Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየአማራ ክልል ነዋሪዎች የመሠረተ ልማት ችግሮች ኑሮአችንን አክብደውታል አሉ

የአማራ ክልል ነዋሪዎች የመሠረተ ልማት ችግሮች ኑሮአችንን አክብደውታል አሉ

ቀን:

በአማራ ክልል የሚገኙ አራት ዞኖች የመሠረተ ልማት አውታሮች ችግሮች እንዳለባቸው አስታወቁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች ባወያዩበት ወቅት፣ ነዋሪዎቹ በዋናነት የመንገድ፣ የኤሌክትሪክና የትምህርት ተቋማት ችግሮች እንዳሉባቸው ገልጸዋል፡፡

የካቲት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. በኮምቦልቻ ከተማ በተካሄደው ውይይት ላይ ከሰሜን ሸዋ፣ ከደቡብ ወሎ፣ ከሰሜን ወሎና ከኦሮሚያ ልዩ ዞን የተወከሉ ነዋሪዎች፣ የመሠረተ ልማት አለመሟላት ኑሮአቸውን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡

ከደቡብ ወሎ ባሉካ ወረዳ ተወካይ የሆኑት አቶ ኃይለ ማርያም አሰፋ በግብርናና በንግድ ሥራ ይተዳደራሉ፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም እንዳሉት፣ ለወፍጮ ቤታቸው የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ለማስገባት ክፍያ የፈጸሙት በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ነገር ግን ባለፉት አራት ዓመታት ቆጣሪው አልገባላቸውም፡፡ ገንዘቡም ያለ ወለድ ታስሮ ቀረብኝ ብለዋል፡፡

- Advertisement -

አቶ ኃይለ ማርያም ከእሳቸው በተጨማሪ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎችም ይህ ችግር ገጥሟቸዋል ብለዋል፡፡ አንድ ወዳጃቸው ትራንስፎርመር ለማስገባት ሁለት መቶ ሺሕ ብር ከፍሎ ቢጠብቅም ትራንስፎርመሩ የውኃ ሽታ ሆኖ መቅረቱን አስረድተዋል፡፡

ከብዙ ቆይታ በኋላ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ኃላፊዎች ዕቃዎቹ በቀድሞ ዋጋ ስለማይገኙ ገንዘብ ጨምሩ ብለዋል ሲሉ አቶ ኃይለ ማርያም ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኔ ተጨማሪ 60 ሺሕ ብር፣ ወዳጄ ተጨማሪ 130 ሺሕ ብር እንድንከፍል ተጠይቀናል፡፡ ይህ ችግር የተፈጠረው በመንግሥት ሆኖ እያለ ለምን እኛ እንጠየቃለን?›› በማለት አቶ ኃይለ ማርያም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል፡፡

ከአራቱም ክልሎች የመጡ ተወካዮች ተመሳሳይ የኤሌክትሪክ ችግር እንዳለባቸው ጠቅሰው፣ በተጨማሪም የኃይል አቅርቦት ችግር እንደገጠማቸው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡ ጎልተው ከተነሱ ችግሮች መካከል የገጠር መንገዶች ለረዥም ጊዜ በማገልገላቸው ምክንያት፣ ከጥቅም ውጪ መሆናቸውንና በአንዳንድ ቦታዎች መንገዶች በክረምት ተሽከርካሪዎችን የማያስተናግዱ በመሆኑ፣ እንዲሁም ጭራሹኑ የመንገድ አውታር የሌላቸው የምሥራቅ አማራ አካባቢዎች እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡

ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ከሚሴ ከተማ የተወከሉት ግለሰብ እንዳሉት፣ ዞኑ ሰባት ወረዳዎች አሉት፡፡ እነዚህ ወረዳዎች በሙሉ ከአፋር ብሔራዊ ክልል ጋር ይጎራበታሉ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ያሉት መንገዶች በክረምት ጥቅም የማይሰጡ በመሆናቸው፣ ከባድ ችግር እንደሆነባቸው ጠቁመዋል፡፡ አካባቢው በአሁኑ ወቅት ከምንጊዜውም የተሻለ ፀጥታ ቢኖረውም፣ ምናልባት የፀጥታ ችግር ቢነሳ ችግሩን ለመፍታት አስቸጋሪ ሁኔታ የሚፈጠር በመሆኑ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአፋርና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ነዋሪዎች አብረው እንደሚማሩ፣ ወደፊት መጋባት ሊኖር ስለሚችልና ይህም የአካባቢውን ሰላም የሚያሳድግ በመሆኑ፣ ለማኅበራዊ ግንኙነቱም ቢሆን የመንገዶቹ መገንባት ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በ2001 ዓ.ም. አካባቢውን በጎበኙበት ወቅት ከጎንጎፍቱ፣ መራኛ፣ ዓለም ከተማ ደጎሎ ድረስ ያለው መንገድ እንደሚገነባ ተስፋ ሰጥተው እንደነበር ያስታወሱት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ መንገዱ እስካሁን አለመገንባቱን ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህ ችግሮች በተጨማሪ አንዳንድ ዞኖች ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲገነቡላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ከነዋሪዎች የተነሱትን ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበጎ መመልከታቸውን ጠቅሰው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የመንገድ ግንባታን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፣ የመጀመሪያው የገጠር ቀበሌዎችን ማገናኘት ነው ብለው፣ ይህ ፕሮጀክት በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በመቶ ቢሊዮን ብር ወጪ በአሥር ሺዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትር ለመገንባት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዕቅድ አማራ ክልል እስካሁን ሰባት ሺሕ ኪሎ ሜትር መንገድ መገንባቱን፣ ሁሉንም መንገዶች በአንድ ጊዜ በአስፓልት ደረጃ ማሳደግ የማይቻል በመሆኑ በሒደት ወደ አስፓልት ደረጃ እንደሚያድግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡ ቃል ተገብተው ያልተገነቡ መንገዶችን በሚመለከትም፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የመዘገበው በመሆኑ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ እንዲካተት በቅርብ እንደሚከታተሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ገብተዋል፡፡

ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎችን በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመልሱ፣ ‹‹የኮሌጆችን ግንባታ የሚመለከታቸው ክልሎች ናቸው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችን በሚመለከት ኢትዮጵያ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎችን በፍጥነት በመገንባት የሚተካከላት የለም፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ ኢሕአዴግ አገሪቱን ሲቆጣጠር አንደኛውን ኮሌጅ ማለት ይቀላል (ሐሮማያ) ግብርና ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ይሰየም እንጂ፣ ግብርና የሚያስተምር ኮሌጅ ነበር፡፡ ከዚያ ተነስቶ መንግሥት በአሥር ዓመት ውስጥ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች አደራጀ፡፡ ከዚያም ባለው አምስት ዓመት 13 ዩኒቨርሲቲዎች አደራጀ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ባለው ወሎ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በአገር ደረጃ አሥር ዩኒቨርሲቲዎች አደራጀ፡፡ በሚቀጥለው አምስት ዓመት ደግሞ 11 ዩኒቨርሲቲዎችን ለማደራጀት አቅዷል፡፡ ቀደም ሲል አንድ ዩኒቨርሲቲ ለአምስት ሚሊዮን ሰው ነበር፡፡ ሁለተኛው ዙር ሲጀመር አንድ ዩኒቨርሲቲ ለ3.5 ሚሊዮን ሰው ነበር፣ ሦስተኛው ዙር ላይ አንድ ዩኒቨርሲቲ ለሦስት ሚሊዮን ነበር፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ አንድ ዩኒቨርሲቲ ለ1.5 ሚሊዮን ሰው እንዲደርስ እናደርጋለን፡፡ በዚህ መሠረት ነው የምንጓዘው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ ምሥራቅ አማራም የዚሁ ዕቅድ አባል ከመሆኑም በተጨማሪ ለዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተጥሎለታል፡፡ ሌላው የኤሌክትሪክ ጥያቄ ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ጉዳይ የትራንስፎርመርና የቆጣሪ ብቻ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በእርግጥ እናንተ የሚመለከታችሁ የትራንስፎርመርና የቆጣሪ ነው፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ተጠቃሚ ነዋሪዎቹ ጥያቄው ትክክል መሆኑን አቶ ኃይለ ማርያም ገልጸው፣ ጉዳዩ እንደ መንግሥት ሲታይ ዋናው ችግር እስካሁን የተዘረጉት መስመሮች እነዚህን ቆጣሪዎችና ትራንስፎርመሮች የመጠቀም አቅም በውስጣቸው ስለሌለ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹የመጀመሪያው ሥራ ትራንስፎርመሩ ዝም ብሎ ቢተከል ሥራችሁን ይረብሻል፡፡ እንዲሁም ከእናንተ ጋር የበለጠ እንጣላለን፡፡ ቆጣሪ ተክለን ኤሌክትሪክ ካልሰጠን የበለጠ እንጣላለን፤›› ሲሉ አቶ ኃይለ ማርያም ለነዋሪዎቹ ተወካዮች አስረድተዋል፡፡

‹‹አሁን እያደረግን ያለነው ሰብስቴሽኖችን በፍጥነት መሥራት ነው፡፡ ሕዝብ እየታገሰን፣ ሰብስቴሽኖችን እንሥራ ብለን ከውጭ ዕቃ እያመጣን ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን እነዚህ ችግሮች በሌሉባቸው አካባቢዎች ትራንስፎርመርና ቆጣሪ ያልገጠሙ እንዳሉ ደርሰንበታል፡፡ ይኼ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መሥሪያ ቤት ችግር ነው፡፡ ይህን የመልካም አስተዳደር ችግር እንፈታለን፤›› በማለት ችግሩን ለመፍታት ከአዲስ አበባ መጀመሩን የተናገሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ በቀጣይነት ወደ ክልልና ዞን ከተሞች እንደሚሸጋገር አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...