Monday, June 17, 2024

ያለዴሞክራሲ ምን ተይዞ ጉዞ?

ዴሞክራቶች በሌሉበት ስለዴሞክራሲ መነጋገር አዳጋች ነው፡፡ ዴሞክራሲ በሰረፀባቸው አገሮች ውስጥ ከግጭት ይልቅ ውይይት፣ ከመጠላለፍ ይልቅ ድርድር፣ ከሐሜትና ከአሉባልታ ይልቅ ክርክር ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትና የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ዋስትና የሚኖራቸው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በለመለመባቸው ሥፍራዎች ብቻ ነው፡፡ ብዙዎቹ የምዕራባውያን አገሮች ዴሞክራሲንና የሰብዓዊ መብት ጥበቃን የውጭ ፖሊሲያቸው ማዕከላዊ ነጥብ የሚያደርጉዋቸው፣ የሰው ልጆች ነፃነት ማረጋገጫ መሣሪያዎች በመሆናቸው ነው፡፡ ዴሞክራሲ የተለያዩ አመለካከቶችና ሐሳቦች በነፃ የሚንሸራሸሩበት ሥርዓት በመሆኑ የዘመናችን ተመራጭ የመንግሥት መመሥረቻ ፍቱን ዘዴ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሒደት የማይመራ አገር የጭቆናና የረገጣ ተምሳሌት ይሆናል፡፡ በዴሞክራሲ የሚመራ አገር ሰላማዊ፣ ጭቆናና አፈናን የማይቀበል፣ የዜጐችን መብት የሚያስከብር፣ የመደራጀት መብት የሚፈቅድ፣ ሰብዓዊ ቀውሶችንና ግጭቶችን የሚያስወግድና የአገርን ብሔራዊ ክብር የሚጠብቅ ነው፡፡ ዴሞክራሲ በዚህ መንገድ ተግባራዊ ሲደረግ የተረጋጋችና የበለፀገች አገር ትኖራለች፡፡ የዴሞክራሲ መርሆዎች ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ ዜጐች በነፃነት ይኖራሉ፡፡ በአገራችን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውጥኖች ከተጀመሩ ግማሽ ክፍለ ዘመን ቢያስቆጥሩም፣ አሁንም ሒደቱ እጅግ አስቸጋሪና ውጣ ውረድ የተሞላበት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ከዛሬ አርባ ዓመት በፊት በተቀጣጠለው የየካቲት 1966 ዓ.ም. አብዮት ሳቢያ በመላ አገሪቱ የደረሰው ሰቆቃ ዴሞክራሲን በአግባቡ ማካሄድ ካለመቻል የተነሳ ከመሆኑም በላይ፣ ከዚያ ዓይነቱ አሳዛኝ ክስተት መማር ባለመቻሉ ዛሬም መናቆሩና መጠላለፉ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ደም በፈሰሰባት አገር ውስጥ ሰላምና መረጋጋት አምጥቶ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ዛሬም ጋሬጣ አለ፡፡ ብሔራዊ ጉዳዮችን አማክሎ ልዩነትን አቻችሎ ከመሄድ ይልቅ አሁንም ጭቅጭቅና ጉሽሚያው በርትቷል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ስለመገንባት እየተነገረ ከዚያ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች ይስተዋላሉ፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ይፋጠጣሉ፡፡ በሕግ አግባብ መፈታት ያለባቸው ጉዳዮች ወደ ግጭትና ትርምስ ያመራሉ፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ንፋስ ገብቶ ልዩነት ሲከሰት ልዩነትን እንዴት አስታርቆ መሄድ ይቻላል ከማለት ይልቅ፣ ልዩነትን ጽንፍ በመውሰድ የማይታረቅ ቅራኔ ይፈጠራል፡፡ ከዚያም ሐሜት፣ አሽሙር፣ ስድብና አላስፈላጊ ድርጊቶች ይፈጸማሉ፡፡ ሰብዕና እየተዋረደ የፖለቲካው መንደር በነገር ይበለሻሻል፡፡ ፖለቲከኞች ገና ከመነሻው ዴሞክራትነት ቢሰርፅባቸው ኖሮ ይህ ሁሉ ችግር አይፈጠርም ነበር፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ልዩነት በዴሞክራሲያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ተቻችሎ መሄድ ይችላልና፡፡ ከዚህ ቀደም በተለይ በአፍሪካ ውስጥ ምርጫዎች ሲካሄዱ ከፍተኛ የሆኑ ፀረ ዴሞክራሲ ተግባሮች ይከናወኑ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የአፍሪካ አኅጉር የአምባገነኖች መናኸሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቁጥራቸው የማይናቅ የአፍሪካ አገሮች ከፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት እየፀዱ የአኅጉሪቱ ገጽታም እየተሻሻለ ነው፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እንዲሆን ለምን አይፈለግም? ፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት ብዙዎችን የአፍሪካ አገሮች የብጥብጥና የትርምስ ማዕከላት አድርጓቸው በመቆየታቸው አፍሪካ ብዙ ዕድሎች አምልጠዋታል ሲባል፣ እኛንም እንደሚመለከተን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ነው ከግለሰብ ፖለቲከኞች አንስቶ እስከተለያዩ ተቋማት ድረስ ለዴሞክራሲ መስረፅ ከፍተኛ ትግል መደረግ አለበት የሚባለው፡፡ ዘንድሮ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ወዲህ በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የሚታው እሰጥ አገባ ኢዴሞክራሲያዊ እየሆነ ነው፡፡ በፓርቲዎች መካከል ችግር ሲከሰት ተቀምጦ ከመነጋገር ይልቅ ሩቅ ለሩቅ ተሁኖ መገለማመጥ ተጀምሯል፡፡ በጠላትነት ዓይን እየተያዩ የመጠፋፋት ስሜት ነግሷል፡፡ ፓርቲዎች በውስጣቸው የሚነሱ ችግሮችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ አብረው ለትግል እንዳልተሠለፉ ሁሉ፣ በስድብ ውርጅብኝ ታጅበው እየተዘላለፉ አባላቶቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን አንገት እያስደፉ ናቸው፡፡ ‹‹ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር›› የሚባለው የዴሞክራሲያዊነት መገለጫ፣ እዚህ አገር ሲደርስ ለምን የጠብ መንስዔ ይሆናል? ሸምጋይና ገላጋይ ጠፍቶ የአንድ ፓርቲ አባላት በሚዲያ እንደዚያ ስም ሲጠፋፉ እስከ መቼ ዝም ይባላል? ጠብን ከማብረድ ይልቅ ድንጋይ የሚያቀብሉ በመብዛታቸው ነው የመፍትሔ ያለህ መባል ያለበት፡፡ እንደሚወቀው ልዩነትን በማስታረቅ ወይም በማጥበብ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ፣ ግጭት እንዲቀሰቀስ ማድረግ ከፖለቲካ ልሂቃን አይጠበቅም፡፡ ሕግን አክብሮ የሚንቀሳቀስ ማንም ፖለቲከኛ ሆነ ቡድን በዴሞክራሲያዊ አገባብ ችግሮችን ካልፈታ ስለዴሞክራሲ የመናገር የሞራል ልዕልና አይኖረውም፡፡ አንዱ የሌላውን መብት በኃይል ማፈን እንደማይችለው ሁሉ፣ ሌላውም ወገን ተቃራኒ የሚለውን መብት የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት የሚገድብ የፖለቲካ ፓርቲ ስለራሱ ዴሞክራትነት ልናገር ቢል መሳቂያ ይሆናል፡፡ በምርጫ ዋዜማ ላይ ተሁኖ ገና ከአሁኑ ንትርክ ውስጥ ሲገባ ምርጫው እንዴት ሆኖ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሊሆን ይችላል የሚለው ያስጨንቃል፡፡ የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ ተግባራዊ በሆነባቸው አገሮች ዜጐች በነፃነት የፈለጉትን የመምረጥ መብት ስላላቸው፣ ተመራጮች ለሕዝብ ያላቸው ከበሬታ ከምንም ነገር በላይ የላቀ ነው፡፡ ነገር ግን ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓትና ለሕግ የበላይነት ዋጋ በማይሰጥባቸው አገሮች ደግሞ ግጭቶች ይኖራሉ፡፡ ለአምባገነንነት በር ይከፈታል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ ራስ ወዳድ ፖለቲከኞች ሌሎችን ከፖለቲካ ምኅዳሩ ሲያገሉና አንዱን ወገን ሌላው ላይ ሲያነሳሱ ነው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት በጎደለው ሥርዓት ውስጥ ዴሞክራሲ ከማበብ ይልቅ እየጫጫ የሚሄደው፣ ፖለቲከኞች የዴሞክራሲን ንድፈ ሐሳብ እያጣመሙ በመተርጐም ወደማይሆን አቅጣጫ ስለሚገፉት ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ልዕልና ሲባል ፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት ይወገዙ፡፡ ለአገራችን ዴሞክራሲ ቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ከ90 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሚኖርባት በዚህች አገር ውስጥ በርካታ ፍላጐቶች አሉ፡፡ እነዚህን ፍላጎቶች አቻችሎና አማክሎ መሄድ የሚቻለው ዴሞክራሲን በሁሉም ሥፍራ ማስቀጠል ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ዴሞክራሲ የዜጎች በነፃነት የመምረጥ መብት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ነው፡፡ ዴሞክራሲ የመቃወም፣ የመደገፍ ወይም ድምፀ ተአቅቦ የማድረግ መብት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ዜጐች በእኩልነት የሚስተናገዱበት መብት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩበት ነው፡፡ ዴሞክራሲ የሕግ የበላይነት የሚሰፍንበት ነው፡፡ በእርግጥ ዴሞክራሲ በሒደት የሚያድግና የሚያብብ ቢሆንም፣ በሕዝብ የነቃና የጐላ ተሳትፎ ተግባራዊ የሚሆን ነው፡፡ ዴሞክራሲ የተጓደለበት ማኅበረሰብ አየር እንደተነፈገ ስለሚቆጠር፣ ያለዴሞክራሲ የትም መድረስ አይቻልም! ያለዴሞክራሲ ምን ተይዞ ጉዞ?

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...