ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚያካሂደው ቅድሚያ ለሴቶች 5 ኪሜ ሩጫ ባለፈው እሑድ (መጋቢት 6፣ 2007 ዓ.ም.) በአዲስ አበባ የተካሄደው ‹‹አገርን ለማልማት ሴቶችን እናሳትፍ›› በሚል መሪ ቃል ነበር፡፡ ከ10000 በላይ ሴቶች በተሳተፉበትና መነሻና መድረሻውን ዳያስፖራ አደባባይ ባደረገው ውድድር ከተሳተፉበት መካከል ለየት ያለ ትርኢት ያሳዩ እንደነበሩበት ፎቶው ያሳያል፡፡ (ፎቶ ከድረ ገጽ)
********
ሙግት
አያ ነጭ አምላኩ ፈጣሪው ፈረንጅ፤
ታሪክ ይሆንና ታዛቢ ፈራጅ
የወንዝህ ልጅ ሆኖ ያገርህ ጠበቃ
ተጠየቅ ይልሃል ÷ አታውቅ እንደሆነ፤
ያሬድ ‹‹ዋይ ዜማ›› ሲል ÷ ዘመረ? ዘፈነ?
ጾመ ድጓ ማነው?
አባትዮው ማነው ÷ ልጅዬው?
ኃይለኛው ታላቁ ራስ ወልደ ገብርኤል
ትክክል ፈራጅ ዳኛ ነው ሲባል
አንድ ልጁን ለምን ሰደደው ገደል?
‹‹እረኝነት ይሻል ከመሆን ካህን››
ብሎ የተቀኘው ማነው፣ መች፣ ለምን?
ሰረገላ ብርሃን የሚባል ሰው ነበር
የጎጃም ምድር ጉድ የሐበሻ ታምር፤
አያ ነጭ አምላኩ አልሰማህም እንዴ፤
ያገርህ አርበኛ ዘምቶ ከውጋዴ
ሲወቃው መሞቱን ታንኩን በጎራዴ?
እሰጥ ይህ አይደለም ‹‹አለመሠልጠን››
ወይ ‹‹ድንቁርና ሕይወት ማባከን››፤
እንደመሰከረ ያ ቴዎድሮስ
ሽጉጡን አጉርሶ ሽጉጡን ሲጎርስ . . .
አያ ነጭ አምላኩ ተረተሃል ÷ አንሣ!
የጣልከው የተውከው ሆኗል መቶ ታምሣ፡፡
አንሣ የጣልከውን ያገርህን ዜማ
የሕዝብህን ቋንቋ የዘርህን ግርማ
ያገርህን ጨዋታ ጭፈራ ዘፈን
ካገርግም ልማድ ÷ መልካም መልካሙን፡፡
አያ ነጭ አምላኩ ምለህ ተፈጠም
አይለምደኝም ብለህ ማጋበስ መልቀም
ፈረንጅ የጣለውን ÷ ያልጣለውንም፤
የፈረንጅ የሆነ ቅዱስ ነው ማለት፡፡
ይውረድ እንደወጣ ከራስህ ውርደት!
ሰውነትህን አትካድ፣ ሕዝብህን አትክዳ
አንተ ለዘሩ ባዳ ለሀገሩ እንግዳ፡፡
- መንግሥቱ ለማት ‹‹ባሻ አሸብር ባሜሪካ›› (1967)
የወላይታ ምሳሌያዊ ንግግር
- አንተ ችጋር የት ትሄዳለህ ቢሉት ሰነፍ ሰው ቤት አለ ይባላል
(በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ)
- አንተ ሌባ ከፊት ለፊትህ ገደል ነው ቢለው አውቄ ነው የመጣሁት አትምከረኝ ይላል
(ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው)
- ይህን ነገር ጨርሱና ድንጋይም ቢሆን አማትቼ እጎርሳለሁ አለ ጅብ
(ነገር ቢበዛ ባህያ አይጫንም)
- አንደ መሀላ የት ትሄዳለህ ይላል ሽማግሌ የማለውን ለመግደል ካጣኸው ቢሉት ያስማለውን እገላለሁ ይላል
(ደባ ራሱን ስለት ድጉሱን)
- አፍ እንዳመጣ አትናገር በተሰነጠቀ መሬት ውስጥ አትግባ
(ከአፍ ከወጣ አፋፍ ነው)
- የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዴሚ ‹‹ዎላይተቶ ሌምሱዋ›› (1987)
********
አስመስሎ የተሠራው የሒትለር ግለ ማስታወሻ
‹‹ስተርን›› የተባለው የጀርመን መጽሔት የአዶልፍ ሒትለር ግለ ማስታወሻዎች (Diaries) የማግኘታቸውን ዜና ይፋ ሲያደርግ ስለሒትለር ሁሉንም ነገር ሊታወቅ ነው፤ ግለ ማስታወሻውም ታትሞ ሰፊ ተነባቢነትን ያገኛል ሲሉ የተናገሩት ጥቂት አልነበሩም፡፡ ግለማስታወሻዎቹንም የእንግሊዙ ሰንዴይ ታይምስና ኒውስ ዊክ መጽሔቶች ተገዝተው ነበር፡፡ ግለ ማስታወሻዎቹ የሒትለር ስለመሆናቸው ጥርጣሬ እንደሌላቸው የተናገሩ የዘመነ ሒትለር ታሪክ ተመራማሪዎችም ነበሩ፡፡
በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከተነሱት መሪዎች መካከል በጨካኝነቱ የሚታወቀው፤ ግላዊ ታሪኩ በአጨቃጫቂነት የሚነሳው የሒትለር ግለ ማስታወሻ የመገኘቱ ዜና የሒትለርን አመለካከት ለሚያራምዱ ጀርመናውያንም ታላቅ የምሥራች ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም በጣም ቀላል በሆነ ምርምራ ግለ ማስታወሻቹ የሒትለር ሳይሆኑ አስመስሎ ሠሪዎች (Forgers) የተሠራ መሆኑ ተደረሰበት፡፡
ግለ ማስታወሻዎቹ የተጻፉበት ወረቀትና ቀለም ሒትለር ከሞተ በኋላ የተሠሩ መሆናቸው ተረጋገጠ፡፡ ‹‹አስመስሎ የመሥራት ጥበብ አድናቆት ሊቸረው ይገባል፤›› የሚለው ሒትለር ግለማስታወሻ አስመስሎ ጸሐፊ ኮንራድ ኩጃ ወረቀቱን የድሮ ለማስመሰል ሻይ ውስጥ ይነክረው እንደነበር የታወቀው ቆይቶ ነበር፡፡
ኩጃ አስመስሎ መሥራት የጀመረው ነፃ የምሳ መመገቢያ ካርዶችን በመሥራት ነው፡፡ በመጨረሻ የሒትለርን ግለ ማስታወሻ አስመስሎ በመሥራትና በማጭበርበር ተከሶ የአራት ዓመት ከድስት ወር እስራት ተፈርዶበት ወደ ወሕኒ ቢወርድም በሦስተኛው ዓመት ተለቋል፡፡
‹‹በርሊን በሩሲያውያን እጅ ከመውደቋ በፊት ከዚያ ተነስታ በነበረችውና በተከሰከሰች አነስተኛ አውሮፕላን ውስጥ ሒትለር ለ12 ዓመታት የጻፋቸው ግለማስታወሻዎቹ ነበሩ›› የሚለው ታሪክ የስተርን መጽሔት ሠራተኞችን ለማሳመን በቂ ነበር፡፡ እውነትም ደግሞ በተጠቀሰው ጊዜ ከበርሊን ተነስታ ስትበር የወደቀች አውሮፕላን ነበረች፡፡ እናም ይህን ‹‹እውነተኛ›› የተባለና ከወደቀችው አውሮፕላን ውስጥ እንደተገኘ የተነገረለትን የሒትለርን ግለ ማስታወሻ ‹‹ስተርን›› በከፍተኛ ምስጢር ለመግዛት ተስማማ፡፡ በዚህም መሠረት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በአስተላላፊው/ባገማ በኩል ለኩጃ ተሰጠ፡፡
ኩጃ ስለሒትለር የተጻፉትን መጻሕፍት፣ የወቅቱን ጋዜጦችና መጽሔቶች እያነበበ፤ በአገሩ የሚባለውን እያብሰለሰለ የሒትለርን ሰብዕና በራሱ መንገድ ለመረዳት፤ ከዚህ ሰብዕናውና በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ አንፃርም ሒትለር በማስታወሻው ሊጽፈው ይችላል የሚለውን ለማውጠንጠን፤ ከዚያም በኋላ የዘመነ ሒትለርን የአጻጻፍ ሥልት ተከትሎ 62 ጥራዝ ያለው ማስታወሻ ለመጻፍ የፈጀበት ሁለት ዓመት ብቻ ነው፡፡
ኩጃ የሒትለርን ግለ ማስታወሻ አስመስሎ በሚጽፍበት ጊዜ የዚያን ዘመን ጄኔራሎች ሙሉ ልብስ ይለብስ ነበር፤ ይህን የሚያደርገው በሒትለር ዘመን ያለ እንዲመስለው መሆኑን ተናግሯል፡፡ ኩጃ ከእስር ቤት ከተፈታ በኋላ በማስመሰል የተሠሩ ሥራዎች የሚቀርቡበት የፈጠራ ሥራዎች ማሳያ (ጋለሪ) ከፍቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አስመስሎ የሠራቸው ሥዕሎች በውድ ዋጋ ተሽጠውለታል፡፡ የኩጃ ሥራዎች ‹‹እውነተኛ ተመሳሳዮች›› (Honest Fakes) ተብለው ለገበያ ከሚቀርቡት ጋር የሚደመሩ ናቸው፡፡ የኩጃ ሕይወትና ሥራ ምናልባትም እንደ ተረት ሲነገር የሚኖር ነው፡፡ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ግን ኩጃ ባለፈው መስከረም በ62 ዓመቱ አርፏል፡፡ የማስመሰል ሞት ይሆን እንዴ?
- መድበል (1993)
*******
ወደላይ የመዋኘት ትንቢት
አገራችን ከእንቅልፏ እየነቃች ነው፤ ማንም ሰው ከሌሊት እንቅልፉ እንደሚነቃ አገራችንም እየነቃች ነው፡፡ አገራችን ባዶና ደሃ ናት፡፡ ድሆቹ የእኛ የሚሉት አንዳችም ነገር የላቸውም፡፡ ባዶዎቹም ልክ እንዳልተጻፈበት ወረቀት ናቸው፡፡ ደሃ መሆን ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም ድህነት ፈጣንና ታላቅ ለውጥን ወደመፈለግ ያመራልና ነው፡፡ በባዶ ወረቀቶች ላይ ብዙ የምንሠራው ነገር አለን፡፡ በንጹሆቹ ወረቀቶች ላይ ልንጽፍባቸው ወይም ዲዛይኖችን ልንሥልባቸው እንችላለን፡፡ ባዶ ወረቀቶች በተለይ ለመጻፍ የተመቹ ናቸው፡፡
… ዛሬ ምዕራባውያን ብዙ ቀድመውናል፡፡ በፍጥነት ልንጓዝና ልንደርስባቸው ይገባል፡፡ በ15 ዓመታት ውስጥ እንግሊዝን እንደርስባታለን፡፡ እነዚህ 15 ዓመታት ይወስኑናል፡፡ የመጀመርያዎቹ አምስት ዓመታት በመጀመርያዎቹ ሦስት ዓመታት ጥገኛ ይሆናሉ፡፡ የመጀመርያዎቹ ሦስቱ ደግሞ በመጀመርያው ዓመት ሥራችን ይወሰናሉ፡፡ የመጀመርያውም ዓመት በመጀመርያው ወር ይወሰናል፡፡ … ከዚህ ግባችን ለመድረስ በፍጥነት ማሽከርከር አለብን፡፡ ሻንጋይ በነበርኩበት ጊዜ አንድ ፕሮፌሰር ‹‹በንፋሱ/በአየሩ ላይ ጋልብ፣ በሞገዱ ውስጥ እለፍ›› (Ride on the Wind and Break Trough the Wind) የሚል አባባል ከጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ አስነብቦኝ ነበር፡፡ ወደላይ ለመዋኘት ኃይላችንን ማስተባበር አለብን ማለቱ ነበር፡፡ ወደታች እንደመዋኘት አይደለምና ጠንክሮ መሥራትን ይሻል፡፡ በእውነት ይህን ሰው አደንቀዋለሁ፤ በጣም ትክክል ነበር፤ ወደላይ መዋኘት አለብን፤ ለዚያውም በፍጥነት፡፡
አንዳንድ ሰዎች ታላቅነትና ስኬትን የሚናፍቁን፣ ጥሩ ውጤት ለማግኘት ብዙ መታገስ የማይፈልጉን፣ ያለፈውን እየኮነኑ በመጪ ላይ ዕውር ተስፋ የሚኮተኩቱትን ሲተቹ እሰማለሁ፡፡ ስኬትንና ታላቅነት በቶሎ መሻት ክፋቱ ምን ይሆን? ያለፈ ታሪክ እርባና የለውም ማለት አይቻልም፡፡ በርግጥም በርካታ ታላላቅ ሥራዎች ትናንት ውስጥ ተፈጽመዋል፡፡ ነገር ግን ነጋ ጠባ ስላለፉት ታላላቅ ሰዎች ማሰብና ማውራት ጠቃሚ አይመስለኝም፤ ታሪክን የማየውም እንዲህ አይደለም፡፡ . . . የሰው ልጅ ታሪክ እያደገ ነው፡፡ በነገ ላይ እውር እምነትን ማሳደር ባይገባም ዓላማችን ነገ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ በነገ/በመጻኢው ላይ ማነጣጠርና እምነት መጣል ትክክል እንደሆነ እናምናለን፤ እምነታችን ግን እውር አይደለም፡፡
ታላቅነትና ስኬትን በጽኑ መፈለጋችንን የሚተቹ አሉ፡፡ ውድቀትንና መከራን መመኘት ነበረብን ይሆን? ያለፈውን እያሞገስን መጻኢውን መኮነንና ማጨለም አለብን? መቼም ቢሆን ታላቅነትንና ስኬትም ለማግኘት በጽኑ እንታገላለን፡፡ በዚህ የሚያምኑ ሁሉ መልካም ሕዝቦች ናቸው፡፡ ጠንካራውንና ለመሥራት የተዘጋጀውን መንፈሳችንን ልንጠብቀው ይገባል፡፡
ማኦ-ሴቱንግ
(ጥር 28 ቀን 1958 እ.ኤ.አ.)
የጅብ ሊቀመንበር
የጅብ ሊቀመንበር
የዝንጆሮ ዳኛ የጦጣ ጸሐፊ
ሁሉም ሌቦች ናቸው
ዘራፊ ቀጣፊ፡፡
(ባለፈው መንግሥት ዘመን የተገጠመ)
የአበባ ፍልስፍና
አበባን ማሰብና በተለይም በተለያዩ መልካቸው መሰደር ‹‹ኢክባና›› ይባላል፡፡ በ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ አንድ ተወዳጅ ባህል የተያዘ ነው፡፡ ከእያንዳንዱ የአበባ አደራደርና አሰዳደር በስተጀርባ የተለየ ፍልስፍና አለ፡፡ የአበቦች አቀማመጥ ሥርዓት ገነትን ምድርንና ሰዎችን እንዲወክል ተደርጎ የሚተረጎምበትና የሚታመንበት ልዩና ጥብቅ ሥርዓቶች አሉት፡፡ እያንዳንዶቹ ቀላሎች ሲሆኑ ሌሎቹ ጥበቦች በጣም በጣም ውስብስቦች ናቸው፡፡ ስለዚህ ዛሬ በመላው ጃፓን 3,000 የሚሆኑ የኢክባና (የአበቦች ሥርዓት) ማስተማሪያ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ 15 ሚሊዮን ተማሪዎች አሏቸው፡፡ አበቦች ለጃፓናውያን ውበትና ፍቅር ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ውስጥ ካደረገው መልካሙ የመንፈስ ኃይል ጋር ተገናኝተው ነፍስን የሚያፈሱበት ነው፡፡
- ደ.ደ. ‹‹በጃፓን የተሠራ›› (1992)