Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከመቐለ ታጁራ ወደብ በ3.2 ቢሊዮን ዶላር ለሚገነባው የባቡር መስመር የመሠረት ድንጋይ ሊቀመጥ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከመቐለ እስከ ጂቡቲ ታጁራ ወደብ ድረስ በ3.2 ቢሊዮን ዶላር ለሚገነባው የባቡር ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ሊጣል ነው፡፡ የመሠረት ድንጋይ የሚጣለው የካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ፣ የካቲት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ደግሞ በወልዲያ (ሃራ ገበያ) መሆኑ ታውቋል፡፡

የመሠረት ድንጋይ የሚቀመጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተገኙበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ውል የተገባለት በ2005 ዓ.ም. ቢሆንም፣ በፋይናንስና በወረቀት ሥራዎች መጓተት ምክንያት ግንባታውን ለመጀመር አለመቻሉ ተገልጿል፡፡

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት እነዚህ ሥራዎች በመጠናቀቃቸው ከሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) 40ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ጋር ተያይዞ የመሠረት ድንጋይ እንዲቀመጥና ግንባታውም እንዲጀመር ቀን መቆረጡን፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ደረጄ ተፈራ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የሕወሓትን የምሥረታ በዓልን ለማክበር ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሚገኙበት ፕሮግራም ላይ የመሠረቱ ድንጋይ እንደሚቀመጥ ተገልጿል፡፡

757 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በሁለት ክፍል ተከፍሎ የሚካሄድ ነው፡፡ የመጀመሪያው ከመቐለ እስከ ወልዲያ (ሃራ ገበያ) የሚገነባውን 368 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ቻይና ኮሙዩኒኬሽንስ ኮንስትራክሽን ካምፓኒ (ሲሲሲሲ) ተረክቧል፡፡ ይህ ግንባታ 1.6 ቢሊዮን ዶላር የሚፈልግ ሲሆን፣ ገንዘቡ ከቻይና ኤግዚም ባንክ አንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ቀሪውን 389 ኪሎ ሜትር ግንባታ የሚያሂደው የቱርክ ኩባንያ ያፒ ማርከንዚ ነው፡፡ ይህ ግንባታ 1.7 ቢሊዮን ዶላር የሚፈልግ ሲሆን፣ ገንዘቡ ከቱርክ መንግሥትና ከክሬዲት ስዊስ መገኘቱ ተገልጿል፡፡ ለፕሮጀክቶቹ የኢትዮጵያ መንግሥት የራሱ የገንዘብ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

የባቡር መስመሩ ሰሜን ኢትዮጵያን ከማዕከላዊው የአገሪቱ ክፍል ከማገናኘቱም በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ ዋነኛ የወጪና ገቢ ንግድ በር ከሆነው ጂቡቲ ወደብ ጋር ያገናኛል፡፡

አቶ ደረጀ እንዳሉት፣ ሁለቱ ኮንትራክተሮች ግንባታውን ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት አጠናቀው ለግንባታው የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን በማጓጓዝ ላይ ይገኛሉ፡፡  

ይህ የባቡር መስመር ተርሚናሎችና ታናሎች የሚኖሩት ሲሆን፣ የባቡር አገልገሎቱ ለዕቃና ለሰዎች ማጓጓዣ አገልገሎት ይውላል፡፡ ፕሮጀክቱ በሦስት ዓመት ተኩል ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች