Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በመሬት ሊዝ ጨረታ የዋጋ ንረት እየታየ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የከተማውን የመሬት ዋጋ ለማረጋጋት በማለት በ12ኛው ሊዝ ጨረታ ከሌላው ጊዜ በአንፃሩ በርካታ ቦታዎችን ለጨረታ ቢያቀርብም፣ በካሬ ሜትር የቀረቡት ዋጋዎች አሁንም ንረት እየታየባቸው ነው፡፡ የከተማው አስተዳዳር ባለፈው ሳምንት የመጨረሻዎቹ ሦስት ቀናት ጨረታውን በከፈተበት ወቅት ለማየት እንደተቻለው፣ ዝቅተኛ የመጫረቻ ዋጋ ይቀርብላቸው የነበሩ ቦታዎች ከፍተኛ ገንዘብ ቀርቦላቸዋል፡፡ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ስድስት ቦታዎች ለጨረታ ቀርበው ሁለቱ ተጫራጮች ባለማግኘታቸው ሲሰረዙ፣ ከሦስቱ ቦታዎች ውስጥ አንዱ 13,000 ብር ሲቀርብለት፣ ሁለቱ ቦታዎች እያንዳንዳቸው 7,500 እና 7,500 ብር በካሬ ሜትር ቀርቦላቸዋል፡፡ በዚህ አካባቢ በተለይ ኮልፌ አጠና ተራ ቀለበት መንገድ አካባቢ ለጨረታ የቀረበው 2,120 ካሬ ሜትር ቦታ የዚህ ዙርን ከፍተኛ የመጫረቻ ዋጋ አግኝቷል፡፡ ለዚህ ቦታ ዘመናዊ አልባሳት ኩባንያ በካሬ ሜትር 65,000 ብር አቅርቧል፡፡ ሁለተኛ የወጣው ዲኤምኤ ኩባንያ ደግሞ 46,680 ብር በካሬ ሜትር አቅርቧል፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ አፓርታማ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቀደም ሲል ከ800 ብር እስከ አንድ ሺሕ ብር ይቀርብባቸው የነበሩ ቦታዎች፣ በዚህ ዙር ለአካባቢው ዝቅተኛ ሆኖ የቀረበው አቶ ሙሉጌታ አብርሃ የተባሉ ባለሀብት በካሬ ሜትር 3,429 ብር አቅርበው አሸናፊ መሆናቸው ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ለጨረታ ለቀረቡት ቦታዎች በካሬ ሜትር ከ15 ሺሕ ብር በላይ ቀርቦላቸዋል፡፡ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ለጨረታ ለቀረበ 327 ካሬ ሜትር ቦታ መስከረም ለማ የተባሉ ባለሀብት በካሬ ሜተር 22,222 ብር አቅርበዋል፡፡ ሁለተኛ የወጡት ሰናይት ገብሩ ደግሞ 17,321 ብር አቅርበዋል፡፡ ይህም የአካባቢው ከፍተኛ ዋጋ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በዚህ 12ኛ ዙር ጨረታ በቦሌ ክፍለ ከተማ ስድስት፣ በአቃቂ ቃሊቲ 15፣ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ስድስት፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ስድስት፣ በየካ ክፍለ ከተማ ስምንት ቦታዎች ለጨረታ ቀርበዋል፡፡ ለእነዚህ ቦታዎች ከ10,000 በላይ ተጫራቾች የቀረቡ ሲሆን፣ ባለሙያዎች እንደሚሉት አሁንም በብዛትና በተከታታይ መሬት ለጨረታ ካልቀረበ የዋጋ ንረቱ ተባብሶ ይቀጥላል፡፡ በዚህ ጨረታ የቀረቡ ቦታዎች ለመኖሪያ፣ ለቅይጥና ለቢዝነስ የሚውሉ ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ ቦታዎች ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ የቀረቡ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች