Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከቂሊንጦ ቃጠሎ ጋር በተገናኘ የመብት ጥሰት መፈጸሙን አረጋገጠ

ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከቂሊንጦ ቃጠሎ ጋር በተገናኘ የመብት ጥሰት መፈጸሙን አረጋገጠ

ቀን:

ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በቂሊንጦ ማረፊያ ቤት ላይ ከደረሰ የእሳት ቃጠሎ ጋር በተገናኘ፣ 16 እስረኞች አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑንና የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አረጋገጠ፡፡

በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ መዘገብ 38 ተከሳሾች በቃጠሎው ተጠርጥረው ከታሰሩ በኋላ፣ ቃጠሎውን እነሱ እንዳስነሱ እንዲያምኑ ለማድረግ በቂሊንጦ የቀጠሮ ማረፊያ ቤት አስተዳደር አማካይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደደረሰባቸው ለፍርድ ቤት በማመልከታቸው፣ ኮሚሽኑ አጣርቶ ሪፖርት እንዲያደርግ በታዘዘው መሠረት ማጣራቱ ታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ የሪፖርተር ምንጮች እንዳረጋገጡት፣ ኮሚሽኑ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸም አለመፈጸሙን ያጣራው፣ ተጠርጣሪዎቹ በሚገኙበት ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት በመገኘት ነው፡፡ የቂሊንጦ ማረፊያ ቤት በመቃጠሉ የተወሰኑ እስረኞች ወደ ሸዋሮቢትና ዝዋይ ማረሚያ ቤቶች መዛወራቸው ይታወሳል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ለፍርድ ቤቱ ያመለከቱት በቂ ብርሃን በሌለበትና ጨለማ በሆነ ጠባብ ቤት ውስጥ 38 እስረኞች እንዲኖሩ መደረጋቸውን፣ የተለያዩ ድብደባዎች እንደተፈጸመባቸው ኮሚሽኑ ከፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መረዳት መቻሉን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

ኮሚሽኑ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ተገኝቶ ከታራሚዎቹ እንዳጣራው፣ የቂሊንጦ ማቆያ ማረፊያ ቤት ቃጠሎ ላይ ተሳትፎ እንዳላቸው የተለዩ ታራሚዎች ወደ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ማመን አለባችሁ እየተባሉ የተለያየ ዓይነት ድብደባ እንደተፈጸመባቸው (የድብደባው ዓይነት በዝርዝር ተገልጿል)፣ ክብረ ነክ ስድብ መሰደባቸውን፣ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደ ደረሰባቸው ለኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን መናገራቸውን፣ የኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን በጥናቱ አስፍሯል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ከታራሚዎቹ እንደተገለጸለት ለሦስት ወራት ያህል በካቴና ታስረው መክረማቸውን፣ በሰውነታቸው ላይ ከቀረ ምልክት በማየት ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የተፈጸመባቸውን ኢሰብዓዊ ድርጊት፣ የደረሰባቸውን አካላዊ ጉዳት በማሳየት በፎቶ እንዲያዝላቸው የጠየቁ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ሊቀበላቸው እንዳልቻለ ለኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ማስረዳታቸውም ተጠቅሷል፡፡

ፍርድ ቤት ቀርበው የደረሰባቸውን በመናገራቸው ወደ ማረሚያ ቤት ሲመለሱ ለሦስት ወራት ጨለማ ቤት ውስጥ እንዲቆዩ መደረጋቸውንና ቀን ቀን መናፈስ እንደማይፈቀድላቸው፣ ከግንቦት ወር 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በማግለያ ክፍል ውስጥ መሆናቸውን እንዳስረዱት የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ተናግሯል፡፡

የኮሚሽኑ አጥኝ ቡድን ለአዲስ አበባ ቂሊንጦ ማረፊያ ቤት ኃላፊ ታራሚዎቹ ደረሰብን ስላሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚመለከት ጥያቄ አቅርቦላቸዋል፡፡

እሳቸው እንደተናገሩት ቃጠሎው በደረሰበት ወቅት እሳቸው ዝዋይ ማረሚያ ቤት ነበሩ፡፡ ከቃጠሎው በኋላ ማቆያ ሥፍራ ባለመኖሩ ምክንያት ታራሚዎቹ ወደ ዝዋይና ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤቶች እንዲሄዱ መደረጋቸውንና በቆይታቸውም ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰባቸው እንዳብራሩ በኮሚሽኑ የሪፖርተር ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በጨለማ ቤት ስለመታሰራቸው ተጠይቀው፣ የቀጠሮ ማረፊያ ቤት ጨለማ ቤት እንደሌለው፣ ሁሉም ነገር የተሟላለት ማለትም መፀዳጃ ቤትና ቴሌቪዥን ያለው ራሱን የቻለ ግቢ መሆኑን እንደተናገሩ የጥናት ቡድኑ ማስረዳቱ ታውቋል፡፡  

አጥኝ ቡድኑ በታሳሪዎቹ ሰውነት ላይ ባደረገው ምልከታ የጣቶች ስብራት፣ የካቴና ምልክት፣ ሰፊና ጠባብ ጠባሳዎች፣ የድብደባ ምልክቶች፣ የጥፍር መውለቅና የተለያዩ የጉዳት ምልክቶችን በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻቸው ላይ መመልከቱን አጥኚ ቡድኑ ማረጋገጡን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

አጥኚ ቡድኑ ታራሚዎች ወደ ማረሚያ ቤቱ ሲገቡ የተመዘገቡ የግል ማኅደራቸውን ተመልክቶ፣ ሰባት ታራሚዎች በአንዳንድ የሰውነት ክፍላቸው ላይ ትንንሽ ጠባሳ መኖሩን ከማስረዳት ባለፈ፣ በጥናቱ እንዳዩት የተጋነነ ምልክት እንዳልነበረባቸው ማረጋገጡንም ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ማረጋገጥ እንደቻለው አቤቱታ ያቀረቡት ታራሚዎች በማኅደራቸው ከሰፈረው አካላዊ ሁኔታዎች በተለየ በሰውነታቸው ላይ ጠባሳዎች፣ ግርፋት የሚመስሉ ምልክቶችና የካቴና እስር ምልክቶች እንዳለባቸው ማስተዋል መቻሉን ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ በሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት በተደረገላቸው ምርመራ አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ማረጋገጡን ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከመርማሪው ቡድኑ የደረሰውን ሪፖርት ካየ በኋላ፣ ለማረሚያ ቤቱ ምክረ ሐሳብ ማቅረቡም ተጠቁሟል፡፡ በተለይ 16 ታራሚዎች የተደነገገው የአካል ደኅንነት መብታቸው መከበር እንዳለበት ኮሚሽኑ ገልጾ፣ በአካላቸው ላይ የታዩት ምልክቶች መንስዔና የታራሚዎቹን ንብረት በተመለከተ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ክፍልና የሕክምና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ፣ ለሚመለከተው አካል እንዲያስተላልፉና ለኮሚሽኑ እንዲያሳውቁ ምክረ ሐሳብ ማቅረቡ ታውቋል፡፡

 

 

 

                                                                                                                                

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...