Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየአዲስ አበባ አስተዳደር ላልተወሰነ ጊዜ ለኢንዱስትሪ ልማት መሬት ማቅረብ አቆመ

የአዲስ አበባ አስተዳደር ላልተወሰነ ጊዜ ለኢንዱስትሪ ልማት መሬት ማቅረብ አቆመ

ቀን:

በርካታ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ መሬት እንዲሰጣቸው እየጠየቁ ቢሆንም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጊዜው መሬት እንዳይቀርብ አገደ፡፡ አስተዳደሩ ዕግድ ያወጣው ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዘርፎች ለመለየት እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ በቀለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አስተዳደሩ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዘርፎች ለመለየት ቢሮው በባለቤትነት ጥናት ማካሄድ መጀመሩንና በቅርቡም ጥናቱን አጠናቆ ለአስተዳደሩ ካቢኔ አቅርቦ ካፀደቀ በኋላ መሬት መስጠት እንደሚጀመር አቶ ዮሐንስ አብራርተዋል፡፡ እስካሁን በኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ መሬት እንዲሰጣቸው ከትንንሽ እስከ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ድረስ ያሉ ባለሀብቶች እያመለከቱ መሆኑን አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡ እስከ በጀት ዓመቱ አጋማሽ ድረስ ከ600 በላይ የሚሆኑ ባለሀብቶች ከኢንዱስትሪ ቢሮ የድጋፍ ደብዳቤ ይዘው በመቅረብ፣ የከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ መሬት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ከቀረቡ በርካታ ጥያቄዎች ውስጥ 40 የሆኑት መሬት ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡ ባለሀብቶች የሚያቀርቧቸው ፕሮጀክቶች የመሬት ልማትና ማኔጀመንት ቢሮ ባለሙያዎች ጥያቄ እንዲያነሱ ማድረጉም ታውቋል፡፡ አስተዳደሩ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች በግልጽ ተለይተው ባለመቀመጣቸው የባለሀብቶቹን የመሬት ጥያቄ የሚያስተናግዱበት መንገድ ግራ የሚያጋባ ስለሆነባቸው ጥያቄ ማንሳታቸውን የአስተዳደሩ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በዚህ መሠረት አስተዳደሩ ላልተወሰነ ጊዜ ቦታ ማቅረብ እንዲቆም በማድረግ ጥናት እንዲካሄድ መወሰኑ ታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዓመታት ቆይታ በኋላ በዚህ ዓመት የኢንዱስትሪ ዞኖችን እያዘጋጀ ለአልሚዎች መሬት ማቅረብ ጀምሯል፡፡ የከተማውን ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲመራ ኃላፊነት የተሰጠው የከተማው ኢንዱስትሪ ቢሮ ነው፡፡ ይህ ቢሮ ከሁለት ወራት በፊት ከንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ተገንጥሎ የወጣ ሲሆን፣ ቢሮውን እንዲመሩ የተሾሙት ደግሞ የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ዮሐንስ በቀለ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በማስፋፊያ ቦታዎች አካባቢ 200 ሔክታር መሬት ለኢንዱስትሪ ልማት አዘጋጅቷል፡፡ የኢንዱስትሪ ዞኑ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት እንደሆነ የአስተዳደሩ ባለሥልጣናት ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ