Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሰው መሆን በቂ ነው!

እነሆ መንገድ! ከቦሌ ድልድይ ወደ ሳሪስ ልንጓዝ ነው። ይህ እንደ ቀልድ ታስበን እንደ ሐምሌ ጎርፍ የሞላነው ጎዳና ‘ዛልዬ ዛልዬ ጣል ጣል አታርጊኝ፣ ያላንቺ ማን አለኝ?’ የሚፏጭበት አልሆነም። ራስን ችሎ መጓዝ፣ ጥርኝ የምታህል መቀመጫ ታድሎ በታክሲ መሸኘት ብርቅ የሆነበት ነው። ትናንት በአውቶሞቢል አሽከርካሪ እንዳልተቀና ዛሬ ‹‹ሳይሻገር ወራጅ አለ›› በሚል የሚቀናበት ሆኗል። ሐሳብ እንደ ሸቀጥ ክቡሩን የሰው ልጅ በነፈሰው አቅጣጫ እያንገዋለለ በባዶ ሲያበጥረው ለመታዘብ የመላዕክትን ጥበብ የአምላክን ጥሞና አይጠይቅም። ሰው መሆን በቂ ነው። በግል ፍላጎት በራስ ትርፍና ኪሳራ ተጋርደው በተጓዙበት ሁሉ ገንዘብ ቁም ነገራቸው፣ ሀብት ቅዠታቸው ለሆኑ ምናልባት በዚህ የትዝብት ዜማ እንዲሳተፉ አይገደዱም። ይህም በከንቱ የመባዘን የሰው ልጆች ችግር፣ የላዩን ታች የታቾችን ላይ በማድረግ በመደብ ትግል አይፈታም። የሚፈታው በመንገድ ብቻ ይመስላል።

መንገድም ይኼን አውቆ ግድ አልባዎችን ከጭቆኖች ጋር ደባልቆ፣ ከኅብረት እሳቤ ይልቅ ራስ ተኮር ርዕዮተ ዓለም ያላቸውን አግንኖ፣ በጥልቅና ስምጥ የሕይወት ባህር ውስጥ ያስቀዝፈናል። ስሜት በሚያጭር እምነት የሆነውን ነኝ ብሎ የተቀበለ እግረኛ እግር የሌለው እያየ ይፅናናል። መከናወንን በቁስ የሚመዝን ደግሞ በአራት እግር ጋሪ እየተጋፋ እግረኛ ባለመሆኑ ይፅናናል። ምናልባት ደግሞ ይኼን በከተሜ ባህሪ ወስኖ ንቆ ማለፍ ይቻላል። በሥልጣኔ ፍቺ ፍሬ ልልቀም ለሚል ግን ሁሉን ንቆ መመነንን ያስመኛል። ያስቻለው በሠልፍ ውስጥ አብሮ እየተራመደ፣ አብሮ እየተቆጠረ ልቡን የመፀየፍ ጠበል ያጠጣል። ይኼን ያህል መንገድ መጥተን፣ ዘመናትን የሚያሰላ የታሪክ ህልውና ጽፈን ግን ዛሬም ድረስ ለመሠረታዊ ፍላጎቶች ብቁ አለመሆናችን የሆነ የሚያሳክክ የመንፈስ ቁስል አለው። በዚህ አያያዛችንስ ስለመሠረተ ልማትና ስለምግብ እያሰብን የኖርነውን ያህል እንቀጥል ይሆን? ምኑን አውቀነው እናንተ!

‹‹ጫናቸው እንጂ! ካርድ በትነህ የጠራሃቸው እንግዶች አደረግካቸው እንዴ አሠልፈህ እጅ እጃቸውን የምታየው?›› ሾፌሩ ወያላው ላይ እየጮኸ ገብቶ ሞተር ያስነሳል። ‹‹የዘንድሮ ሰው ነው እጁ የሚታየው? እንኳን በባዶ በለበሰም ማመን ትተናል። ዕድሜ ለሰልባጅ!›› ወያላው በግብታዊ አስተያየቱ በድህነት ይፈርጀናል። ‹‹ምን ያድርግ በግለሰብ ቱማታ ሕዝብ አይመተር፡፡ ከኢኮኖሚስቶቻችን ጋር ተከራክረን ሳንጨርስ ደግሞ በዚህ ከወያላ ጋር እንጣላ? ጥቂቶች ሲያልፍላቸው ብዙኃን እያለፈባቸው እያየ ድሮስ አላቸው ሊለን ነው? ይበለን ግድ የለም!›› አንድ ጎልማሳ ያጉተመትማል። አንዱ አንድ ሲል ብሶት ድኟ የት እንደሚጋጭ ሳናይ እሳት እየተነሳ ማራገቡን ለምደነዋል። ‹‹ቢሆንም የወንድ ልጅ እጅና የሴት ልጅ ጣት አይናቅም። ሁለቱ ንዋይና ውበት ካልተጣመሩ ሕይወት ሙሉ አትሆንም፤›› ይላል ሾፌራችን። ታክሲዋን እያስጓራ ጋቢና ወደሚገቡት ጥንዶች ያያል። ‹‹ተሳሳትኩ?›› ሲላቸው ቆነጃጁቱ ሾፌሩን እያዩ እንዳልሰሙት ይነግሩታል። አስፋፍቶ ያለውን ይደግማል።

‹‹የትኛው ‘ሴንቸሪ’ ላይ ነው ያለኸው እባክህ? ዕድሜ ለዴሞክራሲ ሴት ልጅ የወንድ እጅ የምታይበት ዘመን ተሸኝቷል እሺ! ካስፈለገም ወንድም የምታይበትም ይሸኛል፤›› ትላለች አንደኛዋ እያንቀጠቀጣት። ‹‹ወዴት ወዴት ነው የምትንሸራተቱት እናንተ ደግሞ!›› ይላል ሾፌሩ ምን እንዳናደዳት አልገባው ብሎ። ‹‹ጉድ ነው! እኛ እዚህ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አልገባንም ብለን እጅ ስናወጣ አውርዱ እንባላለን፡፡ ‘ሊብራሊዝም’ በጎን ልባችን ጠብቶ ጨርሶት አረፈው እኮ? ለመሆኑ ምን እንደምታወራ ታስተውላለች?›› ስትል ከሾፌሩ ጀርባ ጎልማሳው አጠገብ የተሰየመች ወይዘሮ አፏን ትይዛለች። ‹‹ሥልጣን ማገልገያ እንጂ መገልገያ አይደለም። ኅብረተሰባዊነት አንዱ የሌላው መተሳሰቢያ መድረክ እንጂ፣ የራስን ደሴት ከልሎ ለመኖር መሽሎክሎኪያ ጥሻ አይደለም’ እያልን ጭራሽ ያለ አጋር ሊያስቀሩን ነው?›› ይላል ደግሞ ከኋላ የተቀመጠ ባለ ‘ዲሽ’ ጆሮ። ምነው ግን ሰው ነገር እንደሚስበው ሌላው ቢስበው ያስብላል!

ታክሲያችን መንቀሳቀስ ከጀመረች ደቂቆች ነጉደዋል። መነቋቆሩን ያስጀመሩት እጆች ሒሳብ ሊያወጡ እስኪቀደድ ኪሶቻችንን ይበረብራሉ። ወያላው ያጣድፈናል ‹‹ስንት የተቀበረ ጉድ አውጥተን ዘመኑ በፈጠረልን የመረጃ መረብ እየተወራረፍን ሦስት ብርና ሁለት ብር ጠፋችሁ?›› ይላል። መሀል መቀመጫ የተቀመጡ ተሳፋሪዎች ደግሞ የ‘እንዴት ይዞሃል? እንዴት አርጎሃል?’ ከረር ያለ ወህኒ ቤታዊ ሰላምታ ይለዋወጣሉ። ‹‹ኧረ አሳጥሩት በላቸው። እንኳን ሰላምታ መንገዱ እያጠረ፣ የሀብት ማማ ላይ መውጫ መሰላሉ እያጠረ (ፀሐዩ መንግሥታችን ወጥቶ ይጥለቅና) ሰላምታን እንዲህ ማስረዘም በእውነት ፀረ ልማታዊነት ነው፤›› ይላል አጠገቤ የተቀመጠ ቅብጥብጥ ወጣት። በዚህ መሃል ታክሲያችን ትርፍ ልትጭን ትቆማለች። ‹‹እሺ እዚህ ጋ ተሸጋሸጉ!›› አለን ወያላው። ‹‹ወዴት እንሸጋሸግ?›› መጨረሻ ወንበር ሽጉጥ ብላ የተቀመጠች ጠይም አይናማ ትጮኸበታለች። ‹‹ወደ ምትሸጋሸጉበት ነዋ። እናንተ አንተካካም ብላችሁ በ12 ሰው ገንዘብ አንድ ቢያጆ ሠርቼ መኖር የምችል ይመስልሻል? የምጣዶቹ እያሉ የእንቅቦች መንጣጣት አላሠራን አለን እኮ እናንተ?›› ሊፎክር ይቃጣል። ‹‹ወንበሩ እግር ሲያዘረጋ እኮ ነው የምንጠጋጋው። ና እስኪ እንዴት እንደተቀመጥኩ እየኝ…›› አጠገቤ ያለው ተሳፋሪ በስሜት መናገር ሲጀምር ሾፌሩ፣ ‹‹እንቢ ካሉህ በቃ ተዋቸው። ተጠጉ አትጠጉ፣ ውረዱ አትውረዱ ነው እኔስ አሁን ሊያሳብደኝ የደረሰው፤›› ብሎ ታክሲዋን ማንቀሳቀስ ጀመረ። ወያላው ትርፍ ተሳፋሪ ሳይደርብብን ጉዟችን ቀጠለ። አጠገቤ የተቀመጠው ተሳፋሪ፣ ‹‹እነዚህ ወያሎች ግን በለመደ አፋቸው አንድ ቀን የፓርላማ ተመራጮችን ሳይቀር ተጠጉ ባይሉ ውርድ ከራሴ፤›› ብሎኝ ዘለግ ያለ ሳቅ ሳቀ። ‘እኔስ አልስቅም አለቅሳለሁ’ ያለው ማን ነበር? ወይ መንበርና ወንበር!

ጉዟችን ቀጥሏል። ኩርፊያ የጀመረ ይመስላል፡፡ ወያላው ሒሳቡን ተቀብሎ ሲያበቃ ጎማ ላይ ተቀምጦ ሞባይል ስልኩን ይጎረጉራል። መሀል መቀመጫ ከረጅም ጊዜ በኋላ የተገናኙት ተሳፋሪዎች የግል ወሬ ጦዟል። ተሳፋሪው አድማጭ ሳይመስል እነሱን ይከታተላል። ‹‹ያ ማነው ስሙ ጠፋኝ የት ደረሰ? ትገናኛላችሁ?›› ይላል አንደኛው። ‹‹አልሰማህም እንዴ? ኖርዌይ ገባ እኮ…›› የወዲያኛው ይመልሳል። ‹‹ተው እባክህ! ተገላገለ በለኛ!›› እነሱ ከሚያውቁት የግል ችግሩ ይሁን ተወልዶ ካደገባት አገር፣ ከየትኛው እንደተገላገለ ፈጣሪ ያውቃል። ‹‹እና ደውሎልህ ያውቃል?›› ጠያቂው በጥያቄው ይገፋል። ‹‹አልፎ አልፎ። አንድ ቀን እንዲያውም ‘የኢትዮጵያን መንግሥት በመቃወም ሰላማዊ ሠልፍ ወጥቼ ወደ ቤት እየተመለስኩ ነው’ ብሎ ደውሎልኛል፤›› መላሹ መልሱን ይቀጥላል። ‹‹ማ እሱ ሰላማዊ ሠልፍ ወጥቶ? ሰው ሰላም ማለት የሚያፍር ልጅ እዚያ ሄዶ ሠልፍ ወጣ?›› ጠያቂው እጅግ ተገርሟል። ‹‹እኔም ገርሞኝ ጠይቄው ነበር። እንዲያውም ‘በተሠለፍክ ቁጥር መላ (ገንዘብ ማለቱ ነው) ይሰጣል ወይስ እግርህ ከአገር ሲርቅ የአገር ፍቅር ያቃጥልህ ጀመር?’ ስለው ‘አገሩን እስክለምድ ከአገሬ ልጆች ጋር ለመመሳሰል ነው’ አለኝ። አይገርምም?›› ይላል ስለተሰዳጁ በቂ መረጃ ያለው።

‹‹ጉድ ነው! እና በማስመሰልና በመመሳሰል ሆኗል በለኛ የዘመኑ የፖለቲካ ንቅናቄ አባልነት?›› ብሎ ጠያቂው ይስቃል። በዝምታ ሰጥመው ትንሽ እንደተጓዙ አንደኛው ‹‹ወራጅ›› አለ። ታክሲያችን ቆመች። ‹‹ና እስኪ ቤት ገባ ብለህ ትወጣለህ? በስንት ጊዜያችን ተገናኝተን እንዲሁ አትሂድ፤›› አለ ወዳጁ። ‹‹የለም ሌላ ጊዜ። ደግሞስ በዚህ ጊዜ ሰው ቤት እንዲህ ዘው ተብሎ ይኬዳል እንዴ? ሌላ ጊዜ፤›› አለ ተጋባዡ። ‹‹የስደትን ያህል በሰው አገር ዘው ባንልም የባልንጀራ ቤት የራስ ማለት ነው። ፍቅር በማጣት አትከስምም! ለማንኛውም አትጥፋ፤›› ብሎ ጋባዡ መንገዱን ቀጠለ። ሌማት እየተገማመትን ሳንወድ በግድ የተራራቅነው ከስንት ወዳጅ ዘመድ ጋር ይሆን ግን? ወይ ኑሮ!   

ወደ መዳረሻችን ተጠግተናል። መጨረሻ ወንበር ላይ የተቀመጠችው ዓይናማ ወያላውን እየተከታተለች፣ ‹‹በቃ አሁንማ ሲም ካርድ 15 ብር ገባላችሁ፡፡ ይኼን የኔትወርክ መጨናነቅ መቻል ነው፤›› ትላለች። በጥግ በኩል ያለ ጎልማሳ ለማማት ከመቸኮሉ የምትናገረውን ሳትጨርስ፣ ‹‹የአንዳንድ ሰው ነገርና የአውራ ዶሮ ሞኝነት እንዴት ይመሳሰላል እባካችሁ?›› ይላል። አጠገቤ የተሰየመው ነገረ ሥራው ችኩል የሆነ ወጣት ዘወር ብሎ፣ ‹‹እንዴት?›› ብሎ ጠየቀው። ‹‹አውራ ዶሮ ምን ብሎ እንደሚያስብ ታውቃለህ? ‘እኔ ካልጮህኩ ፀሐይ አትወጣም’ ይልልሃል። በተዘዋዋሪ የእኔ እውነትና የእኔ ሐሳብ ብቻ ትክክል  ነው ሲልህ ነው። አሁን እስኪ ሰባት ቢሊዮን ደርሰን እንኳ ገና መሬትን ረግጠን ሳንጨርስ እንዴት ብለን ነው ‘ኔትወርክ’ የምናጨናንቀው? ኋላ ቀርነት ነገራችንን ባጨናነቀውና ባዘገየው ቁጥር ችግሮች ሁሉ ከእኛ ብዛት ጋር መዛመድ አለባቸው?›› ብሎ ያስረዳዋል።

ይኼን ልጅት ትሰማለች። ‹‹አይ እኛ! በቃ በገጠመው ባልገጠመው ነገር ሁሉ ቀለባችን ተረትና ተረብ ሆኖ ቀረ?›› ብላ ጎልማሳውን ገረመመችው። ‹‹ምን ይደረግ? ጽንፍ ይዘን መተቸት ካልቻልን ጽንፍ ይዘን መደገፍ ነዋ የምናውቀው። ገብቶንም ሳይገባንም ከያዝነው ሐሳብ ሌላ መቼ እናዳምጣለን?›› ሲል አጠገቧ ያለ ጭምት መሳይ፣ ‹‹እኮ ልክ እንዳውራ ዶሮ?›› አለው ጎልማሳው። ታክሲያችን ጥጓን ይዞ ስትቆም ወያላው በደመነፍስ ተሽቀንጥሮ ተነስቶ በሩን ከፈተው። ‘መጨረሻ’ ባይለንም እንደ ወትሮው መጨረሻችንን አውቀን ለመውረድ ስንሰናዳ፣ ከሾፌሩ ጀርባ ተቀምጦ የነበረው ጎልማሳ መጨረሻ ወንበር ባልተጨበጠ ጉዳይ ባለመግባባት የሚለያዩትን ተሳፋሪዎች ታዝቦ፣ ‹‹የጥላቻ ፌርማታዎቻችን ብዛታቸው! ፖለቲከኛው፣ መንገደኛው፣ ሕፃን አዋቂው ሳይደማመጥ አልግባባ፣ በሐሳብ አልሸናነፍ እያለ በጥላቻና ቂም የሚለያየው እስከ የትኛው ፌርማታ ድረስ ነው?›› አለ። ወይዘሮዋ መለስ ብላ ‹‹ከእውነተኛዋ የሥልጣኔና የዕድገት ፌርማታ እስክንደርስ!›› ብላው ተፈተለከች። ‘ኧረ ቆዩኝ! እስከዚያስ?’ ብዬ እንዳልጠይቅ ሰው ተበትኗል። ለነገሩ ለመነጋገርም ሆነ ላለመስማማት፣ ለመስጠትም ሆነ ለመንፈግ፣ ለክፋትም ሆነ ለደግነት፣ ለመወዳጀትም ሆነ ለመለያየት ሰው መሆን በቂ ነው ተብሎ የለ? መልካም ጉዞ!  

    

           

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት