደሚሆን፣ ቀሪው 50 በመቶ ደግሞ ለአጠቃላይ ተመዝጋቢዎች እንደሚወጣ ከንቲባው አስረድተዋል፡፡

አቶ ድሪባ እንደተናገሩት፣ የኮንስትራክሽን ዋጋ እየናረ በመሄዱ ምክንያት የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ ይኖራል፡፡ ይህ ጭማሪ ሊኖር የቻለው ከውጭ የሚገቡ የኮንስትራክሽን ዕቃዎች የተገዙበት ዋጋ ከፍ ያለ በመሆኑና ለሰው ኃይል በጉልበትም ሆነ በዕውቀት የሚከፈው ገንዘብ ከፍ ያለ በመሆኑ ነው፡፡

ከንቲባው እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት በሪል ስቴት አልሚዎች ቤቶች በአማካይ በካሬ ሜትር ከ16,000 እስከ 24,000 ብር ይሸጣሉ፡፡ ነገር ግን በኮንዶሚኒየም በተለይም 10/90 ቤቶች በካሬ ሜትር ከ2,000 ብር በታች እንደሆነና 20/80 ደግሞ 3,000 ብር አካባቢ ነው ብለዋል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ መንግሥት መሬት በነፃ በማቅረቡና የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በማሟላቱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ጭማሪው ቀድሞ ከተገለጸው የዋጋ መጠን ከፍተኛ የሚባል ለውጥ እንዳለው እየተነገረ ነው፡፡ የቤቶቹ ዋጋ ካለፉት ስምንተኛና ዘጠነኛ ዙር ለዕድለኞች ከተላለፉት ቤቶች ዋጋ ከ15 እስከ 20 በመቶ ጭማሪ አለው፡፡ ጭማሪው መነሻ ያደረገው በልደታ መልሶ ማልማት ላይ የተካሄዱ ኮንዶሚኒየም ቤቶች በተላለፉበት ዋጋ ላይ ተመሥርቶ የተሰላ ነው ሲሉ፣ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግሥቱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረት ለ10/90 ቤቶች በካሬ ሜትር 1,910 ብር፣ ለ20/80 ስቱዲዮ 2,483 ብር፣ ለ20/80 ባለአንድ መኝታ ቤት 3,438 ብር፣ ለ20/80 ባለሁለት መኝታ ቤት 4,394 ብር፣ ለ20/80 ባለሦስት መኝታ ቤት 4,776 ብር መሆኑን አቶ መስፍን አስረድተዋል፡፡

በ20/80 ቤቶች ፕሮግራም ከተመዘገቡት 134,099 ነዋሪዎች በትክክል የቆጠቡት 81,037 ነዋሪዎች ሆነው በመገኘታቸው፣ ዕጣው ለእነዚሁ ተመዝጋቢዎች እንደሚወጣ ታውቋል፡፡

በሁሉም የመኖሪያ ቤቶች ፕሮግራም 12 ቢሊዮን ብር መቆጠቡን ከንቲባ ድሪባ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በትክክል እየቆጠቡ ያሉ ተመዝጋቢዎችን ለማበረታታት ሲባል ቁጠባ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለስድስት ወራት ያህል የቆጠቡ ተመዝጋቢዎችም በዕጣው እንደሚካተቱ ተመልክቷል፡፡

በዕጣው 1,000 ቤቶች ለ10/90 ፕሮግራም የሚወጡ ሲሆን፣ በዚህ ፕሮግራም እየተካሄደ ያለው ግንባታ በዚህ ዓመት መጨረሻ ሙሉ በመሉ ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች እንደሚተላለፍ ተመልክቷል፡፡

በዚህ ዕጣ 40/60 ፕሮግራም ባይካተትም፣ በዚህ በጀት ዓመት መጨረሻ 1,292 ቤቶች ለተጠቃሚዎች እንደሚተላለፍ ከንቲባው አስረድተዋል፡፡ እነዚህ ቤቶች ሰንጋ ተራ፣ ቃሊቲና ክራውን ሆቴል አካባቢ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከተጀመረ አሥር ዓመታት ባስቆጠረው የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ እስካሁን ድረስ 136,000 ቤቶች ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል፡፡

ነገር ግን የቤት ፈላጊዎች ፍላጎትና ኮንዶሚኒየም ቤቶች እየተገነቡ ያለበት ፍጥነት የማይገናኝ በመሆኑ መንግሥት የውጭ ኩባንያዎች እንዲገቡ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ እነዚህን ኩባንያዎችን የመምረጥ ኃላፊነት የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የወሰደ ሲሆን፣ ይኼንንም በሥሩ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ የተወዳደሩ 28 ኩባንያዎችን በመገምገም ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከንቲባ ድሪባ እንዳሉት፣ የአሁኖቹ የሚተላለፉት ቤቶች ከ500,000 በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ፡፡ ዘመናዊ አሠራር የተዘረጋ በመሆኑም እነዚህ ቤቶች በቀጥታ ለባለዕድለኞች የሚተላለፉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...