Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየቀድሞ የአንበሳ አውቶቡስ ድርጅት ኃላፊዎችና ሠራተኞች በ55.7 ሚሊዮን ብር የሙስና ወንጀል ተከሰሱ

የቀድሞ የአንበሳ አውቶቡስ ድርጅት ኃላፊዎችና ሠራተኞች በ55.7 ሚሊዮን ብር የሙስና ወንጀል ተከሰሱ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ኃላፊዎችና ሠራተኞች የነበሩ 11 ሰዎች፣ በሕዝብና መንግሥት ላይ ከ55.7 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው የሙስና ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የተጠቀሰውን ጉዳት አድርሰዋል ብሎ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩት አቶ በድሉ አሰፋ፣ ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር ደጋፊ የሥራ ሒደት መሪ አቶ አብርሃም ፋንታው፣ የቴክኒክ አገልግሎትና የአውቶሞቲቭ አካላት ፕሮዳክሽን ዋና የሥራ ሒደት መሪ አቶ ንጉሡ ላቃቸው፣ የአውቶሞቲቭ አገልግሎት ጥገና ቨርዥን የሥራ ሒደት ባለቤት አቶ ሙሔ አወል ናቸው፡፡

ድርጊቱን በተባባሪነት ፈጽመዋል ብሎ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ያካተታቸው በድርጅቱ የአውቶ መካኒክ ባለሙያ አቶ መገርሳ ጌታቸው፣ የየካ ዴፖ ጥገና ቨርዥን የሥራ ሒደት ባለቤት አቶ ዓለምነህ ፋንታው፣ የቴክኒክ ትምህርት ብቃትና ምዘና ሥልጠና ኬዝቲም መሪ አቶ ምትኩ ተሰማ፣ የአውቶ መካኒክ ባለሙያ አቶ ታምራት አድማሱ፣ የመካኒሳ ዴፖ ቴክኒክ ግብዓት አቅርቦት ንዑስ የሥራ ሒደት መሪ አቶ ደመላሽ ፈጠነ፣ የፕሮግራምና የድንገተኛ ጥገና ኬዝቲም መሪ አቶ ፍቅሬ ደስታና የመካኒሳ ዴፖ ጥገና ቨርዥን ባለሙያ አቶ ፈይሳ አቦዬ (በሌሉበት) ናቸው፡፡

ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ በ2006 በጀት ዓመት ድርጅቱ በሞተር ብልሽት ምክንያት የቆሙ አውቶቡሶችን ሞተር ቀይሮ ወደ ሥራ ለመግባት ያስባል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ ‹‹ኢጂፕት ፓወር ፎር ኢንተርናሽናል ትሬድ›› ከሚባል የግብፅ ኩባንያ ጋር በቅድመ ጨረታ፣ በጨረታና በድኅረ ጨረታ ባለው ሒደት በመመሳጠር፣ በ33,823,426 ብር የ50 ሞተሮች ግዢ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ተከሳሾቹ የግዥ መመርያን በመተላለፍ የግብፅ ኩባንያ በ2002 ዓ.ም. አዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ተዘጋጅቶ በነበረው የአውቶሞቲቭ ኤግዚቢሽን፣ ለኤግዚቢሽኑ ካቀረባቸው የተሽከርካሪ ሞተሮች መካከል ለድርጅቱ አንድ ሞተር በስጦታ የሰጠ መሆኑን ምክንያት በማድረግ ጨረታውን እንዲያሸነፍ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡

የሞተር ስጦታው እውነተኛ ስጦታ መሆኑና መሥራት አለመሥራቱ ሳይረጋገጥ፣ ኩባንያው ያለምንም ተቀናቃኝ እንዲያሸነፍ መደረጉ ተገቢ እንዳልነበረም አክሏል፡፡ የቴክኒክ ባለሙያዎች ሞተሩን ሲፈትሹ እንደማይሠራ በተለይ ዳገታማ ቦታዎች ላይ ሊሠራ እንደማይችል ተረጋግጦ እያለ፣ የድርጅቱን ጥቅም ማስጠበቅና ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ ሲገባቸው ተከሳሾቹ ግን ግዥው እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

የ50 የዳፍ አውቶብስ ሞተሮች ግዢ ጨረታ በሪፖርተር ጋዜጣ ከወጣ በኋላ 13 ተጫራቾች የቀረቡ ቢሆንም፣ ከተከሳሾቹ ጋር የተመሳጠረው ‹‹ኢጂፕት ፓወር ፎር ኢንተርናሽናል ትሬድ›› ኩባንያ እንዲያሸንፍ ተደርጎ በዋና ሥራ አስኪያጁ እንዲፀድቅ በማድረግ፣ ሞተሮቹ ጥራት እንደሌላቸው እየታወቀ ከላይ የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን በአንድ ጊዜ እንዲከፈል ማድረጋቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ ሞተሮቹ ለአምስት ዓመታት ያገለግላሉ ቢባልም፣ ከ25 ቀናት የአገልግሎት ጊዜ አንስቶ መበላሸት ጀምረው ከ50 ሞተሮች 37 ተበላሽተው ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸውን ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ የ37 ሞተሮች ዋጋም 24,219,722 ብር መሆኑንና ያስገኙት ገቢ 9,653,843 ከመሆኑ አንፃር ሲቀናነስ የ14,565,878 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን አብራርቷል፡፡

ተከሳሾቹ የአዋጭነት ጥናት ሳያስጠኑ፣ የቴክኒክ ፍላጎት መግለጫ በማዘጋጀት ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት ‹‹ከኢጂፕት ፓወር ፎር ኢንተርናሽናል ትሬድ›› ኩባንያ ጋር ሌሎች 13 ተጫራቾች እንዲሳተፉ በማድረግ፣ የፈለጉት ኩባንያ እንዲያሸንፍና ጉዳቱ እንዲደርስ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ ሞተሮቹ ባይበላሹ ኖሮ ከቆሙበት ጊዜ አንስቶ ሊያስገኙ የሚችሉት ገቢ 41,148,318 ብር ይሆን እንደነበር፣ በአጠቃላይ በሕዝብና በመንግሥት ላይ 55,750,196 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ 32 (1ሀ) እና 411(1ሐ) (2 እና 3) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ፣ የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ እንደ መሠረተባቸው ክሱ ያስረዳል፡፡

ተከሳሾቹ የተጠቀሰባቸውን የሕግ ድንጋጌ ከአሥር ዓመታት በላይ የሚያስቀጣ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ጠቅሶ በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ፣ ከአንድ እስከ አራት ያሉት ተከሳሾቹ ከጠበቆቻቸው ጋር፣ ከአምስት እስከ አሥር ያሉት ተከሳሾች ደግሞ ከተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት ከሚመደብላቸው ተከላካይ ጠበቃ ጋር ተመካክረው መቃወሚያ ካላቸው በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያቀርቡ በማዘዝ ለኅዳር 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡   

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...