Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየአዲስ አበባ አስተዳደር ገቢ በመሰብሰብ ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳየ

የአዲስ አበባ አስተዳደር ገቢ በመሰብሰብ ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳየ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተጠናቀቀው ግማሽ ዓመት 15.4 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ቢያቅድም፣ ማሳካት የቻለው 11.04 ቢሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 72 በመቶ ብቻ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

የካቲት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. የተሰበሰበው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በከንቲባ ድሪባ ኩማ የቀረበውን የስድስት ወራት ሪፖርት ካዳመጠ በኋላ፣ በገቢ አሰባሰብ በኩል ያለው የሥራ አፈጻጸም ሊሻሻል እንደሚገባ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

የከተማው አስተዳደር በ2007 ዓ.ም. 27 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት 15.4 ቢሊዮን ብር፣ በቀጣዩ ስድስት ወራት ደግሞ የተቀረውን የመሰብሰብ ዕቅድ ነበረው፡፡

- Advertisement -

ዕቅዱን ማሳካት አለመቻሉን በሪፖርታቸው ያስቀመጡት ከንቲባ ድሪባ፣ የገቢ አሰባሰቡን  ለማሳደግ አስተዳደሩ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር አፈጻጸሙ ደካማ ሊሆን የቻለባቸውን ጉዳዮች ገምግሟል ብለዋል፡፡ ‹‹መሠራት ያለባቸውን ሥራዎች በመለየት ከማዕከል እስከ ወረዳ ያለው አስፈጻሚ ለገቢ አሰባሰቡ ትኩረት መስጠት ይገባዋል፤›› ሲሉ ከንቲባው በሪፖርታቸው አሳስበዋል፡፡

አስተዳደሩ ባለፉት ስድስት ወራት ከሰበሰበው ገቢ ውስጥ 8.244 ቢሊዮን ብር ለካፒታልና ለመደበኛ ወጪዎች አውሏል፡፡ በከንቲባው ሪፖርት እንደተቀመጠው ወጪ ከተደረገው ገንዘብ ውስጥ 2.7 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ፣ 5.6 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪዎች እንዲውል ተደርጓል፡፡

በ30 ገጽ የተዘጋጀው የከንቲባ ድሪባ ሪፖርት ከፋይናንስ ጉዳዮች በተጨማሪ፣ አስተዳደሩ ውጤታማ የሆነባቸውንና ዝቅተኛ አፈጻጸም ያስመዘገበባቸውን ዘርፎች ተንትኗል፡፡ ከእነዚህ መካከል የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች፣ የቄራ አገልግሎቶች፣ ሕገወጥ ንግድና የትራንስፖርት እጥረት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ስድስት ወራት 154 የእሳት ቃጠሎዎችና 51 ድንገተኛ አደጋዎች ተከስተዋል፡፡ በእነዚህ አደጋዎች 38 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተገልጿል፡፡

ከንቲባው እንዳሉት የእሳት ቃጠሎ አደጋው በተለይ ከዚህ በፊት ባልተከሰተባቸው ቦታዎች ለምሳሌ ቦሌ ጭምር ተከስቷል፡፡ ከቦሌ በተጨማሪ በአራዳ፣ በአዲስ ከተማ፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍላተ ከተሞች ከፍተኛ የእሳት አደጋ ተከስቶባቸዋል፡፡ ‹‹የእሳት አደጋን ከመከላከል አንፃር በነዋሪው የሚታየው የቅድመ አደጋ መከላከል ግንዛቤ ክፍተት በመሙላት መከላከል ይጠበቅብናል፤›› በማለት ከንቲባው የአደጋውን ስፋት በሪፖርታቸው አስታውቀዋል፡፡

የቄራዎች አገልግሎትን በሚመለከት ከንቲባው እንዳሉት፣ አስተዳደሩ አዲስ ቄራ ለመገንባት ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጋር በመነጋገር ላይ ነው፡፡ አስተዳደሩ ከዚህ ተቋም ጋር መነጋገር የፈለገው ቄራውን ብለው የሚመጡ አዕዋፋት በአውሮፕላን በረራ ችግር ሊፈጥሩ ይችላል ከሚል ነው፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት አስተዳደሩ 241,970 የተለያዩ እንስሳትን ለማረድ ቢያቅድም ክንውኑ ግን 196,390 የዕርድ አገልግሎት መስጠት ሆኗል፡፡ ይህም የዕቅዱን 81 በመቶ መሆኑን የሚተነትነው የከንቲባው ሪፖርት፣ ሕገወጥ ዕርድን ለመቆጣጠር በተደረገው እንቅስቃሴ 18,530 ኪሎ ግራም ሥጋ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ይጠቁማል፡፡

ሌላኛው የከተማው አስተዳደር ችግር ሕገወጥ ንግድ ነው፡፡ ከንቲባው እንዳሉት በከተማው ያለ ንግድ ፈቃድ መነገድ፣ ከዘርፍ ውጭ መነገድ፣ የአድራሻ ለውጥ ሳያስመዘገቡ መነገድ፣ የዋጋ ዝርዝር አለመለጠፍ፣ የድጎማ ሸቀጦች ላይ ሕገወጥ ተግባር መፈጸምና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ሸቀጦች ይዞ መገኘት ዋነኛ ችግሮች ናቸው፡፡ አስተዳደሩ በእነዚህ አካላት ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን መውሰዱን ከንቲባው ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 6,512 ሱቆች ታሽገዋል፡፡ 23 ንግድ ፈቃዶች ተሰርዘዋል፡፡ 1,055 የሚሆኑት ደግሞ ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡ ውሳኔ ከተሰጠባቸው የክስ መዝገቦች ውስጥ ከሦስት ወራት እስከ ሦስት ዓመት የተፈረደባቸው መኖራቸውንም ሪፖርቱ ያትታል፡፡

በከተማው ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ከንቲባው አብራርተዋል፡፡ ከንቲባው በሪፖርታቸው እንዳሉት፣ በከተማው አስተዳደር የሚታየውን ከፍተኛ የትራንስፖርት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የብዙኃን ትራንስፖርት አቅርቦት ለማሳደግ የዳሰሳ ጥናት ተከናውኗል፡፡ በጥናቱ ግኝት መሠረት አዳዲስ ዘመናዊ አውቶቡሶችን ከኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እንዲገዙ ተወስኗል፡፡ ግዢውን ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ሪፖርቱ ጠቁሞ ግዢው 300 አውቶቡሶችን፣ ሁለት ተንቀሳቃሽ ጋራዦችን፣ ሁለት የተበላሹ መኪኖች ማንሻ ክሬኖችንና አንድ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከልን ይጨምራል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ጉባዔ መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. የሁለተኛ ቀን ውሎውን አድርጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...