Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምየኦሽዊትዝ በር የተዘጋበት 70ኛ ዓመት

የኦሽዊትዝ በር የተዘጋበት 70ኛ ዓመት

ቀን:

‹‹የኦሽዊትዝን የሞት እስረኞች ካምፕ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሴቶች ጋር እንደተቀላቀልኩ ልብሳችንን እንድናወልቅ ትዕዛዝ ተሰጠን፡፡ በኋላም ብዙዎቻችን መታጠቢያ ክፍል ነው ብለን ወደገመትነውና በጣም ወደሚቀዘቅዘው ክፍል እንድንገባ ተደረግን፡፡ ቀዝቃዛው የድንጋይ ወለል፣ በጣራው ላይ የነበሩ አንዳንድ ክፍት ቦታዎች ዛሬም ከፊቴ አልጠፉም፡፡ ውስጥ ሆነን ብንጠብቅ አዲስ ነገር አላየንም፡፡ አንድ የማውቃት ሴት ያላችሁበትን እስካሁን አታውቁም እንዴ? በጋዝ አፍነው የሚገድሉበት ክፍል ውስጥ ነው ያለነው አለችን፡፡›› የናዚ ፓርቲ እ.ኤ.አ. በ1933 የጀርመን መንግሥትን ሥልጣን እንደተቆጣጠረ በምድረ ጀርመንና በወቅቱ በጀርመን ቅኝ ግዛት ሥር በነበሩ አገሮች የዘራው ጥላቻና ዘረኝነት በተለይ የአይሁዶችን ዘር የማጥፋት ፕሮፓጋንዳ በሚሊዮን ለሚቆጠሩና በሰው ታሪክ ዘግናኝ ለተባለው አሰቃቂ ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ የጥፋት ድርጊት ካከተመ ደግሞ 70 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በጀርመን ቅኝ ሥር በነበረችው ፖላንድ የሚገኙት ሦስት የኦሽዊትዝ የሞት ካምፖች በር ከተዘጉም 70 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዛሬ 91 ዓመታቸውን ያከበሩትና በወቅቱ ከተለያዩ አገሮች የመጡ እስረኞች በጋዝ ታፍነው ይገደሉበት የነበረው ክፍል የቴክኒክ ብልሽት ገጥሞት ከሞት የተረፉት ጌና ቱርጄል፣ እ.ኤ.አ. በ1940 ተከፍቶ በ1945 በሶቭየት ኅብረት የነፃነት ታጋዮች አሸናፊነት በሩ ከተዘጋው የኦሽዊትዝ ካምፕ በሕይወት ከተረፉ 200,000 እስረኞች አንዷ ነበሩ፡፡ በጋዝ አፍኖ መግደያው ተርፈው በእስር ቤቱ የነበረውን ሥቃይና መከራ አሳልፈው ታሪክ ለመንገር የበቁት ቱርጄል፣ በካምፑ ቢታሰሩም የጅምላ ግድያ ይኖራል ብለው እንዳልጠረጠሩ ይናገራሉ፡፡ የጅምላ ጭፍጨፋው ግን የብዙዎችን ቤት አፍርሷል፡፡ ወላጅን ከልጆች ለይቷል፡፡ በተለይ በአይሁዶች ዘንድ የታሪክ ጠባሳ ጥሎ አልፋል፡፡ ናዚ ጀርመኖች በአይሁዶች ላይ ያደረሱት በደል ግን ሀብትና ንብረት ከመገበር፣ ወይም ግዛት ከመካፈል ጋር የተያያዘ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ከዘር ጥላቻ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ፣ ‹‹ንፁህ የጀርመናዊ ዘር›› ከሚል አመለካከት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ በጀርመን የሚኖሩ አይሁዶችን ከሥራ በማገድ፣ ከጀርመናውያን ጋር ትዳር እንዳይመሠርቱ በማድረግ፣ በአይሁዶች የተያዙ ንግዶችን ባለመጠቀም የተጀመረው ማግለል አይሎ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አይሁዳውያን ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ የጀርመን ናዚ መንግሥት በዘር ጥላቻ ተነስቶ በዘር ሐረጋቸው በሙሉ ጀርመናዊ ያልሆኑትን ከሥራ ባገደበት፣ ባገለለበት፣ በጨፈጨፈበት እንዲሁም በኦሽዊትዝ ካምፖች አስገብቶ የሰው ዘርን እንደ ቤተ ሙከራ በተጠቀመበትና በጋዝ አፍኖ በገደለበት ወቅት ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ለማወቅ ባይቻልም፣ የአሜሪካ ‹‹ሆሎከስት ሚሞሪያል ሙዚየም›› መረጃ በካምፖቹ ከታሰሩ 1.3 ሚሊዮን አይሁዳውያን 960,000 ተገድለዋል፡፡ 74,000 ፖላንዳውያን፣ 21,000 ሮማውያን፣ 15,000 የሶቭየት ኅብረት፣ 10,000 የተለያዩ አገሮች ዜግነት ያላቸው ከሕፃን እስከ አዋቂ በኦሽዊትዝ የሞት ሰለባ ሆነዋል፡፡ በታሪክ ተመዝግቦ የሚታየውም ዓለም በእስር ቤት ካምፖች ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ሞት ያስመዘገበው የወቅቱ ናዚ ጀርመን በኦሽዊትዝ ካምፖች ውስጥ በፈጸመው የጥላቻ ጅምላ ጭፍጨፋ ብቻ ነው፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የሶቪየት ኅብረት ጦር በጀርመን ላይ በተቀዳጀው ድል የኦሽዊትዝ የሞት ካምፖችን ነፃ ሲያወጣ፣ በውስጡ 7,000 በረሃብ የጠወለጉ ሰዎችን በሕይወት አግኝቷል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የወንድ፣ የሴትና የሕፃናት ልብሶች፣ 6,350 ኪሎ ግራም የሚመዝን የሰው ፀጉር ተገኝቷል፡፡ ያለፈውን ታሪክ ለማስታወስ፣ መቻቻልና ይቅርታን ለማንገሥና ጥላቻን ለማውገዝ፣ በኦሽዊትዝ ሙዚየም ውስጥ ከ100,000 በላይ ጥንድ ጫማዎች፣ 12,000 የማብሰያ ቁሳቁሶች፣ 3,800 ሳምሶናይት ቦርሳዎች ይገኛሉ፡፡ በምድራዊ ሲኦል በሚመሰሉት የኦሽዊትዝ የሞት ካምፖች እስረኞች አንድ ላይ በጋዝ ታፍነው ከመገደል ባለፈም የቁም ስቃይ አይተዋል፡፡ ማኮላሸት፣ ዘግናኝ የተባሉ የሕክምና ሙከራዎችን በአይሁዶችና በሮማ እስረኞች ላይ ማካሄድ፣ በተላላፊ በሽታዎች ምን ያህል እንደሚጠቁ ለማወቅና ለመመራመር ሙከራ ማድረግ የጀርመን የሕክምና ባለሙያዎች ይፈጽሙት የነበረው ወንጀል ነው፡፡ የኦሽዊትዝ የሞት ካምፖች ውስጥ በእስረኞች ላይ ግፍና በደሉን የፈጸሙት 7,000 ያህል የናዚ ሠራተኞች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ሆኖም ከእነዚህ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ብቻ ለፍርድ ቀርበዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 ብቻ 30 የኦሽዊትዝ የሞት ካምፕ ሠራተኞች ተለይተው የታወቁ ሲሆን፣ ለፍርድ እንደሚቀርቡም የጀርመን መንግሥት አሳውቆ ነበር፡፡ የኦሽዊትዝ እስረኞች ነፃ የወጡበት 70ኛ ዓመት ሰሞኑን ሲከበር፣ ከሞት ካመለጡት ብዙዎቹ በዕድሜ ምክንያት መሞታቸው ተወስቷል፡፡ ያሳለፉት መከራና ስቃይም እየተረሳ ነው፡፡ ዛሬ አዲስ ትውልድ ተተክቷል፡፡ ታሪኩን ካልሆነ በስተቀር ድርጊቱን በአካል የሚያስታውሰው እየጠፋ ነው፡፡ ሆኖም አይሁዶችን ዒላማ ያደረገው የፈረንሳዩ የሰሞኑ ጥቃት በዘር ላይ ያነጣጠረውን ጭፍጨፋ ዳግም እንዳያጭር ሥጋት እንዳላቸው፣ የዓለም አይሁድ ኮንግረስ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ላውደር ይናገራሉ፡፡ በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥላቻ እየሰፋ መምጣቱንም ይገልጻሉ፡፡ ‹‹የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ባከተመ ማግሥት በኦሽዊትዝና በሌሎች የእስረኞች ካምፖች ውስጥ ናዚዎች ከፈጸሙት ድርጊት ጋር ማንኛውም ጤናማ ሰው ራሱን ማቆራኘት አይፈልግም፡፡ የሆሎከስት ጊዜው እየራቀ፣ ከሞት የተረፉትም ሆነ ድርጊቱን የፈጸሙት የናዚ ተከታዮች እያለቁ ቢሆንም፣ አይሁዶች በዓለም ሰላም አደፍራሾች ናቸው የሚለው የአክራሪዎች አመለካከት እያገረሸ መጥቷል፤›› ሲሉ ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ኢቫ ኡምሉዋፍ ከኦሽዊትዝ ሞት ካምፕ የተረፉና በሙኒክ የሚኖሩ አዛውንት ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ከ70 ዓመታት በፊት የተፈጸመውን የማስታወስ ልማድ ቀስ በቀስ እየጠፋና እየተቀየረ ነው፡፡ ከወቅቱ አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተረፉ ሰዎች የመኖር ዘመን እያበቃ ነው፡፡ በቅርቡም ያከትማል፡፡ አሁን ያለው ወጣት ትውልድ ነው፡፡ ስለሆሎከስት ያለው አመለካከት ምናባዊ ነው፡፡ በወቅቱ ከነበሩ ናዚ ጀርመናውያን የተወለዱ የልጅ ልጆች ከኦሽዊትዝ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም፣ ሲሉ አሁን ያለው ትውልድ ስለታሪኩ እንዲያውቅና ይቅር መባባልን አጠንክሮ እንዲሄድ ይመክራሉ፡፡ በጀርመን የናዚው ዘመን አልፎ በአዲስ ትውልድ ቢተካም፣ የጥላቻና የዘረኝነት አመለካከት ዛሬም ይንፀባረቃል፡፡ ከኦሽዊትዝ የሞት ካምፕ የተረፉም ሆኑ ጀርመናውያን ራሳቸው በወቅቱ የነበረውን ጭፍጨፋ አውግዘው፣ ለታሪክ ትተውና በይቅርታ አልፈው ሰላማዊ ኑሮን ለመምራት ቢጥሩም፣ ከየአቅጣጫው ብቅ ብቅ የሚሉ የዘር ጥላቻዎች ዛሬም ምድረ ጀርመንን ይፈትኗታል፡፡ በጀርመን ለስደተኞች መኖሪያ ፈቃድ ማግኘትም ከባድ ነው፡፡ ከስደተኛ ውጪ ለሥራ የሚሄዱ የማንኛውም አገር ዜጐች ቢሆኑም ደረጃው ይለያያል እንጂ የሚገለሉበት አጋጣሚ ቀላል አይደለም፡፡ ይህ አመለካከት መሰበር እንዳለበት አጥብቀው የሚናገሩት የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከል ናቸው፡፡ የኦሽዊትዝ የሞት ካምፕ የተዘጋበትና እስረኞች ነፃ የሆኑበትን 70ኛ ዓመት አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት መርከል፣ ጀርመናውያን አለመቻቻልን የማውገዝ ኃላፊነት እንዳለባቸውና ሆሎከስት ጥሎት ያለፈው ፀፀትና ኃፍረት ከ70 ዓመታት በኋላም ጠንካራ ሆኖ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡ ጀርመናውያን በቅርቡ ‹‹ስደተኞች ከአገራችን ይውጡ›› ብለው ያደረጉትን ሰላማዊ ሠልፍም አውግዘዋል፡፡ ‹‹በጀርመን አዲስ ሕይወት የጀመሩም ሆኑ በጦርነትና በሌሎች ችግሮች ሳቢያ በጀርመን ለመኖር ጥያቄ ያቀረቡትን ጥላቻ በተሞላባቸው መፈክሮች እንዲንቋሸሹ አንፈልግም፤›› ሲሉ ጀርመናውያን ዳግም እያንፀባረቁ ካሉት የዘር ጥላቻ እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...