Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አስታራቂ ጠፍቶ ድንጋይ አቀባይ በዛ!

ሰላም! ሰላም! እንዴት ይዟችኋል? በቃ ‘አድቬንቸር ሙቪ’ እያየ በ‘አድቬንቸር’ የሚኖረው አላስቀምጥ አለ አይደል? ጉድ እኮ ነው! ‘በ24 ሰዓት ውስጥ፣ በ48 ሰዓት ውስጥ ያልናችሁን ካላደረግናችሁ ሰዋችሁን አታገኙትም’ ብሎ ነገር የምናውቀው በሲኒማ ነበር። አሁን አሁን ሲኒማ ይሁን የገሀዱ ዓለም ነፀብራቅ ወይም ዓለም ራሷ መለየት አቅቶናል። የምሬን እኮ ነው! ማን ገልባጭ ማን ተገልባጭ እንደሆነ ግራ የገባው ዓለም። ዝም ብሎ ብቻ አንዱ ካንዱ፣ ያ ከዚህ ሲገለባበጥ እኛ በመሀል ባገኘነው አጋጣሚ ‘ቻፓ’ ለማገለባበጥ ስንራወጥ በምንሰማውና በምናየው ነገር ግራ መጋባት። አለቀ! ታዲያ ባሻዬ ሰሞኑን ምን እንዳሉኝ ነግሬያችኋለሁ? “ሲኒማ ቤቶች ጉድ ፈላባቸው” አሉኝ አቦል ቡናቸውን ፉት እንዳሉ። “እንዴት?” ስላቸው “ሰው በቀጥታ ሥርጭት ይኼው የአጋች ታጋች ድራማ እያየ ለምን ብሎ ሲኒማ ከፍሎ ይገባል? አይገባም!” ብለው እኔ ላይ አፈጠጡ።

ባሻዬ ፊልም ሲባል የሚታያቸው ነገር ሰዶ የማሳደድ ትዕይት እንደሆነ አስታወስኩ። አንዱ ሲሮጥ አንዱ ሲያባርር ካላዩ ብዙ ጊዜ ታላቅ ፊልምን ረግጠው ይተኙ እንደነበር ልጃቸው ያጫወተኝ ትዝ አለኝ። ታዲያ ዛሬ ዛሬ ኑሮና ብልኃቱ አልገጣጠም እያለ ሰዶ የማሳደድ ‘ሙቪ’ ራሳችን መሥራት በመጀመራችን እንደ ባሻዬ ቁጭ ብሎ በአክተር ‘ትሪክ’ ከመመሰጥ ኑሮ በሚያሠራን በራሳችን ‘ሰርከስ’ መዝናናት እየበለጠብን መምጣቱን አምኛለሁ። ሰው መቼስ ለጉድ አይደል የተፈጠረው? እውነቴን እኮ ነው! ትከሻው አይችለው ሸክም፣ ዓይኑ አይቆጥረው መከራ የለም ስላችሁ። ግን በአባራሪነትና በተባራሪነት ተቦዳድነን እስከ መቼ ይሆን አባሮሹን የምንቀጥለው? ኧረ የሰላም ያለህ በሉ!

እና አደራችሁ መንገድ ስትሄዱ የሚከተላችሁን ሰው እያጤናችሁ ተጓዙ። ሰው አያየኝም ብላችሁ የማይገባ ሥፍራ ፊኛችሁን ልታስተነፍሱ ምናምን መሽሎክሎክ አታብዙ። የምሬን ነው! ብዙ ሰዓት ከሰው ተገንጥላችሁ አታሳልፉ። ምንም እንኳ ዘመኑ የግለኝነት እንደሆነ ባውቅም ቢያንስ ብትጮሁ ሰው የሚሰማበት ሥፍራ ጠጋ ጠጋ በሉ። አጥፊው ቢሆንም ለሰው መድኃኒቱ ደግሞ ሰው ነው። መማል ይጠበቅብኛል? አዎ!  እናም በዛሬ ጊዜ እንደ አገርም እንደ ግለሰብም ጠላታችን ብዙ ነው። ይኼ አይኤስአይኤስ የሚሉት የሰሞነኛ ጽንፈኛ ቡድን አይበለውና አንዳችንን ይዞ የሩሲያ ማፊያዎች በፊልም ሲያለማምዱን እንደኖሩት 24 ሰዓት ወስኖ ‘የዓባይን ግድብ ካላቆማችሁ’ ወይም ‘በISIS Z ብላችሁ ለድርጅቴ የገንዘብ ድጋፍ ካላደረጋችሁ’ ቢለን ምን አባታችን እንሆናለን? አስቡት እስኪ! ማሰብ ጥሩ ነው። ማሰብ እየደከመንና እየሰለቸን እኮ ነው ያላሰብነው ነገር ባላሰብነው አሳቻ ሰዓት አድብቶ  ቁም ስቅላችንን ያሳየን። አይደል እንዴ?

ታዲያ የባሻዬ ልጅ ከራሴ ጋር የምነጋገርበትን ይኼን የመጥለፍና የመጠለፍ ሰሞነኛ ነገር አንስቶ፣ “አንበርብር እባክህ አንተ በሥራህ ከብዙ ሰዎች ጋር ትገናኛለህ፣ ትውላለህ። አደራ እየተጠነቀቅክ። ኋላ በጃፓን የደረሰው በእኛ ቢደርስ እንኳን ሊያስለቅቅህ የሚረባረብልህ አካል ዜና የሚሠራብህ ጋዜጠኛ የሚኖር አይመስለኝም፤” አለኝ። በጣም ደነገጥኩ። “ያን ያህል?” ስለው፣ “እመነኝ ያን ያህል!” አለኝ በእርግጠኝነት። “እንዴ እኔ እኮ ልማታዊ ደላላ ነኝ፤” ስለው “ብትሆንም ግለሰብ ነህ። አንድ ነህ፤” አለኝ። “ቢያንስ ለምርጫ ቅስቀሳ ፍጆታ እንድውል ታስቦ አንድ ነገር የሚያደርግልኝ አካል አጣለሁ?” ስለው የምር የታገትኩ መስሎኝ ዙሪያ ገባዬን እጅና እግሬን መነጠርኩ። የባሻዬ ልጅ፣ “የቀላል ባቡር ሥራው አልቆ አገልግሎት ሊጀምር ተቃርቦ፣ ከ70 ሺሕ በላይ የቁጠባ ቤቶች ዕጣ ሊወጣ ሽር ጉድ እየተባለ፣ አንተን አስለቅቆ የፖለቲካም ሆነ የሞራል ትርፍ ለማግኘት የሚጥር አይኖርም። እርምህን አውጣ!” ብሎ ቁርጤን ነገረኝ። እኔም ‘ምነው ሰው ከምሆን ባቡር ባደረገኝ’ እያልኩ ጥቂት ደቂቃዎች በቁጭት አበድኩ። የእብደት ዘመን!

አንዴ በዚህ አንዴ በዚያ የምሽሎከለከው በአጭሩ ምን ልላችሁ ፈልጌ መሰላችሁ? ለራሳችሁና ለሕይወታችሁ ዋጋ ስጡ ለማለት ነው። አለበለዚያ ግን አያችሁ ከመጠለፋችሁ በፊት ብዙ እርግጫዎችን ማስተናገዳችሁ አይቀሬ ነው። እኔ ደላላው አንበርብር በገዛ ሕይወቴ ቤተ ሙከራ ውስጥ ያረጋገጥኩት ነገር ቢኖር ዓለምን ከካርቦን ልቀት ቀጥሎ እያበላሻት ያለው ዝምታ ነው። ማንጠግቦሽ በዚህ ባትስማማም። “‘ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባም’ እያልን ስንቱ አፍንጫችን ላይ ቆሞ ደነሰብን?” ስላት መልሷ ዝምታ ነው። ዋሸሁ ግን? አሁን በቀደም ዕለት ምን ሆነ መሰላችሁ? መቼም እኔ እንደምታውቁኝ ይሉኝታ አለብኝ። የድሮ ልጅ ነኛ። አሁን ባለመፈጠሬ የሚቆጨኝ ነገር አንዱ ይኼ በይሉንታ አንደኛ መሆኔ፣ መብትንና የላብን ዋጋ መጠየቅን እንደ ግብዝነትና ስግብግብነት መቁጠሬ ነው።

ታዲያ አንድ ትልቅ ዘመናዊ ቪላ በሚሊዮኖች (ምድር ላይ 100 ዓመት ለመቆየታችን እርግጠኛ ያልሆንን ሰዎች፣ ግማሹን ዕድሜ በሥራ ወይም በዝርፊያ አገባደን ምን ያህል እንደምንሰነብትበት ሳናውቅ በሚሊዮኖች ቪላ ስንሸምት ካለን ምን ይለናል?) አሻሽጬ ሳበቃ ‘ኮሚሽኔን’ ለመቀበል ሁለት ሦስት ቀን ፊቴን አስመታሁ። ሒሳቤን ብዬ አፍ አውጥቼ እንዳልጠይቅ ሻጭም ገዢም በዕድሜ የበሰሉ አዛውንቶች ናቸውና ‘ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች’ ይሆናል ብዬ ተቸገርኩ። የመመላለሴ ሚስጥር ይገባቸዋል ብዬ ብዙ ተመላለስኩ። ግን አልገባቸውም። የገባቸው ዝምታዬ ሞኝነት እንደሆነ ነው። ስንቱ አስተዋይና አራዳ ይሆን ዝም ስላለ ብቻ ሊሞኝ የታጨው? አወይ በረባ ባረባው ስንተዛዘብ የምናባክነው ዕድሜያችን? የምር! የራሳችንን የባከነ ዕድሜ ሳንቆጥር ገዥዎቻችን ተኝተው ሳይሠሩ ያባከኑትን ዕድሜ ስንቆጥር ግን የሚደርስብን የለም!

መጨረሻ ላይ መቼስ ወንድ ልጅ የተነሳበት ቀን ነገሩ አበቃ ማለት አይደል (ኦ ለካ ዛሬ ጊዜ ሴቶችም ይነሳባቸዋል። አታዩም እንዴ ዓለምን ጉድ የሚያሰኙትን ሴት ታጣቂዎችና አሸባሪዎች) “ገንዘቤን” አልኩ። ስንት ሥራ እንዳመለጠኝ እኮ እናንተ ስላላወቃችሁ ነው። አንድ ቀን እንዲያውም የባሻዬ ልጅ፣ “ያንን ገንዘብ አልተቀበልክም?” ብሎ ሲጠይቀኝ ተበሳጭቼ ሕዝብ እየሰማኝ፣ “በገዛ አገራችን ድንኳን መትከያ የምትሆን ሥፍራ አጥተን፣ በኔትወርክ ተማረን፣ በትራንስፖርት ችግር ተመረን፣ (ውኃና መብራት እንኳ አብሮ አደጎቻችን ናቸው) ጭራሽ ሰው የላቡን የጉልበቱን ምንዳ ለምኖ ይበላል?” ብዬ አቀለጥኩት። ያው እንደምታውቁት ብሶት ተባብሶ ‘ዘራፍ ዘራፍ!’ ሲያስብል ሰው በለመደበት አፉ አብዷል ብሎ ከንፈር እየመጠጠ ተጠቋቆመብኝ። ሐሜታውን ልሸሽ በተውኩት መንገድ በኩል ስጓዝ ደግሞ አንድ የሚያውቀኝ ሰው፣ “እባክህ  አሁን የቁጠባ ቤቶች ዕጣ ሲወጣ እኔም ዕጣው ውስጥ እንድካተት የተወሰነ ብር አበድረኝ፤” አይለኝም? ‘እሱ ምን ያድርግ? ሌላ ጊዜ በይሉታ ሳልችል እችላለሁ ሳይኖረኝ አለኝ ብዬ አስለምጄ’ እያልኩ “ስንት ፈልገህ ነው?” ስለው፣ “አንድ 70 ሺሕ ብር አንተ ከሰጠኸኝ ሌላውን ከሌላ እሟሟታለሁ፤” ብሎኝ አረፈው። እሱ ሊሟሟት ሰው ጨምሮ ይገድላል። ግን ሰውን ምን ነካው በአያሌው? ወዲያው ለካ ያለ ምክንያት አይደለም ያለውም የሌለውም ተደምሮ ልማታዊ ባለሀብት የተባለው?  እሺታና ዝምታ ስለማያበዛ ነው’ አልኩኝ። ይህን ባልኩ ቅጽበት ባልሰማ ወዳጄን በቆመበት ትቼው ሄድኩ። ‘ኮሚሽኔንም’ አፍ አውጥቼ ዓይኔን አጉረጥርጬ ስጠይቃቸው ደንበኞቼ ወዲያው ቼክ ፈርመው ሰጡኝ። እኔምለው ግን ችክ ካላሉ ቼክ የለም በቃ?

በሉ እንሰነባበት። ይኼው እያደር ስንት የሚያስጨንቅ ስንት የሚያበሳጭ ስንት የሚያወያይ ችግር እያለብን ያልበላንን ማከክ ሥራችን ሆኗል። ካየሁትና ከሰማሁት! ምን ሆነ መሰላችሁ? እንደ ልማዳችን አንዳንድ ልንል ወደተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ጎራ ብለናል፡፡ እኔና የባሻዬ ልጅ። ጥቂት ስንጫወት ጥቂት ስንጎነጭ እንደቆየን አንድ ነገር የገባው የመሰለ ጎልማሳ ሲጃራ አውጥቶ ለኮሰ። አጠገቡ የተቀመጠው ድምፁን ከፍ አደርጎ፣ “ግድ የለም አንድ ወር እንደምንም እንታገሳለን። ካንድ ወር በኋላ ግን እዚህ ቤት ውስጥ ትምባሆ ቢጨስብን ካንተ ራስ አንወርድም!” ብሎ የግሮሰሪዋ ባለቤት ላይ አፈጠጠ። እኔና የባሻዬ ልጅ ተያየን። ግሮሰሪያችን በአጫሾችና በተቃዋሚዎቻቸው ክርክር በአንድ እግሯ ቆመች። ተቃዋሚዎችና ገዢው ፓርቲ ሲከራከሩ እንኳ ይኼን ያህል አቧራ መነሳቱን እጠራጠራለሁ። “እኮ እናያለን አሁን አዲስ የወጣው ሕግ ተፈጻሚነት ሲጀምር ያኔ አንተ ጀግና ነህ አጠገቤ ቁጭ ብለህ ከለኮስ!” ይላል አንዱ። ሌላው ተቀብሎ “አይ እኛ! ስንት ቁስልና ስንት ችግር እያለብን፣ ስንት የኑሮ ውጣ ውረድ ጣጣ አስቀምጠን፣ ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ጠባብ የዴሞክራሲያዊ ሜዳ ይዘን ለምንድነው በቀላሉ መግባባት በምንችልባቸው ጉዳዮች መነታረክ የሚቀናን?” ይላል።

የባሻዬ ልጅ ደግሞ “እውነቱን እኮ ነው! ስንት አነታራኪ የቁጥጥር ሕግ የሚያስፈልጋቸው መሠረታዊ የአኗኗር ዘይቤዬያችንን የሚያናጉ ጉዳዮች እያሉ ያልበላንን የምናከው ለምንድነው ግን?” ሲለኝ ጎል ገባ። ጭብጨባና ፉጨቱ ትግትጉን አበረደው። እኔ ደላላው አንበርብር ጤናን በተመለከተ የማያወላውል አቋም አለኝ። ሱሰኛውን ሳይሆን ሱስን አወግዛለሁ። ግን ከምናወራላቸው ሱሶች በላይ የማናወራባቸው በርካታ እንከኖች ሥር ለሥር እንደ ምስጥ ቦርቡረው ሲጥሉን ዝም ማለታችን አይገባኝም። አንዱ አባራሪ ሌላው ተባራሪ እየሆንስ እስከ መቼ እንዘልቀዋለን? በነገራችን ላይ ድሮ ወዳጆች ወይም ጎረቤታሞች ሲጣሉ ገላጋይ ወይም አስታራቂ ብዙ ነበር፡፡ ዛሬ ለምን ይሆን ድንጋይ አቀባዩ የበዛው? አስታራቂ ጠፍቶ ድንጋይ አቀባይ ሲበዛ የምፀአት ቀን የቀረበ እየመሰለኝ እደነግጣለሁ፡፡ ከድንጋጤ ይሰውራችሁ፡፡ መልካም ሰንበት!             

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት