Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከአይኤስ የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ 26 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ...

ከአይኤስ የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ 26 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመሠረተ

ቀን:

  • በኢትዮጵያ የጅሐድ ጦርነት ለማወጅ ዝግጅት እያደረጉ ነበር ተብሏል

አይኤስ ከሚባለው የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉና በአዲስ አበባ፣ በሐረርና በአላባ ከተሞች ውስጥ ቡድን በማደራጀትና በማስተባበር ላይ እያሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተገለጸ 26 ተጠርጣሪዎች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ተከሳሾቹ አክራሪና ፅንፈኛ ሃይማኖታዊ ርዕዮተ ዓለም በመያዝና ዓላማቸውን ለማሳካት፣ ራሱን አይኤስ ብሎ ከሚጠራው የሽብር ቡድን ጋር ትስስር በመፍጠር፣ በሶማሊያ ቦሳሶ ከሚገኘው ከኤይኤስ ክንፍ ጋር ተገናኝተው ወታደራዊ ሥልጠና መውሰዳቸውን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸው ክስ ያስረዳል፡፡ ተከሳሾቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሥልጠናውን ወስደው ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ የጅሐድ ጦርነት ለማወጅ በእንቅስቃሴ ላይ እያሉ መሆኑንም፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡

አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ኦሮሚያ፣ ሐረሪ፣ ደቡብና አማራ ክልሎች የሚኖሩ መሆናቸውን በክስ ቻርጁ ላይ የተጠቀሰው አድራሻቸው ይጠቁማል፡፡

ተከሳሾቹ በሕገ መንግሥቱ የተከበረውን የሃይማኖትና እምነት ነፃነት የሚቃረን፣ እንዲሁም ከእነሱ እምነት፣ አስተሳሰብና አስተምህሮ ውጪ በኢትዮጵያ ሊኖር እንደማይገባ የሚገልጽ አክራሪና ፅንፈኛ እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት እየተዘዋወሩ ወጣቶችን ይመለምሉና ያስተባብሩ እንደነበር ክሱ ይገልጻል፡፡

ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ የሽብር ቡድኑ ድምፅ ነው በሚባለው ‹‹ቢላል ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ›› የሬዲዮ ድምፅ አማካይነት፣ ዕርዳታ ያሰባስቡ እንደነበረም ጠቁሟል፡፡ በእስልምና  ሃይማኖት ሽፋን አመፅ ለመደገፍ ገንዘብ እያሰባሰቡ እንደነበርም በክሱ ተገልጿል፡፡   

‹‹እስላማዊ ታጋዮች›› በሚል ድረ ገጽና በ‹‹ዋትስአፕ›› አማካይነት በተለያዩ አገሮች ከሚገኙ የሽብር ቡድኑ አመራሮችም ጋር ይገናኙ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡

በተለይ አሜሪካ ከሚገኘው አብድልሀብ ከሚባል የሽብር ቡድኑ አመራርና በሱዳን ከሚገኙ አመራሮች ጋር በስልክና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በመገናኘት፣ የተለያዩ ተልዕኮዎችን ለመፈጸም ትዕዛዝ ይቀበሉ እንደነበር በክሱ ተጠቁሟል፡፡

በቅፅል ስሙ አቡ አብደላ የሚባለው በክሪ አወል የተባለው አንደኛ ተከሳሽ፣ በጅዳና በየመን የአይኤስን የሽብር ቡድን በገንዘብ የማገዝ ሥራ ሲያከናውን ቆይቶ፣ በሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ፣ አሜሪካ ከሚገኘው የሽብር ቡድኑ አመራር ጋር ሲገናኝ እንደነበር ክሱ ያስረዳል፡፡ ተከሳሹ ‹‹አል ሸሪያ›› በሚባል ቡድን አማካይነት ኢትዮጵያ ውስጥ የጅሐድ ጦርነት ለማወጅ፣ በቅፅል ስሙ አቡዜር ከሚባለው ሁለተኛ ተከሳሽ መሐመድ ሐሰን ጋር በመገናኘት፣ የጅሐድ ጦርነት ስለሚጀመርበት ቀን ሲወያዩ መክረማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

የሽብር ቡድኑን ለማጠናከር አባላትን ሲመለምሉ፣ የጦር መሣሪያ የሚታጠቁበትን ሁኔታ ሲያመቻቹና ለሙስሊሙ ጥሩ አስተሳሰብ አለው ብለው ከሚያምኑት አይኤስ የሽብር ቡድን ጋር፣ ወታደራዊ ሥልጠና ለመውሰድ መስማማታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡ ስምምነታቸውን በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ዓለም ባንክ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው አብዱ ሙስጠፋ በሚባለው ተከሳሽ ቤት ተሰባስበው፣ ለሥልጠና ወደ ሶማሊያ ለመሄድ ውሳኔ ማሳለፋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አክሏል፡፡ ሥልጠና ወስደው ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ የጅሐድ ጦርነት በመጀመር እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት ስምምነት ካደረጉ በኋላ፣ ወደ ሥልጠና ቦታ ለመሄድ ጉዞ ሲጀምሩ ሚያዝያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

አብዛኛዎቹ ተከሳሾች ሐረርና አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም አክሏል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ በአዲስ አበባ፣ ሐረርና አላባ ውስጥ የሚገኙትን የሽብር ቡድን በመምራት፣ በማደራጀት፣ በአመራርነት በመሳተፋቸውና የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ) እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ፣ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በማንኛውም መንገድ መሳተፍ ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡

ተከሳሾቹ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀርበው ክሱ ተነቦላቸዋል፡፡ የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለታኅሳስ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡    

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...