የኢትዮጵያን ክርስቲያናዊ ቅርሶች የሚያሳይ ዐውደ ርዕይ ማሳቹሴትስ በሚገኘው ሙዚየም ኦፍ ራሽያን አይከንስ በመታየት ላይ ነው፡፡ በዐውደ ርዕዩ ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንስቶ የነበሩ 60 ቅርሶች ተካተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ቀሳውስት የሚያደርጓቸው መስቀሎች፣ አነስተኛና ግዙፍ ሃይማኖታዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች ይገኙበታል፡፡ ቅርሶቹ የአንድ አውሮፓዊ ንብረት ሲሆኑ፣ ኪውሬተሩ ዶ/ር ማርክ ሎርክ ይባላል፡፡ ሙዚየሙ በተጨማሪ በድንጋይ ጥርብ ላይ የሚገኙ ሥዕሎችን የሚያሳይ ሲሆን፣ ለአራት ወራት ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆን የሙዝየሙ ድረ ገጽ አስታውቋል፡፡ ሥዕሎቹ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውና በቤተክርስቲያን ግድግዳና በመጽሐፍ ቅዱስ ሽፋን የሚገኙ ናቸው፡፡ በደማቅ ቀለማትና ለየት ያለ የፊት ቅርፅ አሣሣል የሚታወቀው የኢትዮጵያ ባህላዊ አሣሣል ከቀደምት የባዘንታይን ክርስቲያን አርት ጋር ትስስር አለው፡፡