Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

በ56 ዓመቷ ‹‹ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ›› ዱብ ያደረገችው ቤተ እስራኤላዊት በካፕላን የሕክምና ማዕከል

ትኩስ ፅሁፎች

የሕፃን ተአምር ለ56 ዓመቷ ቤተ እስራኤላዊት

ከ24 ዓመት በፊት የደርግ መንግሥት ለማክተም የቀናት ዕድሜ ሲቀረው እስራኤል ኢትዮጵያውያኑን ቤተ እስራኤላውያን ወደ አገሯ ለማጓጓዝ ዘመቻ ሰሎሞንን አካሂዳ ነበር፡፡ ያኔ ወደ አገሯ ከወሰደቻቸው ኢትዮጵያውያት መካከል ዘንድሮ 56ኛ ዓመት ዕድሜ ላይ የደረሰችው ታሚ ትገኝበታለች፡፡

ዘጠኝ ወንድሞች ያሏት ታሚ ጎጆ ብትወጣም ሦስት ጉልቻ ብትጎልትም ዓይኗን በዓይኗ ሳታይ ዓመታት ነጉደዋል፡፡ ልጅ የማግኘት ሕልሟም እውን አልሆነላትም፡፡ ከዓመታት ትግል በኋላ ግን ዘንድሮ በለስ ቀንቷታል፡፡ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ዱብ አርጋለች፡፡

የሳይንስና የባህል መዲና በሆነችው ርኆቦት ከተማ የሚገኘው ካፕላን የሕክምና ማዕከል ባለፈው ሰኞ እንዳስታወቀው ሴትዮይቱ በ56 ዓመቷ 3.61 ኪሎ የሚመዝን ጤናማ ሕፃን የወለደችው ለወር ያህል በሆስፒታሉ ተኝታ በተደረገላት ክትትል ነው፡፡

******

ዘ ጀሩሳሌም ፖስት በጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ዘገባው እንደገለጸው፣ ለሆስፒታሉ ሐኪሞችና ባልደረቦች ምስጋና ያቀረበችው ወላዲቷ ‹‹የዘመናት ጉጉቴ ይህን ስጦታ በእጆቼ ማቀፍ ችያለሁ›› ብላለች፡፡

አልመጣም

ምንም ያህል ብርሃን ቢሆን 

      መቅረዝ ባይለይም ከእጄ

የማይነጋ ቀን አለ

      ልምጣ ብል እንኳ ፈቅጄ

የማላቋርጠው በዋና

      የማልሻገረው በታንኳ

የማላልፈው ባህር አለ

      ምንም ብወድህ እንኳ

ዓይኖችህን ማየት ብናፍቅ

      አንተነትህ ከ’ኔ ርቆ

ላልችል አልሞክር ለማለፍ

ከፊቴ ያለውን ሸለቆ

በምኞት ፈረስ ስሰግር

      ልደርስብህ ስንጠራራ

መንገዴ ላይ ተጋረጠ

      ችዬ የማልወጣው ተራራ

የቱንም ያህል ብወድህ

      የኔ ላደርግህ ብሻ

ብገባ የማልወጣበት

      ይታየኛል ትልቅ ዋሻ

አትጠብቀኝ ውዴ!

ይቅር አትጠብቀኝ

      ችዬ አልመጣም እዚያ ማዶ

እግሬ ቢሄድ ወደ ሌላ

      ልቤ ይኑር አንተን ወ’ዶ፡፡

ሜሮን ጌትነት ‹‹ዙረት›› (2006)

******

ጀግናዋ ውርዬ ሕፃኑን ከሞት ታደገችው

ምስጋና በሩሲያ ለምትገኘውና ሚሻ በሚል ስያሜ ለምትታወቀው ድመት ይሁንና መሰንበቻውን በሩሪያዋ ኦብኒስክ ከተማ ከአንድ ሕንፃ ጥግ በረዷማ ቁር ላይ የተጣለ ሕፃንን ከሞት ታድጋዋለች፡፡ ውርዬ ወደ ማረፊያዋ ለመግባት ደረጃውን ስትወጣ ከ12 ሳምንታት እምብዛም የማያልፈውን ሕፃን በማየቷ ባሰማችው የተለየ ድምፅ የአካባቢው ነዋሪ ሰምተው በመድረሳቸው ወላጆቹ የጣሉት ሕፃን መትረፉን ሴንትራል ኢሮፒያን ኒውስ በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡ ሕፃኑ ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን፣ የመንደሩ ነዋሪዎችም ለጀግናዋ ውርዬ የምትወደውን ምግብ እንዳቀረቡላት ዘገባው አመልክቷል፡፡

*******

የማር እንጀራ

ንቦች የማር እንጀራ የሚሠሩት በሆዳቸው የታችኛው ክፍል የሚገኙ እጢዎች የሚያመነጩትን ሰም ተጠቅመው ነው። የማር እንጀራ እጅግ የተራቀቀ የምሕንድስና ጥበብ እንደሆነ ይነገራል። ለምን?

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ አንድን ቦታ ስድስት ጎን ባለው ቅርጽ መከፋፈል በሦስት ማዕዘን፣ በካሬ ወይም በሌላ በማንኛውም ቅርጽ ከመከፋፈል በተሻለ በአነስተኛ የግንባታ ዕቃ ብዙ መያዝ የሚችል ክፍልፋይ ለመሥራት ያስችላል። የሒሳብ ሊቃውንት ይህን የተገነዘቡት ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ቢሆንም ይህ የሆነበትን ምክንያት ግን ሙሉ በሙሉ አልተረዱም ነበር። 1999 ፕሮፌሰር ቶማስ ሄልስ፣ የማር እንጀራ ቅርጽ ያለውን ብልጫ የሚያሳይ የሒሳብ ማስረጃ አቀረቡ፤ ይህንን ማስረጃየማር እንጀራ መላምትብለው ጠርተውታል። አንድን ቦታ ብዙ ጠንካራ ድጋፍ ሳያስፈልግ እኩል ቦታ ለመከፋፈል ከሁሉ የተሻለው መንገድ ባለስድስት እኩል ጎን ያለው ቅርጽ መጠቀም እንደሆነ ፕሮፌሰሩ አስረድተዋል።

ንቦች፣ ያላቸውን ቦታ ያለምንም ብክነት ለመጠቀም ቦታውን ባለስድስት ጎን በሆኑ ቅርጾች ይከፋፍሉታል፤ ይህም ጠንካራ ሆኖም ብዙ ክብደት የሌለው እንዲሁም በአነስተኛ ሰም ብዙ ማር የመያዝ አቅም ያለው የማር እንጀራ ለመሥራት ያስችላቸዋል። የማር እንጀራአስደናቂ ጥበብ የሚታይበት የግንባታ ንድፍመባሉ ምንም አያስደንቅም።

በዛሬው ጊዜ የሳይንስ ሊቃውንት የንቦችን የማር እንጀራ በመኮረጅ ጠንካራና አንድን ቦታ በተሻለ መንገድ ለመጠቀም የሚያስችሉ ንድፎችን መሥራት ችለዋል። ለምሳሌ፣ የአውሮፕላን መሐንዲሶች የማር እንጀራን ንድፍ በመኮረጅ የተሠሩ ሰሌዳዎችን በመጠቀም ነዳጅ ቆጣቢ የሆኑ ጠንካራና ቀላል አውሮፕላኖችን ይሠራሉ።

  • ንቁ! (ጥር 2015)

******

የደግነት ጋሻ

ሦስት ወንድ ልጆች የነበሩት አንድ ሰው ነበር፡፡ ልጆቹንም በጥሩ ሁኔታ በመንከባከብ መልካም ባህሪይ ይዘው እንዲያድጉ አደረገ፡፡ በዚያን ጊዜ መልካም አዛውንት ሰዎች አሟሟታቸውን መተንበይ ይችሉ ነበርና ይህም አባት የመሞቻው ቀን እየተቃረበ መምጣቱን ባወቀ ጊዜ ሦስቱን ልጆች ጠርቶ ሃብቱን በማካፈል ከብቶቹን፣ መሬቱንና የእንሰት ተክሎቹን ከፋፍሎ ካወረሳቸው በኋላ መርቆ ሸኛቸው፡፡ ለራሱ ያስቀረው ነገር ጋሻውን ብቻ ነበር፡፡

በሲዳማ ባህል ጋሻ በጣም ልዩ ንብረት ነው፡፡ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የቤተሰብ ውርስ ነው፡፡ ነገር ግን ለታላቅ ልጅ ሳይሆን አባትየው ከልጆቹ መሃል ታላቅ ሰው ይሆናል ብሎ ለሚያስበው ሰው ይሰጥ ነበር፡፡ ይህ ሰው ግን ጋሻውን ለየትኛውም ልጅ አልሰጠም፡፡

አባትየውምልጆቼ ሆይ! ደግነት በባህላችን ትልቅ ዋጋ አለውና እናንተም አሁን ሄዳችሁ መልካምና ደግ ሥራ ሠርታችሁ እንድትመጡ እፈልጋለሁ፡፡ ከዚያም ወደዚህ ተመልሳችሁ የሠራችሁትን መልካም ነገር ትነግሩኛላችሁ፡፡ ከእናንተ ውስጥ የበለጠውን ደግነት ላደረገው ልጄ ይህንን የውርስ ጋሻ እሸልመዋለሁ፡፡አላቸው፡፡

ልጆቹም ሁሉ ጋሻውን ይፈልጉት ነበርና መልካሙን ነገር ለማድረግ በየፊናቸው ሄዱ፡፡ ከሄዱበትም ሲመለሱ አንደኛውአባቴ ሆይ! አንድ በጣም ደግ ነገር አድርጌያለሁ፡፡ እንግዲህ አንተ ፍረድ፡፡ አንድ በዳዴ የሚሄድ የነበረ ህጻን ከአንዲት ወንዝ ውስጥ ወድቆ እናቱ በፍርሃትና በድንጋጤ ቆማ ስታየው እኔ ለህይወቴ ሳልሳሳ ወንዙ ውስጥ ዘልዬ ገብቼ ህጻኑን አዳንኩት፡፡አለ፡፡

አባትየውምይህ ደግነት አይባልም፡፡ ይህ ሰው በመሆንህ ብቻ የምታደርገው ሰብአዊነት ነው፡፡ ህጻንንም ማዳን ያው ነው፡፡ ይህን ማንም ሊያደርገው ይችላል፡፡አለ፡፡

ሁለተኛውም ልጅአባቴ ሆይ! አንድ ብቸኛ መንገደኛ በመንገዱ ላይ ሳለእባክህ ገንዘቤን ጠብቅልኝብሎ 100 ከብር የተሠሩ የገንዘብ ቅጠሎችን ሰጥቶኝ ሄደ፡፡ ያንን ሁሉ ገንዘብ መስረቅ ስችል ጠብቄለት ሲመለስ 100 ብሩን ሰጥቸዋለሁ፡፡ እርሱም 10 የብር ቅጠሎችን ሊሰጠኝ ቢፈልግምአይሆንም፣ ይህ ያንተ ገንዘብ ነው፡፡ እኔ ጠበኩልህ እንጂ ምንም ስላላደረኩልህ ምንም አይነት ሽልማት አልቀበልህም፡፡አልኩት፡፡ይህ ደግነት አይደለም?” አለው፡፡

አዛውንቱም አባትአይደለም ልጄ! ይህ የሚያሳየው አንተ የገንዘብ ፍቅር እንደሌለህ ነው፡፡ ይህ በርግጥ ጥሩ ባህሪይ ነው፡፡ ነገር ግን ደግነት አይደለም፡፡አለው፡፡

ካያም የተባለው ሦስተኛው ልጁእሺ፣ እኔ ደግሞ ያደረኩትን ልንገራችሁ፡፡ በመንገድ ላይ እየሄድኩ ሳለ በድንገት ቀንደኛ ጠላታችንና ለዘመናት ስንጣላው የነበረውን ሰው በድንገት አገኘሁት፡፡ ከገደል አፋፍ ላይ ተኝቶ ነበርና ሄጄ ገፍትሬ ገደሉ ውስጥ ልጥለው ስችል ወይም ሄጄ ስቀሰቅሰው ቀና ብሎ ሲያየኝ ከቤተሰቤ ጋር ለረጅም ጊዜ ሲናቆር መኖሩን ስለሚያውቅ ለመዞር ሲገላበጥ ገደሉ ውስጥ ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ቀስ ብዬ ቀስቅሼው ወደ ደልዳላ ቦታ በመውሰድ ያለ ሥጋት እንዲተኛ ካደረኩት በኋላ ትቼው ሄጃለሁ፡፡አለ፡፡

አባትየውምአዎ፣ ልጄ ይህ ነው እውነተኛ ደግነት፡፡ እርሱ ያንተ ጠላት ብቻ ሳይሆን የቤተሰቡ በሙሉ ጠላት ነው፡፡ ነገር ግን አንተ ሕይወቱን አድነኸዋልና ጋሻውን የምሰጠው ላንተ ነው፡፡አለው፡፡

የታሪኩም መልዕክትጠላቶችህን በበቀል አትፈልጋቸው፡፡የሚል ነው፡፡

  • በአበበ ከበደ የተተረከ የሲዳማ ተረት (ከኢትዮጵያ ተረቶች ገጽ)

 

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች