Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅበአዲስ አበባ አራት ኪሎ በአሁን ጊዜ ቆሞ ከሚታየው የድል ሐውልት በፊት፣ ቆሞ...

በአዲስ አበባ አራት ኪሎ በአሁን ጊዜ ቆሞ ከሚታየው የድል ሐውልት በፊት፣ ቆሞ የነበረው የአክሱም ሐውልቶችን የሚመስለው ሐውልት

ቀን:

መወድስ

እሩቅ ሰው

ሰው፣ ባዶ ሰው

ስሜ ተዋናይ ነው ይህ ግጥሜን ለሰማህ

በረዶ ለበረዶ

መብረቅም ለመብረቅ ገዢና ተገዢ እንዳለው ታውቃለህ?

ታድያ!

በኃጢአተኛው የሚፈርድበት

ለፃድቁ ደግሞ በቅን ሚፈርድለት

የምጡቅ ኢዮር ሰማይ አምላክ በኢዮር ላይ መኖሩን ልቡናህ

ሲያውቀው

የሕይወቱ ዓመት በፍጥነት ለሚያልቅ ለዚህ ለባዶ ሰው

አጥንቱ ሰማይ መቃብር ለሚወርድ ለዚህ ለራቁት ሰው

በወርቅ ለመገዛት ልብህ እንዴት ከጀለ ነገ አፈር ለባሹ አምላክ

እንዲሆነው

ምክንያቱም

ይኼ የምታየው የግብዞች ዓለም ጽንስ የሆነ አበባ

ማለዳ ላይ በቅሎ ፈጥኖ ረጋፊ ነው ጣይ እንኳ ሳትገባ

እናም የሰው ልጅ ሆይ!

ለሰውና ለወርቅ መገዛትህን ተወው፡፡

ምክንያቱም፣ አልማዝና ወርቁ ባለም የምታየው

ከአንገትህ ሳይገባ ሳታጌጥበት ነው

ጊዜህ የምታልፈው፡፡

  • ኤፍሬም ሥዩም ተሰማ ‹‹ተዋናይ ብሉይ የግዕዝ ቅኔያት ፍልስፍና›› (2006)

*  *  *

 ‹‹አረ ተገላገሉ ጣጣው በዛ››

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፖስታ ቴሌፎንና ቴሌግራም ሚኒስትር የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በተገኙበት በፍርድ ቤት በራፍ ላይ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሾፌር የነበሩት ግራዝማች ኡመር ከባላጋራቸው ጋር ተጣልተው ግብግብ ይጋጠማሉ፡፡ ሁለቱም ወፍራሞችና እኩል ጉልበት ስለነበራቸው በግብግቡ ተያይዘው ይወድቃሉ፡፡ ትንቅንቁ ቀጥሎ እንዳለ አቅጣጫው ያለየለት የፈስ ጩኸት ተሰማ፡፡ በዚህ ጊዜ ነጋድራስ ‹‹አረ ተገላገሉ ጣጣው በዛ!›› አሉ ይባላል፡፡

**********

የሙጫ እሳት ራት አስደናቂ የመስማት ችሎታ

ትልቁ የሙጫ እሳት ራት እስከ ዛሬ ከሚታወቁት ፍጥረታት ሁሉ በተሻለ፣ በጣም ቀጭን (high pitch) የሆኑ ድምፆችን መስማት ይችላል። ይሁንና የስፒል አናት የሚያክሉት የዚህ ነፍሳት ጆሮዎች የተሠሩበት መንገድ በጣም ቀላል ነው።

 እንደ ጄደብሊው ድረ ገጽ ዘገባ፣ ተመራማሪዎች ይህ የእሳት ራት ያለውን የመስማት ችሎታ ለብዙ ዓመታት ሲያጠኑ ቆይተዋል። በቅርቡ ደግሞ በስኮትላንድ በሚገኘው ስትራትክላይድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉ የሳይንስ ምሁራን የተለያየ መጠን ያላቸውን ድምፆች በመጠቀም የዚህን የእሳት ራት የመስማት ችሎታ ለመለካት ሞክረዋል።

“የጆሮ ታምቡሮቹን” እርግብግቢት ከለኩ በኋላ ለመስማት በሚጠቀሙባቸው የነርቭ ሴሎች ላይ የታየውን እንቅስቃሴ መዘገቡ። የእሳት ራቶቹ እስከ 300 ኪሎ ኸርዝ የሚደርስ ድምፅ መስማት እንደሚችሉ በዚህ መንገድ አወቁ። በሌላ በኩል የሌሊት ወፎች መስማት የሚችሉት እስከ 212 ኪሎ ኸርዝ የሚደርስ ድምፅ ሲሆን ዶልፊኖች ደግሞ እስከ 160 ኪሎ ኸርዝ የሚደርስ ድምፅ ነው፤ የሰው ልጆች ግን ከ20 ኪሎ ኸርዝ የሚበልጥ ድምፅ መስማት አይችሉም።

ተመራማሪዎች የዚህን የእሳት ራት ከፍተኛ የመስማት ችሎታ መሠረት በማድረግ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መሥራት ይፈልጋሉ። በስትራትክላይድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሠሩት ዶክተር ጄምስ ዊንድሚል የእነዚህን ነፍሳት የመስማት ችሎታ በማየት “የተሻለ ጥራት ያላቸውና መጠናቸው አነስተኛ የሆነ የድምፅ ማጉያዎችን መሥራት” እንደሚቻል ተናግረዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “እነዚህ የድምፅ ማጉያዎች በሞባይል ስልኮች፣ መስማት የሚቸግራቸውን ሰዎች በሚረዱ መሣሪያዎችና በሌሎች መሣሪያዎች ውስጥ ሊገጠሙ ይችላሉ።”

* * *

የ‹‹ጂንኒ›› ወግ

በአማርኛ ‹‹ጋኔን›› የሚባለው ነገር ምን ጊዜም ቢሆን እርኩስ ነው፡፡ ደግሞም በሌሎች ላይ የሚያድር ‹‹መንፈስ›› ነው እንጂ ከሌሎች ተለይቶ የሚኖር ፍጡር አይደለም፡፡ ጋኔንን የሚገፋው ሰይጣን ነው፡፡ በሰይጣን ጦር የተወጋ ሰው ነው የ‹‹አጋንንት›› መንፈስ የሚያድርበት፡፡ ‹‹ጂንኒ›› ግን ራሷን የቻለች ፍጥረት ናት፡፡ የራሷ አካልና ንቅናቄም አላት፡፡ እንደ ሰው ትበላለች፣ ትጠጣለችም፡፡ ግብርና ውሎዋም እርኩስ ብቻ አይደለም፡፡ በጐ ምግባር ያላቸውና በጎ የሚሠሩ ‹‹ጂንኒዎች›› በብዛት አሉ፡፡ እርኩስ የሆኑና ክፋትን ብቻ በምድር ላይ የሚዘሩ ጂንኒዎችም ሞልተዋል፡፡

‹‹ጂንኒ›› ማሰብ ከሚችሉ ሦስት ፍጥረቶችም መካከልም አንዷ ናት (ቀሪዎቹ ሁለቱ መላእክትና የሰው ልጅ ናቸው)፡፡ የራሷ መንግሥትና ሀገርም አላት፡፡ የምትኖረው በምድር ላይ ብቻ ሳይሆን በባህርም ጭምር ነው፡፡ በተራራ፣ በጫካ፣ በዛፍ ስንጥቆች መሀል፣ በወንዝ፣ በኩሬ ወዘተ … መኖር ትችላለች፡፡

‹‹ጂንኒ›› እንደ ሰው በሁለት እግሯ ነው የምትራመደው፡፡ ነገር ግን የታችኛው ቅልጥሟ ከአህያ እግር ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የእግሯ ኮቴም ቢሆን ከከብትና ከአህያ ሸኮና ጋር ነው የሚመሳሰለው፡፡ ከዚህ ሌላ መላው የጂንኒ አካል ጸጉራም ነው፡፡ ከእግር እስከ ራሷ ድረስ በጸጉር ተሸፍናለች፡፡ ይህ ጸጉሯም ከቀበሮ ወይም ከውሻ ጸጉር ጋር ይመሳሰላል፡፡ መልኩ ግን እንደ አህያ ቆዳ ዳለቻ ነው፡፡ መላው አካሏም ዳለቻ መልክ ነው ያለው፡፡

ጂንኒ እንዲህ ሆና የምትታየው በተፈጥሮ አካሏ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ የተፈጥሮ ገላዋ ሁልጊዜ አትገኝም፡፡ አካልና ገላዋን እንደፈለገች መቀያየር ትችላለች፡፡ በአንድ ጊዜ ግዙፍ ሆና ከዛፍ ቁመት ጋር ልትስተካከል ይቻላታል፡፡ ብትፈልግ ላም፣ ካሻትም በሬ፣ ከፈቀደችም ድመት መሆን ትችላለች፡፡

  • አፈንዲ ሙተቂ ‹‹የወግ ሽርሽር – ከሐረር እስከ ሸገር›› (2006)

 * * *

ብሂሎች

  • ስለ ጥቁሮችና ነጮች እኩልነት በትክክል ለመናገር የሚችሉት እኩል የምናንቀሳቅሳቸውና የምናሠራቸው የፋብሪካ ሞተሮች ብቻ ናቸው፡፡ (እኩል የምናንቀሳቅሳቸው ሞተሮች የሚከፈለንን ከፍተኛ ደሞዝ ልዩነት አይተው የሚፈርዱ ቢሆኑ ኖሮ በእጅጉ ባዘኑ ነበር፡፡)
  • በሐቅ ለመኖር የምንፈልግ ከሆነ መታገል አለብን፡፡
  • እኛ ሽማግሌዎች የዛሬ ልጆች የሚሏቸው ነገሮች እኛ ስንወለድ እንዳልነበሩ መረዳት አለብን፡፡
  • ደም ከፈራህ ባለ ልኳንዳ አትሁን፡፡
  • የተነገሩት ቃላት እንደገና ተነገሩ፣ የተደመጡት ቃላት እንደገና ተደመጡና ተጠኑ፡፡
  • ‹‹ባሮች›› የሚባሉት በጉልበት ተገደውና ሰንሰለት ተከርችሞባቸው የተሸጡት ሳይሆኑ ባርነትን በአካልም በሞራልም የተቀበሉት ናቸው፡፡

ሴኔጋላዊው የሥነ ጽሑፍ ሰው ሴምቤኔ ዮስማኔ የተናገረው

  • ተሾመ ብርሃኑ ከማል ‹‹የዓለማችን ታላላቅ ሰዎችና ጥቅሶቻቸው›› (2007)

**************

በሰሜን ሸዋ በደረታቸው የተጣበቁ ሁለት ሕፃናት ተወለዱ

ሰሞኑን ከሰሜን ሸዋ  የተሰማው አንዲት እናት በደረታቸው አካባቢ የተጣበቁ ሁለት ሕፃናት መወለዳቸው ነው፡፡

ኤፍ.ቢ.ሲ ሞገድ አሳብሮ እንዳስደመጠው፣ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ መርሐ ቤቴ ወረዳ፣ ዓለም ከተማ፣ እናት ሆስፒታል ውስጥ ጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም. የተወለዱት ሕፃናት ፅንሶቹ ደረታቸው አካባቢ የተጣበቁ፣ የጋራ ልብና የየራሳቸው አንገትና ጭንቅላት ያላቸው ነገር ግን ከሆዳቸው በታች ያልተጣበቁ ናቸው።

ፅንሶቹ ለአራት ሰዓታት ያህል በህይወት ቆይተው ሕይወታቸው ቢያልፍም፥  እናት ግን በሙሉ ጤንነት ላይ ትገኛለች።

ይህ አይነት ክስተት ከ60 ሺህ ሰዎች ውስጥ በአንዷ ላይ ሊደርስ እንደሚችል ዜናው አውስቷል፡፡

**********

ከዶሮ ተረፈ ምርት ነዳጅን

ከዶሮ ተረፈ ምርት ነዳጅ ማምረት እንደሚቻል በሁለት ኢትዮጵያውያት ተማሪዎች የተደረገው ምርምርና ፈጠራ ይፋ ተደረገ፡፡

ኢዜአ እንደዘገበው፣ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ሥር በሚገኘው የመቐለ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ይፋ የተደረገው  የምርምር ፕሮጀክቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ ግኝት መሆኑም ተገልጿል።

ከዶሮ ተረፈ ምርት የተገኘው ነዳጅ ምርት ከዚህ ቀደም ለምግብ ከሚውለው ሰብልና ከከርሰ ምድር ከሚገኘው የተፈጥሮ ነዳጅ ጋር ሲነጻጸር የአካባቢ ብክለትን አያስከትልም ተብሏል፡፡ ከዚሁ ተረፈ ምርት ማዳበሪያና የእንሰሳት መኖን ማምረት እንደሚቻልም  ተገልጿል፡፡

ተመራማሪዎቹ  የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች  ኤዶምና  ታሪክ እንዳሉት ‹‹የፈጠራ ፕሮጀክቶቹን ተግባራዊ በማድረግ አገሪቱ እየደረሰባት ካለው ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ጫናና የአካባቢ ብክለት ለማላቀቅ ገንዘብ ካላቸው ባለሀብቶች ጋር በቅንጅት ለመሥራት ተዘጋጅተናል›› ብለዋል።

**********

ባልና ሚስቱ

ሚስት ባሏ ዘንድ ትደውላለች፡፡

– አንተ የማትረባ!  የትነው ያለኸው?

– ባል፦ ፒያሳ ነኝ!
– ሚስት፦ እዛ ምን ትሠራለሀ?!
– ባል፦ አንዴ ትዝ ካለሽ የሆነ ወርቅ ቤት አልጎበኘንም?
– ሚስት፦ አስታወስኩት ውዴ
– ባል፦ የወርቅ ሀብል አይተሽ ወደድኩት ስትይ ገንዘብ ሳገኝ
  እገዛልሻለሁ አላልኩም?
– ሚስት፦ አዎ የኔ ፍቅር
– ባል፦ ወርቅ ቤቱን አወቅሽው?
– ሚስት፦ አዎ ወለላዬ
– ባል፦ ከእሱ አጠገብ ያለው ግሮሰሪ ነኝ

********

ፍቅር በዘመነ ዲጂታል
ጎግዬ አስጎግዬ ያን ሰሞን ያጣኋት
አወይ አጋጣሚ CHAT ላይ አገኘኋት፤
ADD ያረኳትን ልጅ ዓምናና ካቻምና
አየኋት FACEBOOK ላይ ያቻትና ያቻትና፡፡
ONLINE አየናት ሲሉኝ ትላንትና
FACEBOOK LOGIN ብዬ አጣኋት ሄድኩና፤
አገኛት እንደሆን TWITTER ላይ ሄድኩኝ
ዓይኔ እንደናፈቃት ሳላያት አደርኩኝ፤
YOUTUBE ገብቼ SEARCH አድርጌ አጣኋት
TODAY እንደ ድንገት FACEBOOK ላይ አየኋት
ጎግዬ አስጎግዬ ዛሬ አግኝቻታለሁ
CHAT አድርጊው በሏት እኔ እሻላታለሁ፡፡

  • ‹‹የፍቅር ጣዕም›› (ከድረ ገጽ)

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...