Saturday, May 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርና ምርቶች በተገኘው ዋጋ እንዲሸጡ ንግድ ሚኒስቴር የሰጠውን መመርያ ኤክስፖርተሮች ተቃወሙ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ገበያ ለግብርና ምርቶች የሚቀርበው ዋጋ እያሽቆለቆለ ቢሆንም፣ ኤክስፖርተሮች ዋጋን ከግምት ሳያስገቡ እንዲልኩ ንግድ ሚኒስቴር መመርያ መስጠቱን ተቃወሙ፡፡

ንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔና ምክትላቸው አቶ ያዕቆብ ያላ የቡና፣ የቅባትና  የቁም እንስሳ ላኪዎችን በተናጠል እየሰበሰቡ ውይይት አድርገዋል፡፡

የውይይቱ መነሻ ባለፉት ስምንት ወራት የግብርና ምርቶች ወጭ ንግድ ዕቅድ አፈጻጸም ከተገመተው በታች በመሆኑ፣ ማሻሻል ያስፈልጋል የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ንግድ ሚኒስቴር በተለይ ለቡናና የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ ለሚልኩ ባለሀብቶች ያቀረበው ምክረ ሐሳብ ተቃውሞ እንደገጠመው በውይይቱ የታደሙ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ንግድ ሚኒስቴር ለቡና ነጋዴዎች ያቀረበው ምክረ ሐሳብ፣ በዓመቱ መጀመሪያ ወደውጪ ለመላክ የያዙትን ዕቅድ እንዳልፈጸሙ በሚገልጽ ወቀሳ መጀመሩ ተገልጿል፡፡

ነገር ግን ነጋዴዎቹ ባቀዱት መሠረት ቡና ወደውጪ ባለመላካቸው የኤክስፖርት አፈጻጸሙ ደካማ ሊሆን እንደቻለ አቶ ያዕቆብ ገልጸው፣ ይኼንን አፈጻጸም በማቀጥሉት አራት ወራቶች በማካካስ የዓለምን የገበያ ዋጋ ከግምት ሳያስገቡ በተገኘው ዋጋ ሽያጭ እንዲያከናውኑ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

ነገር ግን ይህን ሐሳብ ላኪዎች ሊቀበሉት እንዳልቻሉ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ነጋዴዎቹ በወቅቱ ለሚኒስትሮቹ ባቀረቡት መከራከሪያ፣ በዕቅዳቸው መሠረት ቡና ወደ ውጪ መላክ ያልቻሉት የአገር ውስጥ የገበያ ዋጋ ውድ የሚባል ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ፓውንድ ቡና (ከግማሽ ኪሎ ትንሽ ያነሰ) በአገር ውስጥ ገበያ ሁለት ዶላር አካባቢ ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በዓለም ገበያ ውስጥ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ አንድ ፓውንድ ቡና 1 ዶላር ከ35 ነው፡፡

የነጋዴዎቹ ጥያቄ ይህን ኪሣራ ማን ይሸፍናል የሚል መሆኑ ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የቡና ገበሬዎች የዓለም የቡና ዋጋ ይጨምራል እየተባለ በመንግሥት ተቋማት በኩል እየተገለጸላቸው በመሆኑ ቡና ወደ ገበያ እየወጣ አለመሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ነገር ግን የንግድ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ነጋዴዎቹ ባነሱት ድጎማ ይደረጋል ወይ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጡ፣ ገበሬው ግን የያዘውን ቡና ወደገበያ እንዲያቀርብ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

በ2007 ግማሽ ዓመት 73,593 ቶን ቡና በመላክ 269.03 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነበር፡፡ ነገር ግን 72,556 ቶን ቡና ተልኮ 308.50 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህ ዕቅድ ስኬታማ የሚባል ቢሆንም፣ ቡናው በ2006 ዓ.ም. ይላካል ተብሎ ሳይላክ የቀረና በበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት የተላከ በመሆኑ፣ ስኬቱ ይህንን ዓመት እንደማይገልጽ የባለሙያዎች ዕምነት ነው፡፡

ነገር ግን በዚህ ዓመት ከተመረተ ቡና ይህ ነው በሚባል መልኩ ወደ ውጪ ባለመላኩ ጉዳዩን የከፋ እንዳደረገው መረጃዎች እየጠቆሙ ነው፡፡

አቶ ከበደ የስድስት ወራት ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፣ አፈጻጸሙ በአንፃራዊነት የተሻለ የሆነበት ምክንያት የዓለም የቡና ገበያ ዋጋ መሻሻል በማሳየቱና (በወቅቱ) የከረመ ቡና ተሟጦ እንዲወጣ በመደረጉ ነው ብለው ነበር፡፡

የቅባት እህሎች ላይም ተመሳሳይ ችግር እንዳለ ተገልጿል፡፡ በግማሽ ዓመቱ 122,603 ቶን የቅባት እህሎችን በመላክ 249,46 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ነበር፡፡ ነገር ግን 111,493 ቶን በመላክ 211.1 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡

የዚህ ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ዕድገት ያሳየ ሆነም፣ ዕድገቱ ሊታይ የቻለው የዓለም የቅባት እህሎች የገበያ ዋጋ እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም፣ የከረመ ምርት ክምችት ተሟጦ እንዲወጣ በመደረጉ መሆኑን ሚኒስቴሩ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመት የቅባት እህሎችን የሚያመርቱ አገሮች፣ ጥሩ ምርት በማግኘታቸው የዓለም ዋጋ እንደቡና ዝቅ ማለቱ ታውቋል፡፡ ንግድ ሚኒስቴር በተገኘው ዋጋ እንዲላክ ሲያሳስብም ነጋዴዎቹ አሁንም፣ ኪሳራውን ማን ይሸፍናል የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡

ከሁለቱ የግብርና ምርቶች የተለየው የቁም እንስሳት ግብይት ዘርፍ ነው፣ ይህ ዘርፍ በግማሽ ዓመቱ 464,593 እንሰሳቶችን በቁማቸው በመላክ 126.6 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል፡፡ ነገር ግን 332,872 እንስሳቶችን በመላክ 90.7 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡

ለአፈጻጸሙ ማነስ ሚኒስቴሩም ላኪዎችም፣ የኮንትሮባንድ ንግድን ተጠያቂ በማድረግ ተስማምተዋል፡፡ አቶ ያዕቆብ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጠርና እንስሳት በሚወጡባቸው በሮች ኳራንቲን ጣቢያዎችን እየተገነቡ መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን ነጋዴዎች አፈጻጸማቸውን እንዲያስተካክሉ ጠይቀዋል፡፡ መፍትሔ ለማፈላለግ የተጠራው የውይይት መድረክ ኪሳራን የሚያበረታታ ሆኖ በመገኘቱ ውጤታማ ለማለት እንደማቸገሩ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነጋዴዎች ገልጸዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የውጪ ንግድ ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ቢኮራ አስተያየት እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች