Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቱርክ ኩባንያ በአዲስ አበባ 300 ሺሕ ቤቶች ለመገንባት ጥያቄ አቀረበ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግዙፉ የቱርክ ኩባንያ ፌርማኖግሉ አዲስ አበባ ውስጥ 300 ሺሕ ቤቶች ለመገንባት ጥያቄ አቀረበ፡፡ ኩባንያው እገነባለሁ ያለው የመኖሪያ ቤቶች ቁጥር አዲስ አበባ ከተማ ከአሥር ዓመት በፊት በአጠቃላይ ካሉዋት መኖሪያ ቤቶችና ንግድ ቤቶች መጠን ጋር እንደሚጠጋጋ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በ1996 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ ባካሄደው ጥናት በአዲስ አበባ 328 ሺሕ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች እንዳሉ ገልጾ ነበር፡፡ ፌርማኖግሉ መንግሥት ፕሮጀክቱን እንዲቀበለው ጥያቄውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቅርቧል፡፡ በቱርክ ፕሬዚዳንት የሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን እየተመራ ባለፈው ረቡዕ ምሽት አዲስ አበባ ከገባው የልዑካን ቡድን ውስጥ የዚህ ኩባንያ ባለቤት ተካተዋል፡፡ የዚህ ግዙፍ ኩባንያ ባለቤትና ፕሬዚዳንት ካዚም ፌርማኖግሉ በፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኩባንያው አዲስ አበባ ውስጥ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱን ከፍቷል፡፡ የሚገነባቸውን የመኖሪያ ሕንፃዎች ዲዛይን በመሥራትም ከኮንስትራክሽን ጋር ግንኙነት ላላቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት በማቅረብ የፕሮጀክቱን ጠቀሜታ በማስረዳት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ አዲስ አበባ የሚገኘው የኩባንያው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ፕሮጀክቱን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጥ ከሪፖርተር ጥያቄ ቢቀርብለትም፣ ከመንግሥት ጋር እየተካሄደ ያለው ውይይት ሳይጠናቀቅ መረጃ እንደማይሰጥ ገልጿል፡፡ ነገር ግን ሪፖርተር ባገኘው መረጃ ኩባንያው 45 ወለል ያላቸው መንትያ ሕንፃዎችን ጨምሮ አራት ወለልና ሰባት ወለል ያላቸው የመኖሪያ መንደሮችን ለመገንባት አቅዷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በፕሮጀክቱ ውስጥ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ የገበያ ሥፍራ፣ አረንጓዴና ክፍት ቦታዎች፣ ቴአትር ቤት፣ ሲኒማ ቤትና የመዋኛ ገንዳ ተካቷል፡፡ ኩባንያው እገነባለሁ ብሎ ያቀደው ትምህርት ቤት 20 ሺሕ ተማሪዎችን የመያዝ አቅም ይኖረዋል ተብሏል፡፡ ሆስፒታሉ ደግሞ 2,000 ሕሙማን በአንድ ጊዜ የሚስተናገዱበት የመኝታ ክፍሎች እንደሚኖሩት ተገልጿል፡፡ ኩባንያው ያቀረበው ፕሮጀክት ሰፊ መሬት የሚፈልግ ቢሆንም ለጊዜው መጠኑ ባለመታወቁ፣ መንግሥት ፕሮጀክቱን ከተቀበለው በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የኩባንያውን ቴክኒካል ብቃትና የፋይናንስ ሁኔታ መርምሮ ለአዲስ አበባ አስተዳደር የድጋፍ ደብዳቤ ይጽፋል ተብሏል፡፡ ይህ ኢንስቲትዩት እስካሁን አምስት የውጭ አገር ኩባንያዎች በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤቶች (ሪል ስቴት) ለመገንባት ያቀረቡትን ጥያቄ ከገመገመ በኋላ ድጋፉን ሰጥቷል፡፡ አብዛኛዎቹ ኩባንያዎች ራሱን የቻለ አንድ የከተማ ክፍል የመገንባት ዕቅድ ያላቸው በመሆናቸው፣ ከፍተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍልና የውጭ አገር ማኅበረሰብ ላይ ያነጣጠሩ ናቸው፡፡ የቱርኩ ኩባንያ ፌርማኖግሉ ባለፉት 68 ዓመታት በርካታ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ማከናወኑን ከድረ ገጹ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ ኩባንያው ታናሎች፣ ድልድዮች፣ መንገዶችና የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ማካሄዱም ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች