Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዱባይ ግዙፍ ኩባንያ በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለማካሄድ ፍላጐት አሳየ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዩናይትድ ዓረብ ኢምሬትስ ግዙፍ ኩባንያ ፒቮት ኢንጂነሪንግና ጄኔራል ኮንትራክቲንግ፣ በአዲስ አበባ ከተማ 350 ሺሕ ቤቶችን ለመገንባት ፍላጐት አሳየ፡፡

ኩባንያው ፍላጎቱን ለመንግሥት በይፋ ያቀረበ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በጉዳዩ ላይ መምከሩ ታውቋል፡፡

ኩባንያው ትከረቱን ያደረገው መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የመኖሪያ ቤቶች እጥረት ለመቅረፍ በጀመረው ፕሮግራም ላይ ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም በተለይ በ20/80 እና በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም ከ800 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ተመዝግበዋል፡፡ ነገር ግን ግንባታው እየተጓተተ ነው በሚል ምክንያት ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል፡፡

በዚህ መሠረት የውጭ ኩባንያዎችን መርጦ እንዲያስገባ ኃላፊነት የተሰጠው የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በሥሩ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አማካይነት ጨረታ አውጥቷል፡፡

በዚህ ጨረታ 28 የውጭና አገር በቀል ኩባንያዎች ተሳታፊ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ከእነዚህ ኩባንያዎች መካከል ይህ የዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ ኩባንያ የሚገኝበት ቢሆንም፣ ከጨረታው ይልቅ በድርድር ፕሮጀክቱን ለማግኘት የተለያዩ ፕሮፖዛሎችን በመቅረፅ ላይ ይገኛል፡፡

ላለፉት 35 ዓመታት በተለያዩ የኮንስትራክሽንና የኢንጂነሪነግ ዘርፎች ውስጥ የቆየው ፒቮት ኢንጂነሪንግ ኩባንያ፣ ለመንግሥት ካቀረባቸው መደራደሪያ ነጥቦች መካከል ኢንጂነሪንግ ፕሮኪዩርመንት ኮንስትራክሽን (ከዲዛይን እስከ ግንባታ ማጠቃለያ አጠቃላይ ሥራ) እንዲሰጠውና ይህንንም ለማካሄድ ፋይናንስ እንደሚያመጣ ነው፡፡

ከዚህ በላይ ኩባንያው በተለያዩ አገሮች በዘርፉ የካበተ ልምድ ስላለው መንግሥት የሚፈልጋቸውን የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂዎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያመጣ ካቀረበው ፕሮፖዛል ለመረዳት ተችሏል፡፡

ኩባንያው በየካቲት 2007 ዓ.ም. መጀመሪያ ዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጻፈው ደብዳቤ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በመኖሪያ ቤቶች ልማት ዘርፍ መሳተፍ የሚፈልግ በመሆኑ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ እንዲያዝለት ጠይቋል፡፡

በኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰዒድ አል መሃይሪ ለኤምባሲው የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሚያካሂዳቸው የቤቶችና ሌሎች የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ሰነዶችን አቅርቧል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ የተለያዩ የኮንስትራክሽን ዕድሎች ተሳታፊ ለመሆን ስለምንፈልግ፣ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ይዘን ለመምጣት ፍላጐት አድሮብናል፤›› ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው በደብዳቤው ፍላጐታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኤምባሲው የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ከኩባንያው ጋር ማገናኘቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡

መንግሥት የቤቶች ግንባታ የሚያካሂዱ ኩባንያዎችን ለመምረጥ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ባወጣው ጨረታ 28 ተወዳዳሪዎችን አግኝቷል፡፡ የወጣው ጨረታ ቅድመ ማጣሪያ ሲሆን፣ የአሸናፊዎች መረጣ ለማካሄድ በሒደት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

ከዱባዩ ኩባንያ ፕሮፖዛል በኋላ መንግሥት በጨረታው ይቀጥላል? ወይስ የኩባንያውን ፕሮጀክት ተቀብሎ ጨረታውን ይሰርዛል? ለሚለው ጥያቄ ምላሹ በቀጣይ የሚታወቅ መሆኑን ምንጮች አመልክተዋል፡፡

ፒቮት ኢንጂነሪንግና ኮንትራክቲንግ ኩባንያ እ.ኤ.አ. በ1978 አቡዳቢ ውስጥ የተመሠረተ ሲሆን፣ በዱባይና በሻርጃ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች