Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊመንግሥት ለባቡር ፕሮጀክቶች ከሚያስፈልገው 60 ቢሊዮን ብር 18 ቢሊዮን ብር ሸፍኜያለሁ አለ

መንግሥት ለባቡር ፕሮጀክቶች ከሚያስፈልገው 60 ቢሊዮን ብር 18 ቢሊዮን ብር ሸፍኜያለሁ አለ

ቀን:

የዘገየው የባቡር ፕሮጀክት በይፋ ግንባታው ተጀመረ

መንግሥት ለባቡር ፕሮጀክቶች ከሚያስፈልገው 60 ቢሊዮን ብር ውስጥ 25 በመቶ ወይም 18 ቢሊዮን ብር መሸፈኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አስታወቁ፡፡

መንግሥት በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመገንባት ካቀደው የባቡር መስመር ሁለት ሺሕ ኪሎ ሜትር ውስጥ 1,500 ኪሎ ሜትሩን አስጀምሯል፡፡ ለዚህ ግንባታ 60 ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን፣ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 75 በመቶ ከቻይናና ከአውሮፓ አገሮች ሲገኝ፣ ቀሪው 25 በመቶ ወይም 18 ቢሊዮን ብር በኢትዮጵያ መንግሥት መሸፈኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አስታወቁ፡፡

- Advertisement -

‹‹ሰዎች ለእነዚህ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ገንዘብ እንዳላዋጣች ያስባሉ፡፡ የ60 ቢሊዮን ብር 25 በመቶ እጅግ ትልቅ ወጪ ነው፤›› በማለት የኢትዮጵያ ግምጃ ቤት ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም ይህን የተናገሩት አዋሽ – ወልዲያ ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ፕሮጀክት ከተፈረመ ከሁለት ዓመት በኋላ፣ የካቲት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ሥራውን በይፋ በተጀመረበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ሊጓተት የቻለው በወቅቱ የፋይናንስ ምንጮች ማግኘት ባለመቻሉ ሲሆን፣ ከአምስት ወራት በፊት ፕሮጀክቱ ከሚፈልገው 1.7 ቢሊዮን ብር ውስጥ የቱርክ ኤግዚም ባንክና ክሬዲት ስዊስ በጋራ 1.23 ቢሊዮን ዶላር ብድር በመፍቀዳቸው ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ቀሪው ገንዘብ በኢትዮጰያ መንግሥት የሚሸፈን መሆኑ ታውቋል፡፡  

ሥራውን የካቲት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በመሆን በኮምቦልቻ ከተማ የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥ አስጀምረዋል፡፡ ይህንን ግዙፍ ግንባታ ለማካሄድ ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ጋር ውል የገባው የቱርኩ ኩባንያ ያፒ መርከዚ ሬይልዌይ ኢንጂነሪንግ ኩባንያ በኮምቦልቻ ከተማ የሠራተኞች ካምፕ ገንብቶ በዕለቱ ሥራውን ጀምሯል፡፡

ይህ የባቡር መስመር ከአዋሽ እስከ መቀሌ የሚዘረጋው የባቡር መስመር ፕሮጀክት አካል ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በሁለት ተከፍሎ የሚሠራ ሲሆን፣ ከመቀሌ – ወልዲያ – ሃራ ገበያ የሚዘረጋውን 250 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር የቻይናው ሲሲሲሲ ኩባንያ ተረክቧል፡፡ ይህ ፕሮጀክት 1.6 ቢሊዮን ዶላር የሚፈልግ ሲሆን፣ ገንዘቡ ከቻይና መንግሥት ኤግዚም ባንክ ተገኝቷል፡፡ ፕሮጀክቱን የካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በይፋ ሥራውን ማስጀመራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ቀጣዩ ከወልዲያ (ሃራ ገበያ) ጀምሮ እስከ አዋሽ ድረስ የሚዘረጋው የባቡር መስመር ፕሮጀክት የሚገነባው ደግሞ ያፒ መርከዚ ሬይልዌይ ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ነው፡፡

ይህ ፕሮጀክት የወልዲያ ከተማን አለመንካቱ የአካባቢውን ነዋሪዎች ቅር ማሰኘቱ ታውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የዚያኑ ዕለት ከሰዓት በኋላ ከምሥራቅ አማራ ክልል ነዋሪዎች ጋር ባካሄዱት ውይይት፣ ፕሮጀክቱ ወልዲያ ከተማን ባለመንካቱ የአካባቢውን ነዋሪዎች ቅር ማሰኘቱ ታውቋል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ይህ ሊሆን የቻለው ወልዲያ ከተማ እጅግ ተራራማ በመሆኑና የባቡር ትራንስፖርትን ደግሞ በተራራ ላይ ማካሄድ ባለመቻሉ ነው፡፡ አንዳንድ አስቸጋሪ ቦታዎችን በዋሻ ውስጥ ለማሳለፍ ተሞክሯል፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ ውድ በመሆኑ ከወልዲያ ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሃራ ገበያ እንዲያልፍ ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሃራ ገበያ ለወልዲያ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ በመሆኑ፣ ምርቶችን በከባድ ተሽከርካሪዎች ማጓጓዝ እንደሚቻል አቶ ኃይለ ማርያም አስረድተዋል፡፡

የባቡር ፕሮጀክቱ አዋሽ አሚባራ፣ ሸዋ ሮቢት ሰንበቴ፣ ካራቆሬ መኮይ፣ ኮምቦልቻ፣ ሐይቅ፣ መርሳና ሃራ ገበያን ያቋርጣል፡፡ አዋሽ ወልዲያ ሃራ ገበያ 15 የባቡር ጣቢያዎች ሲኖሩት፣ አይሻ፣ ሸዋሮቢት፣ ኮምቦልቻ፣ ሐይቅ ዋና ዋና ጣቢያዎች ይገነቡለታል፡፡ ፐሮጀክቱ 65 ድልድዮች ሲኖሩት፣ ከእነዚህ ድልድዮች አንዱ 641 ሜትር ርዝመት ይኖረዋል ተብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 12 ዋሻዎች እንደሚኖሩ፣ ከዋሻዎቹ ውስጥ ካራቆሬ ላይ የሚገነባው ረዥሙ ዋሻ ነው ተብሏል፡፡ ፕሮጀክቱ አሥር የባቡር መቆጣጠሪያዎችና ስምንት የኤሌክትሪክ ሰብስቴሽን ጣቢያዎች እንደሚኖሩት ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አዋሽ – ወልዲያ ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መሐመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በያፒ መርከንዚ የሚገነባው ፕሮጀክት ከአዲስ አበባ (ሰበታ ከተማ) እስከ ጂቡቲ የሚዘረጋውን የባቡር መስመር አዋሽ ደርሶ ወይ ወደ አዲስ አበባ ወይም ወደ ጂቡቲ መጓዝ ይችላል፡፡

ይህ ፕሮጀክት የፊርማ ስምምነት በተካሄደበት ወቅት ቢጀመር በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ዘንድሮ ይጠናቀቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ ሥራ የተገባው ዘግይቶ ነው፡፡ ባለፈው ረቡዕ ፕሮጀክቱ በይፋ ሲጀምር የያፒ መርከንዚ መሥራችና ሊቀመንበር ሚስተር ኤርሲን አሪዎግሉ እንዳሉት፣ የኮንትራት ስምምነት ከተፈረመ ሁለት ዓመት ያለፈ ቢሆንም፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ለፕሮጀክቱ መሠረታዊ ጉዳይ የሆኑ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የመነሻ ዲዛይን ዝግጅት፣ የሞቢላይዜሽን ሥራ፣ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማምረትና ፋይናንስ ማፈላለግ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡

ሊቀመንበሩ እንዳሉት የሚያስፈልገው ፋይናንስ ከአምስት ወራት በፊት በመገኘቱ፣ የግንባታ እንቅስቃሴ ውስጥ ተገብቷል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪና የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ፣ በወቅቱ የፋይናንስ መዘግየት ከግምት ውስጥ ገብቶ ፕሮጀክቱ ከተያዘለት ጊዜ ገደብ ባጠረ ጊዜ እንዲጠናቀቅ አደራ ብለዋል፡፡

መንግሥት በአጠቃላይ በመላ አገሪቱ ከአምስት ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ የባቡር ኔትወርክ የመገንባት ዕቅድ ይዟል፡፡ ከዚህ ውስጥ ዘንድሮ በሚጠናቀቀው የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ሁለት ሺሕ ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር የመገንባት ዕቅድ ነበረው፡፡

ነገር ግን ከሁለት መስመሮች ውጪ ያሉት ሌሎቹ ፋይናንስ ስላልተገኘላቸው፣ የፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን ሳይጀመሩ የዕቅድ ዘመኑ እየተገባደደ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባ – ሰበታ – ጂቡቲና አዋሽ – መቐለ ፕሮጀክቶች ብቻ በዕቅድ ዘመኑ ፋይናንስ ተገኝቶላቸው ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...