ለማሚቶች (Cormorants) ትላልቅ ወፎች ሲሆኑ፣ የተያያዘ እግር እና መንጠቆ ዓይነት ምንቃር አላቸው፡፡ ምግባቸው ሙሉ ለሙሉ ዓሳ ነው፡፡ ወደ ውኃ ውስጥ ለመጥለቅ ዓሳዎችን ለመያዝ የሚያገለግላቸውነ እግራቸውንና ክንፋቸውን ይጠቀማሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ዓሳ የሚያጠምዱት ለመዝናናት ይመስላል፡፡ ከጠገቡም በኋላ እንኳን ማጥመዱን አያቋርጡም፡፡ ስለዚህም ሰዎች ታዳጊ ወፎችን ዓሳን እንዲያጠምዱ ያሠለጥኗቸዋል፡፡ ያጠመዱትን ዓሳ እንዳይውጡት (ለራሳቸው ጥቅም እንዳያውሉት) ግን በመጀመሪያ አንገታቸው ላይ ቀለበት ይደረግባቸዋል፡፡ ቀስ በቀስ ደግሞ ካልተፈቀደላቸው በስተቀር ቀለበቱም ባይኖር ዓሳውን እንደማይበሉት ሆነው ይሠለጥናሉ፡፡ በዚህ መሠረት ወፎቹ ዓሳውን ወደ ጀልባው የሚያስገቡ ሲሆን፣ ለዚህም ትብብራቸው ቁርጥራጭ (ለገበያ የማይቀርብ) አነስተኛ ዓሳ ይሰጣቸዋል፡፡
አንዳንዴ ብዙ ለማሚቶች በኅብረት በመሆን የተበታተኑ ዓሳዎችን በመክበብ በቀላሉ እንዲያዙ ያደርጋሉ፡፡ አሊያም ሁለት ወይም ከዛ በላይ ሆነው ተለቅ ያለውን ዓሳ በቀላሉ ይይዙታል፡፡ የሠለጠኑት ወፎች በጣም ከፍተኛ ጥቅም ሲኖራቸው አንዳንድ ለማሚቶች በአንድ ሰዓት ውስጥ አንድ መቶ የሚሆኑ ዓሳዎችን ሊይዙ ይችላሉ ተብሎ ይገመታል፡፡
- ማንይንገረው ሸንቁጥ፣ ባለአከርካሪዎች (2004 ዓ.ም.)