Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የደቡብ ሱዳን ቀውስ ጦሱ ለኢትዮጵያ ከመትረፉ በፊት መፍትሔ ይፈለግ!

  የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስምምነት ላይ በመድረስ፣ ከአሥር ሺሕ በላይ ዜጎች የሞቱበትንና ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ተሰደዱበትን ጦርነት ያስቆማሉ ተብሎ ቢጠበቅም ለገላጋይ አስቸግረው ያለ ውጤት ተለያይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በምታስተባብረው ኢጋድ አማካይነት የተደረጉት የሰላም ጥረቶች በሙሉ ከሽፈው፣ ሁለቱ ወገኖች እንደገና ለሌላ እልቂትና ውድመት እየተዘጋጁ ናቸው፡፡ የደቡብ ሱዳን ሰላም ማጣት ለአካባቢው አገሮች በተለይም ለኢትዮጵያ ፈተና ነው፡፡ ይህንን አደገኛ አካሄድ መቀልበስ ካልተቻለ የአገሪቱ ጦስ ለሌሎችም ይተርፋል፡፡ ለኢትዮጵያ ደግሞ የከበደ ይሆናል፡፡

  የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ተቀናቃኛቸው ዶ/ር ሪክ ማቻር ከአንድ ዓመት በላይ የተለፋበትን የሰላም ስምምነት እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ያለውጤት ሲበትኑት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ መላው ዓለም ከፍተኛ የኃዘን ድባብ አጥልቶበታል፡፡ በሁለት ግለሰቦች በሚመሩ ቡድናዊ ፍላጎቶች ምክንያት በደቡብ ሱዳን መረጋጋት መፍጠር ባለመቻሉ፣ አሁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ ይህ አደጋ ደግሞ ኢትዮጵያና ሌሎች ጎረቤት አገሮችን በቀጥታ ይመለከታቸዋል፡፡ የጦርነቱ የሰደድ እሳት አንዴ ከተቀጣጠለ ለማቆም አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ፣ በአካባቢው ጽንፈኛ የሆኑ ጦረኞችም የተደላደለ መሬት ያገኛሉ፡፡

  ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ካሉ አገሮች የተረጋጋችና ሰላማዊ አገር ብትሆንም፣ በጎረቤት አገሮች የሚፈጠር ችግር ምን ያህል ጫና እንደሚያሳድርባት በተለያዩ ወቅቶች ታይቷል፡፡ እብሪተኛው የሻዕቢያ መንግሥት ኢትዮጵያንና ሌሎች ጎረቤት አገሮችን ማመስ የሚችልበት አቋም ላይ ባይገኝም፣ በሶማሊያ ከአልሸባብ ጋር ያደረገውን ዓይነት ያልተቀደሰ ግንኙነት ከሌሎች ጦረኞች ጋር እንደሚያደርግ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በድንበር ምክንያት ለሁለት ዓመታት የተደረገው ጦርነት በይፋ ባለመቆሙ ምክንያት፣ ሻዕቢያና አመራሩ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የጦርነት እሳት እንዳይበርድ ይፈልጋሉ፡፡ በጎረቤት ሶማሊያ አከርካሪው ቢመታም አሁንም በአጥፍቶ ጠፊነት የተሰማራው አልሸባብ ለአካባቢው ሥጋት ነው፡፡ በሱዳን በዳርፉርና በአቢዬ ግዛት አሁንም የጦርነት ሥጋት አለ፡፡ ጎሳዎቻቸውን ከጀርባቸው ያሠለፉት የደቡብ ሱዳን ተቀናቀኞች የጦርነቱን ቋያ የበለጠ ካቀጣጠሉት ተስፋ የተጣለበት ሰላም ዋጋ ያጣል፡፡ አካባቢው ይተራመሳል፡፡ ጦሱ ለኢትዮጵያም ይተርፋል፡፡

  ምንም እንኳ ሁለቱ ተቀናቃኝ መሪዎች ሰላም እንዲሰፍን ፍላጎት እንዳላቸው በአደባባይ ቢደሰኩሩም፣ በደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግሥት ምሥረታ የሥልጣን ክፍፍል ላይ የያዙትን ድብቅ አጀንዳ መተው አልፈለጉም፡፡ ለሕዝብ እልቂትና ለአገራቸው ውድመት ከማሰብ ይልቅ፣ በሚመሠረተው መንግሥት ውስጥ ማን የተሻለ ድርሻ ይኖረዋል የሚለው ጉዳይ አንገብጋቢ ሆኖባቸዋል፡፡ ከዚህ ድብቅ ዓላማ በስተጀርባ የመሸጉ ኃይሎች ቀውሱ ከሚረግብ ይልቅ ቢባባስ ተጠቃሚ ስለሚሆኑ የሰላም ጥረቱን ደግሞ እያሰናከሉ ናቸው፡፡ እንግዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት እዚህ ላይ ነው ነቃ ማለት የሚገባው፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ቀውሱ ተቀጣጥሎ ደቡብ ሱዳን ስትጋይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜገች ሸሽተው የተጠለሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ይህ በራሱ ለአገሪቱ ትልቅ ሸክም ነው፡፡ ሰብዓዊነት በጣም ጠቃሚ ተግባር ቢሆንም፣ ወደፊት ስደቱ ሲጨምር ጉዳቱ ከሚታሰበው በላይ ይሆናል፡፡ የጎሳዎች ግጭት ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡

  በኢትዮጵያ መንግሥት መሪነት በኢጋድ አማካይነት የተካሄዱ በርካታ ጥረቶች ቢከሽፉም፣ አሁንም ለሰላም የሚደረገው ጥረት በስፋት ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል፡፡ ጎረቤት በእሳት ሲቃጠል በሰላም ተኝቶ ማደር እንደማይቻል ሁሉ፣ ደቡብ ሱዳን ሰላም ካልሆነች ጦሱ ለኢትዮጵያም ጭምር ነው፡፡ አዲሲቱ አገር ነፃ ወጥታ በሁለት እግሮቿ ከመቆሟ በፊት ጀምሮ በተለያዩ ሙያዎችና ኢንቨስትመንቶች የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን በርካታ ነበሩ፡፡ ሰላም ቢኖር አገሪቱ የኢትዮጵያ ሁነኛ ገበያ ትሆን ነበር፡፡ አየር መንገዱ፣ ባንኮች፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ የተለያዩ ኩባንያዎችና ግለሰቦች ሳይቀሩ ተጠቃሚ ይሆኑ ነበር፡፡ አሁን ያ ሁሉ ቀርቶ ውጥረት በመንገሡ ምክንያት፣ ኢትዮጵያና የአካባቢው አገሮች የሰላም ያለህ እያሉ ነው፡፡ ይህ ሰላም እንዲሰፍን ግን ቁርጠኝነቱ ይቀጥል፡፡

  ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ዶ/ር ማቻር የሰላም ውይይቱን ያቋረጡት ከቡድኖቻቸው ጋር ምክክር በማድረግ ልዩነታቸውን ለማጥበብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ወደኋላ ተመልሰው የሰፋውን ልዩነት በማጥበብ የአገራቸውን ሰላም ለማስፈን ከወሰኑ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን የንፁኃን ደም እንደ ውኃ የሚፈስባትን አገራቸውን ከሥልጣን ቅርምት አስተሳሰብ ወጥተው መታደግ ካልቻሉ፣ አሁንም ትልቅ አደጋ አለ፡፡ የአካባቢው ሰላም እንቅልፍ የሚነሳቸው ኃይሎች የተዛባ ምክር ችግር እንዳይፈጥር ቀድሞ መገኘት ተገቢ ነው፡፡ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በማስተባበር በሁለቱ ጦረኛ ወገኖች ላይ ጫና በማሳደር የሰላም ስምምነቱን እንዲፈርሙ ማድረግ፣ ሰላም በማይፈልጉ ወገኖች ላይ ማዕቀብ መጣል፣ ጠንካራ የሰላም አስከባሪ ኃይል በአስቸኳይ ማሰማራትና ሌሎች ተመሳሳይ ሕጋዊ ዕርምጃዎችን መውሰድ የግድ ነው፡፡ ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ሲባል ይህ ጉዳይ አጣዳፊ መሆን አለበት፡፡

  የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የገነባውን ተሰሚነት በመጠቀም የተቋረጠው ድርድር እንዲቀጥል የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የምታድገው፣ የምትበለጽገው፣ ሰላም የሚሰፍንባትና ዴሞክራሲ የሚጎለብትባት ሰላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ አካባቢው ሲተራመስና የጦርነት አውድማ ሲሆን ዕድገት ይታወካል፡፡ ልማት ይደናቀፋል፡፡ ሰብዓዊ መብት ይጣሳል፡፡ የዴሞክራሲ ችግኝ ይጠወልጋል፡፡ የደቡብ ሱዳን ጦስ ለኢትዮጵያ ከመትረፉ በፊት አፋጣኝ መፍትሔ ይፈለግ!

   

    

     

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ለካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስድስት የቦርድ አባላት ተሾሙ

  ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

  የትጥቅ  መፍታት ሒደትና የሰላም እንቅፋቶች

  የትግራይ ተራሮች ከጦር መሣሪያ ጩኸት የተገላገሉ ይመስላል፡፡ በየምሽጉ አድፍጠው...

  በሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው

  ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ በክልሎችም ሊቋቋም ነው በቅርቡ ተቋቁሞ ወደ...

  የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚመራና የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ተቋም የመመሥረት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ

  የኢንሹራንስ (መድን) ዘርፍን የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...

  ዘንድሮ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን በበይነ መረብ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ

  በሁሉም መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሐ ግብሮች የሚመረቁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ምሁራንና ልሂቃን ከአስተዋዩ ሕዝብ ታሪክ ተማሩ!

  አገራዊ ምክክሩን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ የኢትዮጵያን የትናንት ትውልዶችና የዛሬውን ይዘት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ትውልዶች ለአገራቸው የነበራቸው ቀናዒነት የፈለቀበት...

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...