Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የትምባሆ ሞኖፖል የመሬት ጥያቄ ግጭት አስነሳ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብሔራዊ ትምባሆ ሞኖፖል ድርጅት ከውጭ የሚያስገባውን ትምባሆ ቅጠል በአገር ውስጥ ለማምረት የያዘው ዕቅድ ችግር ገጠመው፡፡ ድርጅቱ በደቡብ ክልል ጋሞ ጎፋ ዞን የጠየቀው መሬት ባለፈው ሳምንት ግጭት አስነስቷል፡፡

ድርጅቱ ቦታውን መውሰድ የለበትም ያሉ የምዕራብ ዓባያ ነዋሪዎች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተው የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ፣ ስድስት ሰዎች ቆስለዋል፡፡ የጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ተወካይ አቶ ዓለማየሁ አደሬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በግጭቱ አንድ የአካባቢው ሰው ሲሞት፣ አንድ ፖሊስ ቆስሏል፡፡ ‹‹ሌላ ቁስለኛ የለም፡፡ ነገር ግን የግጭቱ መንስዔ የአካባቢው ሰዎች ከመሬቱ ጋር ቢያያይዙትም ምክንያቱ ግን ይህ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ የ15 ደቂቃ ግጭት ነው ያሉት አቶ ዓለማየሁ፣ ግጭቱን መቆጣጠር የተቻለ መሆኑንና መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ከአባቢው ነዋሪዎች ጋር ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በተሰጠው መሬት ጉዳይ ግን አዲስ ውሳኔ አይኖርም፤›› ሲሉ አቶ ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡ ትምባሆ ሞኖፖል ከሁለት ዓመት በፊት ለጋሞ ጎፋ ዞን አሥር ሔክታር መሬት እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቧል፡፡  ዞኑ በምዕራብ ዓባያ አሥር ሔክታር መሬት እንዲሰጠው ከብዙ ቆይታ በኋላ መወሰኑ ታውቋል፡፡

ነገር ግን ቦታው ለትምባሆ ሞኖፖል መስጠቱ አግባብ አይደለም ያሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ እንዳሰሙ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው መረጃዎች እንደጠቆሙት፣ ለድርጅቱ እንዲሰጥ የተወሰነው ቦታ የአካባቢውን ነዋሪዎች የሚያፈናቅል ባይሆንም፣ ወደፊት መስፋፊያቸው በመሆኑ ተላልፎ እንዳይሰጥ ተቃውሟቸውን አቅርበዋል፡፡ ትምባሆ ሞኖፖል ከዚህ ቦታ በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን አሥር ሔክታር መሬት ጠይቋል፡፡ ነገር ግን ጥያቄው ከሁለት ዓመት በፊት የቀረበ ቢሆንም፣ ከብዙ ቆይታ በኋላ የተጠየቀው መሬት ለአርብቶ አደሮች የተያዘ ፕሮጀክት  የሚከናወንበት ነው ተብሎ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

የብሔራዊ ትምባሆ ሞኖፖል ድርጅት ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አየለ አለበል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የድርጅቱ የመሬት ጥያቄ በመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት አልተሳካም፡፡ በተለይ በምሥራቅ ሸዋ የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት በማጣቱ እንደ አዲስ በድጋሚ መሬት ለማግኘት እየተሞከረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ትምባሆ ሞኖፖል ለሚያመርታቸው የተለያዩ ሲጋራዎች 60 በመቶ የሚሆነውን የትምባሆ ቅጠል ከውጭ አገር ያስገባል፡፡ የትምባሆ ቅጠል የሚመጣው ከህንድና ከብራዚል ሲሆን፣ ይህም ድርጅቱን በዓመት 11 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስወጣው አቶ አየለ ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱ ይህንን ወጪ ለማስቀረት በአገር ውስጥ ለማምረት የያዘው ዕቅድ የቦታ ጥያቄው ምላሽ በማጣቱ እየተጓተተ መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል፡፡

ድርጅቱ በአራት ቦታዎች የትምባሆ ማቀነባበሪያዎችና ችግኝ ጣቢያዎች አሉት፡፡ ይህንን ወደ ስድስት ለማሳደግ የአካባቢው ገበሬዎች የትምባሆ ቅጠል እንዲያመርቱና እንዲያቀርቡለት ፕሮጀክት ቀርፆ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ አቶ አየለ እንዳሉት፣ የትምባሆ ቅጠል የሚያመርት ገበሬ ዋጋውን ቀድሞ የሚያውቅ በመሆኑ፣ እንዲሁም ድርጅቱም የተመረተ ትምባሆ የመግዛት ግዴታ ስላለበት ገበሬው ተጠቃሚ ነው፡፡

ከተመሠረተ 55 ዓመታት ያስቆጠረው ትምባሆ ሞኖፖል 78 በመቶ በየመን ኩባንያ ሼባ ኢንቨስትመንት የተያዘ ነው፡፡ ከወራት በፊት 78 በመቶ የመንግሥት 22 በመቶ የሼባ ድርሻ የነበረ ቢሆንም፣ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ቦርድ ባሳለፈው ውሳኔ የመንግሥት ድርሻ የነበረው 60 በመቶ አክሲዮን እንዲተላለፍ በመወሰኑ ሼባ ኢንቨስትመንት የትምባሆ ሞኖፖልን የአንበሳውን ድርሻ ሊይዝ ችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች