Wednesday, June 19, 2024

ትኩረት ለብሔራዊ መግባባት!

ለአንድ አገር ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሰላም ነው፡፡ ሰላም የሚኖረው ደግሞ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ ድርድርና መግባባት ሲኖር ነው፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዘርፍ መስኮች ዜጎች በብሔራዊ ጉዳይ መግባባት ይኖርባቸዋል፡፡ መግባባት በሌለበት ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት ይኖራሉ ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡ ለዚህም ነው ለአገር ህልውና ሲባል ብሔራዊ መግባባት ትኩረት ያስፈልገዋል የሚባለው፡፡ በአገራችን በተለይ ሕዝብን እንወክላለን በሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚታየው ቅራኔ ለብሔራዊ መግባባት እንቅፋት እየሆነ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ እንዲሁም ተቃዋሚ ፓርቲዎች እርስ በርሳቸው በሚፈጥሯቸው አለመግባባቶች ቅራኔዎች ሲጦዙ ይታያሉ፡፡ ችግሮችን በሰከነ መንገድ ተነጋግሮ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ፣ ኢዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መጠላለፍ በስፋት ይታያል፡፡ የቅራኔው ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ በአገር ጠላትነት በመፈራረጅ ለመነጋገር የማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሥልጣን በምርጫ ለመያዝ መፎካከር ያለባቸው ፓርቲዎች ሁሌም ለጠብ ሲጋበዙ ነው የሚታዩት፡፡ ይህ አሳሳቢ ችግር አንድ ቦታ ላይ ሊቆም ይገባዋል፡፡ ሁሉም ፓርቲዎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት እንታገላለን ሲሉ ሰላማዊውንና ዴሞክራሲያዊውን መንገድ ብቻ መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ ከዴሞክራሲያዊ ጎዳና በማፈንገጥ ለፀብና ለብጥብጥ ክፍተት መፍጠር ሕገወጥነት መሆኑን ሊረዱት ይገባል፡፡ ዴሞክራሲ ሁሌም መሠረት የሚያደርገው ሁሉም ሰው እኩል መብት እንዳለውና አገርም የምትተዳደረው በሕዝብ ድምፅ በሚገኝ ሥልጣን ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ ሁነኛ መሣሪያው ምርጫ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ደግሞ የአንድ አገር ሕዝብ በመንግሥት ውሳኔ ሰጪነት በተወካዮች አማካይነት ለመሳተፍ የሚያስችል የዘመናችን ተመራጭ ዘዴ ነው፡፡ ፖለቲከኞች ለሥልጣን የሚያበቃቸው ወሳኝ ኃይል ሕዝብ ስለሆነ እሱን በሚገባ ማክበር እንዳለባቸው ነው፡፡ የሕዝብ ፈቃድ ፈጻሚ ናቸውና፡፡ በሕዝብ ድምፅ እንዳኛለን የሚሉ ፖለቲከኞች የሕዝብ መብት የሚረግጡ፣ ነፃነቱን የሚገፉ፣ በስሙ የሚቀልዱና ኢዲሞክራሲያዊ ተግባራትን የሚያከናውኑ ከሆኑ መገለጫቸው አምባገነንነት ነው፡፡ ሕዝብ ነፃነቱን ይፈልጋል ማለት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ እንዲከበሩለት ይሻል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥልጣንም ያዙ አልያዙ ለሕዝብ ፈቃድ ታዛዥ መሆን አለባቸው፡፡ ሕዝብ ሰላሙን ይፈልጋል፣ የሕግ የበላይነት እንዲኖር አጥብቆ ይጠይቃል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሰላማዊ መንገድ አፈንግጠው የብጥብጥና የትርምስ መሐንዲሶች እንዳይሆኑ ይሻል፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሠረታዊ አቋሞቻቸው እንደተጠበቁ ሆነው፣ በዴሞክራሲያዊ ሒደቶች ላይ በመደራደር ነፃና ሰላማዊ ድባብ እንዲፈጠር ተግተው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በተለይ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ድርድር ለማድረግ ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ ድርድር በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ ተመሥርቶ መካሄድ ሲኖርበት በሰባራ ሰንካላ ምክንያቶች ተቀራርቦ ከመነጋገር ይልቅ፣ ተለያይተው በየፊናቸው መንጎድ ይቀናቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ የሰላማዊውን የፖለቲካ ትግል ሥልት በመከተል በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ዳገት ሆኖባቸዋል፡፡ ገዥው ፓርቲ ተቃዋሚዎች ለሕዝቡ የሚፈይዱት አንዳችም ጠቃሚ ነገር የለም ብሎ በመደምደም በሩን ሲዘጋጋባቸው፣ ተቃዋሚዎችም ያዚያኑ ያህል ፋይዳ ቢስነህ በማለት ያጣጥሉታል፡፡ በፀረ ዴሞክራሲያዊነት ይፈርጁታል፡፡ ሁለቱም ወገኖች በተለያዩ መድረኮች መደራደር እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ ቢናገሩም፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ መጎልበት ድርድር ጠቃሚ በመሆኑ የእንደራደር ግብዣ ቢያቀርቡም ተግባራዊ ማድረግ አልቻሉም፡፡ በዚህ የተነሳ አየሩን የሞላው ጥላቻና ክፉ መንፈስ ነው፡፡ ለዴሞክራሲ ሲባል ግን ሰላምን ማስቀደም የሚጠቅመው አገርን ነው፡፡ አገርን ማዕከል ያላደረገ ሥልጣን ፍለጋ ለማንም አይበጅም፡፡ በማንኛውም የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሒደት ውስጥ ከጥላቻ ይልቅ ድርድር ይቀድማል፡፡ ሰላምን በማስፈን ዴሞክራሲን ለመገንባት በሚደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ለብጥብጥ ቦታ አለመስጠት ነው፡፡ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ሥልጣን ለመያዝ የሚታገል ማንኛውንም ዓይነት ርዕዮተ ዓለም የሚከተል ፓርቲ፣ በምንም ዓይነት መንገድ ብጥብጥን የዓላማው ማሳኪያ ለማድረግ አይነሳም፡፡ ይልቁንም ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲያብቡና ሕዝቡ በነፃነት የየዕለት ሕይወቱን እንዲመራ መደላደሉን ያመቻቻል፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ጉልበት፣ ሕገወጥነት፣ አፈና፣ አጭበርባሪነትና አመኔታ ማጣት አይፈለግም፡፡ ለዚህም ነው ተፎካካሪዎች ከአመፅ ይልቅ ድርድር ያስቀድሙ የሚባለው፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያምኑበትን ዓላማ በነፃነት እያቀነቀኑ ለብሔራዊ መግባባት ግን በሩን መጠርቀም የለባቸውም፡፡ ድርድር የግድ ነው መባል አለበት፡፡ የፊታችን ግንቦት የሚካሄደው ምርጫ በተቃረበበት ወቅት ገና ከአሁኑ የድርድርን በር የሚዘጉ የሚመስሉ ትዕይንቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ ሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር አለመግባባት ፈጥረዋል፡፡ እነሱ ምርጫ ቦርድ ገዥውን ፓርቲ ወክሎ ችግር እየፈጠረብን ነው በማለት ላይ ናቸው፡፡ ገዥው ፓርቲ ምርጫ ሲመጣ የተለመደ ጩኸታቸውን ማሰማታቸው የተለመደ ነው በማለት ይወነጅላቸዋል፡፡ እዚህ ላይ ቆም ተብሎ መታሰብ ያለበት ሁሉም ፓርቲዎች በሕዝብ ዳኝነት የሚበየንባቸው መሆኑን ነው፡፡ ሕዝቡ የመምረጥ መብቱን ተጠቅሞ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ሲፈልጉ በእርግጥም ሒደቱ ሰላማዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ መሆን ይኖርበታል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በዝቅተኛው የዴሞክራሲ መሥፈርት መሠረት ምርጫ የሕዝብ ፍላጎት በነፃነት የሚገለጽበት ሒደት መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ለመምረጥ የሚያስችለውን ምዝገባ እንዲያካሂድ በማድረግ በሰላማዊ መንገድ መወዳደርን ቅድሚያ ሊሰጡት ይገባል፡፡ ይህ ጤነኛ አካሄድ እንዲኖር ለማድረግ ካላስፈላጊ ውዝግብና ኢዲሞክራሲያዊ ጎዳና መውጣት አለባቸው፡፡ ድርድር የሰላማዊ ትግሉ መገለጫ ይሁን፡፡ አሁንም ትኩረት ለብሔራዊ መግባባት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...